ወላጆችና ልጆች

በቦጋለ ወልዴ

ብዙ ወላጆች በሰል ያለና የላቀ ጥበብ ይጐድላቸዋል ሲል ብስልስል ያሉ የተቀመሩ ጥናታዊ አመለካከቶችን በየአንጓቸው እየቃኘ ዶ/ር ኤርሲዶ ለንደቦ “ኑሮ” የተሰኘውና ለህትመት የበቃው መፅሐፍ “እያንዳንዱ ሰው የራሱ ህይወት ቀራፂ ነው!” በሚል ይዘት የአስተሳሰብ ባህላችንን ቃኘት ማድረግ እንደሚያሻን የዘከረውን በዋቢነት እኔም ለጋዜጣችን አምድ እንደሚሆን አብረን ልንቋደሰው በመሻቴ እነሆ ይድረስ ብያለሁ፡፡

ልጆቻችን የዓመቱን የሁለተኛ መንፈቅ ፈተና እየተፈተኑ ይገኛሉ፡፡ ከፊሎቹም በወርሃ ሰኔ የመጨረሻው ሳምንት ማጠናቀቂያ ላይ በየደረጃው የሚፈተኑ ተማሪዎቻችን ፈተናቸውን ሲያጠቃልሉ፣ በተለምዶ በክረምቱ በሚጋሩት የእረፍት ጊዜያቸው መርሃ ግብር ከወላጆች፣ ከማህበረሰቡ፣ ከሚመለከታቸው መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ አጋሮቻችን ምን ምን ዓይነት ገንቢ የሆኑ ድጋፍና ሁለንተናዊ የማጐልመሻ ክህሎቶችን እንዴትና በምን መንገድ ይጋሩ ይሆን? ይህቺን ያህል ዳር ዳር ካልኩኝ የመጽሐፉ አዘጋጅ ወላጆችና ልጆች ሲል ባሳፈረው ንዑሰ ርዕሰ ጉዳይ እንደሚከተለው ያመላክተናል፡፡

ብዙ ወላጆች ብስል ጥበብ ስለሚጐድላቸው ልጆቻቸውን የጠቀሙ እየመሰላቸው ተደጋጋሚ ስህተት ሲሰሩ እንመለከታለን ሲል ወቀሳ ቢጤ አቅርቦልናል፡፡ ይበልጡን በሚኖራቸው በቂ መጪው ጊዜያት ልጆች በቀላል ምክርና ድጋፍ በአጭር ስልጠናና ልምምድ ብዙ ነገሮችን ማከናወን ይቻላሉ፡፡ የማከናወን ኃላፊነትም አለባቸው፡፡ አስደሳች ህይወትን እውቀትና ከህሎት በማዳበር /የስኬት ስራ መስራትን፣ ማለትም ብቃትን የመገንባት/ የልጆችን ኃላፊነት እንደሸክም የሚቆጥር ወላጅ ሸክሙን ወደ ራሱ አንሸራቶት እየሰራ ፣ ውጤቱን ብቻ /የስኬት ምልክቱን ብቻ/ ይሰጣቸዋል፡፡

ነገር ግን ልጆቹን የጠቀመ ይመስለዋል እንጂ የስኬት ስራ መሠረተ ብቃትን /እውቀትንና የህይወት ክህሎትን/ ለመገንባት የሚያስችላቸውን እድል እየነፈጋቸው ነው፡ ሁልጊዜና ሁሉም ነገር በሌላ ሰው እንዲዘጋጅላቸው እንዲቀርብላቸው የሚፈልጉ፣ ከሰው የሚጠብቁ ደካማ ልጆች ይሆናሉ፡፡ ልብስ መልበስና ጫማ ማሰር ያለመዱ ህፃናት በርካታ በመሆናቸው፣ አንዳንድ ት/ቤቶች ለ7 ዓመት ልጆች ጫማ ማሰርን ሲያስተምሩ ይታያሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ በራስ ማጉረስም ሸክም ሆኖ፣ ሁልጊዜ ህፃናትን በጉርሻ ብቻ የሚመግቡ አላዋቂ ወላጆች ጥቂት አይደሉም፡፡ ህፃናቱ መጥገብና /የስኬት ምልክት/ ብቻ በቁንፅል የሚያዩ ወይም በየቅፅበቱ ረሃብን /የችግር ምልክትን/ ማስታገስ ብቻ የሚመለከቱ ይሆናሉ፡፡

በአንፃሩ ስኬትን እውን የማድረግና ለዚህ የሚያስፈልጉ ከህሎቶችንና ኃላፊነቶችን ለማሟላት ግን ፍፁም አቅም የሌላቸወ ይሆናሉ፡፡ ብሎም ኃላፊነታቸውንም ወደ ሌላ አካል ያንሸራትታሉ፡፡ ጥበብ የጐደለው የወላጆች ድጋፍ ልጆች ነገሮችን ሁላ የራሳቸው ውጥን ድምዳሜ ላይ እንዳይደርሱ፣ እንዳይጠይቁና

ኃሳባቸውን እንዳይገልፁና እንዳይናገሩ ፣ ብሎም ጥሩና መጥፎውን እንዳያመዛዝኑና በራሳቸውም እንዳይወስኑም ይዳርጋቸዋል፡፡ እንዲሁም ይኸው ጥበብ የጐደለው የአስተሳሰብ ባህል የልጆችን የማገናዘብ፣ የመመርመርና የማመዛዘን ሃላፊነት ወደ ራሱ ስለሚወስድና ስለሚሸከም ነው፡፡ ፀሐፊ ዶ/ር ኤርሲዶ ለንደቦ እንዲሁም ልብ ያስተዋለውን ልብ እንድንል እንዳሰፈረው፡- ወላጅ ልጆችን ተክቶ ይናገራል፡፡

ልጆች በራሳቸው መረጃን በመትጋት እንዳያገኙ፣ አማራጭ እውቀትንና የማገናዘብ ክህሎትን እንዳያዳብሩ እድል በመዝጋት ወላጅ ልጆችን ተክቶ ድምዳሜ ስለሚያቀርብላቸው ራሳቸውን ችለው እንዳይመራመሩ ስለሚገድባቸው የምርምር ክህሎታቸውን ስለሚያግድ በራሳቸው የበቁና የተሻሉ ሆነው እንደሚፈለገው /ከፍ ያለ ውጤትን/ በግልና በጋራ ማስመዝገብ እንደሚሳናቸው አብራርቶታል፡፡ እኛስ የወላጅነት ሚናችን ምን ይመስል ይሆን? “ኑሮ” የተሰኘውን የጥበብ አንኳር መጽሐፍን ጀባ ! ለእናንተ ያሉን ዶ/ር ኤርሲዶ እንደዚህም “እኔ የምልህን ብቻ ስማ” የሚሉ አንዳንዱ ወላጅ፣ ልጆቹ አገናዝበው የደረሱበትን ሃሳብ ትክክልም ቢሆን ከልክ ባለፈ ቁጣና ቁጥጥር ይከለክላል።

ይህ ደግሞ አታገናዝብ እንደማለት ይሆናል፡፡ አንዳንድ ወላጅ ደግሞ ልጆቹ ያለ እውቀትና ሳያገናዝቡ የሚናገሩትን ሐሳብ እያሞገሰ መረን ይለቅቃቸዋል፡፡ ይኸኛውም በአንፃሩ ማወቅና ማገናዘብን ጭራሽ ይጋፋዋል፡፡ ወላጅ ሁሌም እራሱ እየወሰነ “የአድርግ አታድርግ ትእዛዝ ይሰጣቸዋል፡፡ ልጆቻቸው ጥሩን ከመጥፎ የሚለዩበት የሥነ ምግባር መርህን እንዳያውቁ፣ የማመዛዘንና በራስ ውሳኔ የመመራት ክህሎት እንዳይገነቡ እየገደበ አጉል ያደርጋል፡፡ “ከላይ እንደተገለፀው “እኔ ያዘዝኩትን ብቻ አድርግ” የሚል ወላጅ ልጆቹ አመዛዝነው በራሳቸው የወሰኑት መልካም ነገር ቢሆን እንኳ በቁጥጥር አባዜ ይከለክላቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ የሚያመለክተው ደግሞ ልጆቹን “የማመዛዘን ኃላፊነት አያስፈልጋችሁም” እንደማለት፡፡

አንዳንዱ ወላጅ ደግሞ ልጆቹ ያለእውቀትና ሳያመዛዝኑ መጥፎ ነገር ሲወሰኑና ሲፈፅሙ እያየ፣ “ደግ አደረጋችሁ” ብሎ ያባብላቸዋል። ይህ ደግሞ “የማመዛዘን ኃላፊነት የለባችሁም” እንደማለት ነው ይለናል ዶክተሩ፡፡ ልጆች እውቀትንና መርህን እንዲጨብጡ ፣ የማገናዘብና የመማዛዘን ክህሎት እንዲያዳብሩ በዚህም የግል መብታቸውን እያከበሩ የሌሎችንም የማክበር፣ ከእኩዮቻቸው ጋር እውነትንና እውቀትን በመሻት ኃሳብ የመለዋወጥና የመተባበር፣ አለመግባባትንና ልዩነትንም በሰላም የመፍታት እውቀትና ክህሎት እንዲያዳብሩ ማገዝ ያስፈልጋል፡፡

ብዙ ወላጆች ግን “አድርግ አታድርግ” ብሎ የትእዛዝና የቁጥጥር አጥር ውስጥ የሚከረችም ወይም “ያሻቸውን ቢያደርጉ እኔ አለሁላቸው” ብሎ እቅፍ ውስጥ እያሞላቀቀ የሚያሟሟ የልጅ አስተዳደግን ሲሞክር ይታያል፡፡ እቅፍ ውስጥ ሆኖ ለጊዜው ችግር ባይኖር እንኳ ከእቅፍ የወጣ ቀን እንዴትስ ሊሆነው ሲል ምላሹን እንድናብላላው ያመላክተናል፡፡ በተለይ ገንዘብን፣ ፆታን፣ ግንኙነትን፣ የቤተሰብ አስተዳደርን በዚህ ውስጥም የልጆች ሚና በተመለከተ፣ ልጆች በትክክለኛ ጊዜና መጠን በመረጃ እንዲያውቁና ቀስ በቀስ እንዲለማመዱ ማድግ ሲገባ፣ ወላጅ ሁሉንም ኃላፊነት በራሱ ሲወጣው ስለሚቆይ፣ ልጆች ያለእውቀት፣ ያለመርህና ያለክህሎት ያድጋሉ፡፡

ዳሩ ግን ልጆች ለዘለዓለም በወላጆች ቁጥጥር ወይም እቅፍ ውስጥ ሊቆዩ አይችሉም፡፡ ጊዜው ደርሶ ፣ ልጆች ከቤተሰብ ተለይተው ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ የቤተሰብ የቁጥጥርና የእቅፍ ህይወት እንደ”ባርነት ጊዜ” በመቁጠር ፣ በዘፈቀደ የማድረግ “ነፃነት” ያገኙ ይመስላቸዋል፡፡ እናም እውቀትንና መርህን ፣ የማገናዘብና የማመዛዘን ክህሎትን ስላላዳበር፣ የ”መረንነት” የ”ነፃነትን” ልዩነት በውል አይረዱትም፡፡ ከዚህም የተነሳ ለአደገኛ ሱሶች፣ ጥንቃቄ ለጐደለው ወሲብ፣ ሴቶቹ ላልተፈለገ እርግዝናና ኤች አይ ቪ ኤድስን ለመሳሰሉት ጣጣዎች፣ ከኮሌጅ እና ከዩኒቨርሲቲዎችም በሙሉ አቅማቸው ትምህርታቸውን ስለማይከታተሉ የትምህርታቸውን ገበታ ሳያጠናቅቁ የመባረር እድል ሊገጥማቸውም እንደሚችል ጭምር አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያመለክቱ ዶ/ር ኤርሲዶ እንድናስተውል አበክረው ጠቁመዋል፡፡

እኚህ ለአብነት ያህል ከጠቃቀሱልን በተጨማሪ እንዲሁም አትተውልናል፡፡ ሌላው ችግር፣ የእናትና አባትን ኃላፊነት ያለ እድሜ ወደ ልጆች በማስተላለፍ ልጆች ከሚችሉት በላይ ቤተሰብን የመደገፍ ኃላፊነት እንዲሸከሙ ማድረግ ነው፡፡ ሌላው አይነት shifting the Burdens ቤተሰብ ልጆቹን የሚያዛልቅ እውቀትንና ክህሎትን በማያዳብር ሥራ ላይ ይጠምዳቸዋል፡፡ በዚህም ሰበብ የትምህርት እድል ያጣው ልጅ እውቀት ሳያካብት፣ ሁሌም ክህሎትን በማያዳብር ስራ ላይ ተጣብቆ በዝቅተኛ ገቢ ኑሮ የሚገፉ ይሆናል፡፡ ልጆች የተጐዱ ወላጆቻቸውን መደገፋቸው ጥሩ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ልጆች የሚወለዱት ወላጆችን ለመጦር ነው ብሎ በልጆች ላይ ኃላፊነትን መጫን ግን ትልቅ ስህተት ነው፡፡

ልጅን “ይጦረኛል” የሚለው አስተሳሰብ በሃገራችን እንደባህል ስለተያዘ ብዙ ሰዎች ያለ እቅድ ይወልዳሉ፡፡ እድሜ ለገፋ እለት /ለእርጅና/ ጊዜ የሚጠቅም ገንዘብ ብዙዎቹ አይቆጥቡም። እንዲህ ዓይነቱ ሰር የሰደደ ባህል ኃላፊነትን እንደሸክም አንፏቆ ወደሚቀጥለው ትውልድ የሚጭን ጐጂ ልምድ ነው በማለት ዶ/ር ኤርሲዶ ለንደቦ በእርግጥም በዘመነ የአስተሳሰብ ባህል ፋና ወጊ እንድንሆን “ኑሮ” በተሰኘው መጽሐፉ አደራ ማለቱን ወድጄ አጋርቻለሁና እኛም አበክረን የአስተሳሰባችንን ባህል መፈተሹ አይበጅም ትላላችሁ?