ባለፉት ሶስት አመታት በሁሉም ዘርፎች በክልሉ አመርቂ ዉጤቶች ተመዝግበዋል – ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ

ባለፉት ሶስት አመታት በሁሉም ዘርፎች በክልሉ አመርቂ ዉጤቶች ተመዝግበዋል – ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ

ሀዋሳ፡ ሰኔ 27/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) ባለፉት ሶስት አመታት በሁሉም ዘርፎች በክልሉ አመርቂ ዉጤቶች መመዝገባቸውን የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ገለጹ፡፡

የሲዳማ ክልል ምስረታ 3ኛ አመት በተለያዩ ዝግጅቶች በሀዋሳ እየተከበረ ነው።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ በዓሉን አስመልክተው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የክልሉን ህዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተሰሩ ስራዎች በሁሉም ዘርፎች አመርቂ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።

የሲዳማ ህዝብ እራሱን በራሱ ለማስተዳደር ለዘመናት የታገለው ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጥያቄዎቹ እንዲመለሱለት ነበር ያሉት አቶ ደስታ አሁን ላይ ጥያቄዎቹ ደረጃ በደረጃ እየተመለሱ እንደሆነ አመላክተዋል።

የክልሉን ቀበሌያት እርስ በእርስ በመንገድ ለማስተሳሰር በተሰሩ ስራዎች 85 በመቶ የሚሆኑ የክልሉ አካባቢዎች እርስ በእርስ መተሳሰራቸውን ገልጸዋል።

የክልሉን የንፁህ መጠጥ ውሃ ሽፋን ለማሳደግ የተሰራው ስራ ዉጤታማ መሆኑን ተናግረዋል።

የትምህርት ሽፋንን ለማሳደግ መንግስት ከሚሰራው መደበኛ ስራ ጎን ለጎን ባለሀብቶችን በማሳተፍ በርካታ ትምህርት ቤቶች ለአገልግሎት እየበቁ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ የትምህርት ጥራትም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል።

3 ሆስፒታሎችና 13 ጤና ጣቢያዎች የተገነቡ ሲሆን 20 ነባር የጤና ተቋማት ደግሞ ከፍተኛ ጥገና በዚሁ ወቅት መደረጉም ተጠቅሷል።

ክልሉ ፖለቲካዊ እምርታዎችን አስመዝግቧል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሃገራዊ አጀንዳዎች ላይ በንቃት ተሳታፊ መሆን መቻሉን አስረድተዋል።

የክልሉን ሰላምና መረጋጋት ማረጋገጥ በመቻሉ ባለፉት አመታት የሀገሪቱን ታላላቅ ኩነቶችን በብቃት ክልሉ ማስተናገድ መቻሉ ትልቅ ትርጉም ለክልሉ ህዝብ እንዳለውም አንስተዋል።

በጥቂት አመታት የተገኙ አመርቂ ውጤቶችን በማጠናከር ድክመቶችን በማረም መላው የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ የክልሉ መንግስት እንደሚሰራ ርዕሰ መስተዳድሩ አረጋግጠዋል።

ዘጋቢ፡ ጀማል የሱፍ