በዩኒቨርስቲው የመውጫ ፈተና (Exit Exam) ለሚወስዱ 4ሺህ 7መቶ በላይ ተማሪዎች  በቂ ዝግጅት ማድረጉን  የዋቸሞ ዩኒቨርስቲ  አስታወቀ

ሀዋሳ፡ ሰኔ 17/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ)በዩኒቨርስቲው የመውጫ ፈተና (Exit Exam) ለሚወስዱ 4ሺህ 7መቶ በላይ ተማሪዎች  በቂ ዝግጅት ማድረጉን  የዋቸሞ ዩኒቨርስቲ  አስታውቀዋል።

በዋቸሞ ዩኒቨርስቲ የአካዳሚክ ፕሮግራሞች ዳይሬክተር ዶ/ር ሙላቱ ኦሴ በትምህርት ሚኒስቴር በኩል የትምህርት ጥራትን ለማሳካት ከተያዙ ዕቅዶች አንዱ የሆነውን የመውጫ ፈተና በዩኒቨርስቲው ለመስጠት ባለፉት ወራት የተለያዩ ዝግጅቶች ሲደረጉ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

በፈተናው ከዩኒቨርስቲው 2ሺህ 9መቶ 91 ተማሪዎች ከግል ኮሌጆች ደግሞ 1ሺህ 7መቶ 49 በድምሩ 4ሺህ 7መቶ 40 ተማሪዎች ፈተናውን እንደሚወስዱ ገልፀዋል።

ፈተናው በበየነ-መረብ የሚሰጥ እንደሚሆኑ መጠን ኮምፒውተሮችና ሌሎች ተያያዥ ግብዓቶች (VDI ROOM) መሟላት፣ አውቶማቲክ ጀነሬተር መዘጋጀት፣ ለተማሪዎች የመለኪያ ፈተና መሰጠት፣ የማካካሻ ትምህርቶችን ጨምሮ የኮምፒውተር ልምምድና ሌሎች የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ስለማከናወናቸውም አንስተዋል።

በመውጫ ፈተና ወቅት ችግሮች እንዳይከሰቱ በዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት የሚመራና የኮሌጆችን ዲኖች ያቀፈ እንዲሁም ሌሎች  ባለድረሻ አካለት ያሉበት ግብረሃይል ተቋቋሞ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ ብለዋል::

በዩኒቨርስቲው ያነጋገርናቸው ተፈታኝ ተማሪዎችም ባለፉት  ወቅት ለመውጫ ፈተና ራሳቸውን ሲያዘጋጁ  እንደነበሩ ገልፀው ዩኒቨርስቲው ለፈተናው የሚረዱ ስልጠናዎችን፣ የበይነመረብ ልምምድ ስራዎች ተከናውኗል ብለዋል።

ተማሪዎች በስነልቦና ረገድ ራሳቸውን በማዘጋጀት በቀረው ጊዜ ዝግጅቶቻቸውን እንዲያደርጉ መክረዋል።

ዘጋቢ፡ ሄኖስ ካሳ – ከሆሳዕና ጣቢያችን