የኢትዮጵያ የኩላሊት ሕመም ማህበር ለምክር ቤት አባላት እና ሠራተኞች ነጻ የኩላሊት፣ የደም ግፊት እና የስኳር ሕክምና አገልግሎት ሰጠ

የኢትዮጵያ የኩላሊት ሕመም ማህበር ለምክር ቤት አባላት እና ሠራተኞች ነጻ የኩላሊት፣ የደም ግፊት እና የስኳር ሕክምና አገልግሎት ሰጠ

ሀዋሳ፡ ሰኔ 16/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) ለኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እና ሰራተኞች በኢትዮጵያ የኩላሊት ሕመም ማህበር የተዘጋጀ ነጻ የኩላሊት፣ የደም ግፊት እና የስኳር ሕክምና አገልግሎት ተሰጥቷል።

በዕለቱም፤ አገልግሎቱን አስመልክቶ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባዔ ወ/ሮ ሎሚ በዶ የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል።

በንግግራቸውም፤ በአሁኑ ወቅት የኩላሊት በሽታ በዓለማችን የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን እየጎዳ ይገኛል ያሉ ሲሆን፤ ማህበሩ ነፃ የኩላሊት ምርመራና የምክር አገልግሎት በመስጠቱ አመስግነዋል።

በቀጣይነትም ምርመራው በሀገር-አቀፍ ደረጃ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች፣ የመንግስት እና የግል ተቋማት እንዲሁም የሕብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ እንዲሆን ምክር ቤቱ ድጋፍ እንደሚያደርግ ምክትል አፈ-ጉባዔዋ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የኩላሊት ሕመም ማህበር መስራች እና ሊቀ-መንበር ዶክተር ሊሳን ሰይፉ በበኩላቸው፤ በዓለማችን ከሚገኙ ከአስር ሰዎች መካከል አንድ ሰው በኩላሊት በሽታ ተጠቂ እንደሆነ ጠቁመው፤ በሽታውም በአንዳንድ ሰዎች ምንም አይነት ምልክትን ሳያሳይ ለከፋ አደጋ ሊያጋልጥ ስለሚችል ሕብረተሰቡ የቅድመ-ምርመራ ልምድን እንዲያሳድግ አሳስበዋል።

የደም ግፊት፣ የስኳር ህመም፣ ረቂቅ ተሕዋስያን፣ ከፍተኛ ውፍረት፣ የዕድሜ መግፋት፣ አልኮል መጠጣት እንዲሁም ሲጋራ ማጨስ ለኩላሊት ህመም አጋላጭ መሆናቸውንም ዶክተር ሊሳን ገልጸዋል።

ማህበሩ መከላከል ላይ ትኩረት በማድረግ ግንዛቤ የማስጨበጥ እና ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ እንዲኖር እንደሚሠራ ዶክተሯ ተናግረዋል።

ዶክተሯ አክለውም፤ ጤናማ የአመጋገብ ሥርአትን እና የአኗኗር ዘይቤን በመከተል ተላላፊ ላልሆኑ የጤና እክሎች ተጋላጭነትን መቀነስ እንደሚቻል አስረድተዋል።

ምንጭ ፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት