ወጣቶችን የመረጃ ተጠቃሚዎች በማድረግ ከሥነ ተዋልዶ የጤና ችግሮች እንዲላቀቁ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን መወጣት እንደሚገባቸው ተገለፀ

ወጣቶችን የመረጃ ተጠቃሚዎች በማድረግ ከሥነ ተዋልዶ የጤና ችግሮች እንዲላቀቁ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን መወጣት እንደሚገባቸው ተገለፀ

ሀዋሳ፡ ሰኔ 15/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) ወጣቶችን የመረጃ ተጠቃሚዎች በማድረግ ከሥነ ተዋልዶ የጤና ችግሮች እንዲላቀቁ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን መወጣት እንደሚገባቸው ተገልጿል።

ወጣቶች በሥነ ተዋልዶ ጤና ችግሮች ላይ የተለያዩ መረጃዎችን ማግኘት የሚችሉበት ነፃ የስልክ መስመር አገልግሎት ለባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ክልል አቀፍ ሥልጠና በጌዴኦ ዞን ዲላ ከተማ ተሰጥቷል።

መድረኩን በንግግር የከፈቱት የደቡብ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊና የወጣቶች ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሙስጠፋ ኢሳ እንደተናገሩት የወጣትነት ዕድሜ ለዘርፈ ብዙ አካላዊና ሥነልቦናዊ ችግሮች የተጋለጠ መሆኑን በመጠቆም በወጣቶች ዘንድ በሚስተዋለው የመረጃ አጠቃቀም ክፍተት ምክንያት ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መዘዞች እየተዳረጉ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በወጣቱ ትውልድ ዘንድ የሚስተዋሉ ችግሮች በአብዛኛው ሀገርን ዋጋ እያስከፈሉ መሆኑን በመግለፅ በቀጣይ ክልሉ ባለው የሚዲያ አማራጮች በመጠቀም በልዩ ትኩረት ሊሠራበት እንደሚገባም አስታውሰዋል።

ሀገርን ለማልማት በሚደረገው ርብርብ ጤናማና አምራች ወጣቶችን ማፍራት የመጀመሪያው ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ መሆኑን ያብራሩት አቶ ሙስጠፋ በወጣቶች ስብዕና ግንባታ ላይ ሁሉም መረባረብ እንዳለበትም አሳስበዋል።

በቀጣይም በክልሉ በሁሉም መዋቅር ላይ በዘርፉ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እንደሚያደርጉ ገልፀው የወጣቶችን ስብዕና ከመገንባት ረገድ ቤተ እምነቶችና የባህል ተቋማት የላቀ ሚና ስላላቸው የበኩላቸውን እንዲወጡም አስገንዝበዋል።

ስልጠናውን የሰጡት የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ የቤተሰብ ዕቅድና አፍላ ወጣቶች ጤና ባለሙያ አቶ መሪሁን ገብሬ  በበኩላቸው የነገው ሀገር ተረካቢ ወጣቶች በሱስና በልዩ ልዩ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እየተጎዱ በመሆናቸው ችግሩን ለመቅረፍ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ካልተረባረቡበት አስቸጋሪ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ መሆናቸውን አብራርተዋል።

አያይዘውም በወጣቶች ስብዕና ላይ በትኩረት መሥራት ለነገ የማይባል ጉዳይ ነው ያሉት ባለሙያው በሕይወታቸው ደስተኛ፣ ጤናማና አምራች ዜጎችን ለማፍራት በወጣቶች ሁለንተናዊ ስብዕና ግንባታ ላይ መትጋት ይኖርብናል ብለዋል።

አቶ ደግነት ኃይሉ የጌዴኦ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያው ኃላፊ ሲሆኑ የወጣቶች የሥነተዋልዶ ጤና ችግር ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በጌዴኦ ዞን ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ጤናማ ወጣቶችን ከመፍጠር ረገድ ትልቁን ሚና የሚጫወተው ቤተሰብ መሆኑን የተናገሩት የመምሪያው ኃላፊ አቶ ደግነት ይህን ከግምት በማስገባት መምሪያው በዞን ደረጃ ከባለድርሻ አካላትና ከወጣቶች አደረጃጀት ጋር በዘርፉ ግብረ ኃይል አቋቁመው ርብርብ እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በስልጠናው የክልልና የዞኑ ጤና ቢሮ ኃላፊዎች፣ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ኃላፊዎች፣ የጤና ባለሙያዎችና የሚዲያ አካላት ተሳትፈውበታል።

ዘጋቢ፡ እስራኤል ብርሃኑ – ከፍሰሃገነት ጣቢያችን