ካክሆቭካ፤ግዙፉን የውኃ ማዘያ ግድብ ማን ደረመሰው?

ካክሆቭካ፤ግዙፉን የውኃ ማዘያ ግድብ ማን ደረመሰው?

በፈረኦን ደበበ

በአብሮነት ይኖሩ ለነበሩ ህዝቦች የህይወት መሠረት ነበር፡፡ የልማት ቀንዲል፤ የዕድገት ፋና ወጊ የሆነ መሠረተ-ልማትም ነበር -ግዙፉ ግድብ፡፡ ይሁንና የቆመበትን ዓላማ ስቶ ሰሞኑን የውድመቶች መንስኤ ሆነ፡፡

አንጀቱ ተዘረገፈ፡፡ የያዘውን ሀብትና ንብረት ተፋ፡፡ አጉረመረመ፡፡ ያሳደጋቸውን ሰዎችም ሆነ እንስሳትን ጠራርጎ ወሰደ፡፡

አንዳንዶች “ትልቁ በሰው አማካይነት የተፈጸመ አካባቢያዊ ውድመት” ብለው የጠሩት አደጋ እርግጥም ባለፉት 10 ዓመታት ከታዩት ድንገተኞች መካከል ከፍተኛው ነው። የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ በመሠረተ ልማት ላይ ከደረሱ ውድመቶች ተጠቃሽ ሆኖም ነው የሚታየው፡፡

በሙሉ መጠሪያው ኖቫ ካክሆቭካ ተብሎ የሚጠራው ግድብ ቀደም ባለ ጊዜ በሶቪየት ህብረት የተገነባ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ በ1956። ከዚያ ወዲህ የሩሲያና ዩክሬን ህዝቦች እምብርት ከመሆን አልፎ አካባቢውን አልምቷል፡፡ ከእርሻ ሥራ ባለፈ ኤሌክትሪክና ለኒውክሌር ኃይል ምንጭነትም ድጋፍ ሆኗል፡፡

የተሰጋው ግን አልቀረም፡፡ ሰሞኑን የደረሰበት ከባድ የመሣሪያ ጥቃት ግድቡን ሰብሮበታል፡፡ በውስጡ የያዛቸው እምቅ ሀብቶችንም እንዲዘረግፍ አድርጓል። ከያዘበት ዓላማ ውጭ የተፈጥሮ አካባቢውንም ጠራርጎ በመውሰዱ ጭምር፡፡

ሩሲያና ዩክሬን አሁን አንዱ ሌላኛውን እየወነጀሉ ባሉበት ማን መታው? እንዴትና በምን ዓይነት መሣሪያ ተመታ ? የሚለውም ጉዳይ እያነጋገረ ነው፡፡ ዲንፕሮ በሚባለው ግዙፍ ወንዝ ላይ ተንጣሎ ፤ በአንድ በኩል እንደ ትልቅ የውኃ ግድብ በሌላ በኩል ደግሞ እንደ ድልድይ ሆኖ ፣ ሰዎችን ከአንድ ጫፍ ወደ ሌላው የሚያሸጋግረው ግንብ አሁን የለም፡፡

እነዚህ አሳዛኝ ክስተቶች ሰዎች ለምን እርስ በርስ እንዲህ ይጨካከናሉ የሚያሰኝ ነው፡፡ ሁለቱን ህዝቦች ሳይሰስት እየጠቀመ ባለው ንብረት ላይ ለምን እሳት ወረወሩበት? ብሔራዊ ጥቅማቸው ከጋራ መገልገያቸው ይበልጣል? የሚሉ ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡

አዎን ጊዜው ሩሲያ የመጨረሻውን ጥቃት ፈጽማ ወሳኝ የሆነውን የባክሙት ምድር በእጇ ያስገባችበት ነበር፡፡ ዩክሬን በበኩሏ በደረሰባትን ኪሳራ ሀዘን የተቀመጠችበት። ረዘም ካለ ጊዜ በፊት የወጠነችው የመልሶ ማጥቃት እርምጃ መዳረሻ፡፡

አሁንም ድርጊቱን የፈጸመው ማን እንደሆነ በውል አልታወቀም፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለም መሠረተ ልማቱ ለሁለቱ ሀገራት እኩል የሚያገለግል ከመሆን ባለፈ በሳምንቱ የነበረው ከፍተኛ የውኃ ግፊት ግድግዳውን አፈረሰ የሚሉ መላ ምቶችም እየተሰነዘሩ ነው፡፡

ብዙ ወታደራዊ የመረጃ ተንታኞች ሁሉ የተጋሩት ይህ ሀሳብ ግን ረጅም ዘመን ህዝቡን ሲያገለግል ለቆየው ግድብ መዘርገፍ ተዓማኒነት ያለው ምክንያት ሊሆን አይችልም፡፡ ለምን ቢባል ቦታው በዋናው የውጊያ ግንባር ላይ ከመሆን ባለፈ አስቀድሞ በተመሳሳይ ሁኔታ ዩክሬን በሩሲያ ላይ ካደረሰቻቸው ውድመቶች ጋርም ስለሚመሳሰል፡፡

አሁንም ከተፏፏመው ውጊያ ሳንወጣ በተግባር ላይ ያሉ ወታደራዊ ስትራቴጂ እና ታክቲኮችን መውሰድ እንችላለን፡፡ ግድቡ የሁለቱ ህዝቦች የጋራ ሀብት ሆኖ ቢያገለግላቸውም ዩክሬን አስቀድማ ሥጋቷን እየገለጸች የቆየችበት ሁኔታ መኖሩ የድርጊቱ ፈጻሚ እራሷ እንዳልሆነች የሚያስመስል ነው፡፡

ድርጊት ፈጻሚዋ ዩክሬን እንዳልሆነች የሚያሳየው ሌላ መረጃ ደግሞ ሩሲያ ድሏን ለመጠበቅ ትዘጋጅ የነበረችበት ወቅት ሲሆን ዩክሬን በበኩሏ ለመልሶ ማጥቃት ዝግጅቷን እያጠናቀቀች የነበረችበት ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ዩክሬን ድልድዩን ለመሸጋገሪያነት ትፈልጋለችና ይህንን የሚደናቅፍ ተግባር ትፈጽማለች ተብሎ አይጠበቅም፡፡

የሆነ ሆኖ ኖቫ ካክሆቭካ ተደርምሷል፡፡ የተጣለበትን ልማታዊ ኃላፊነቱን ትቶ ወደ አውዳሚነት ተቀይሯል፡፡ የእርሻ መሬቶችን ጠራርጓል፡፡ ሰዎችና እንስሳትን በልቷል። ዛፖሮዥሃ ለተባለውን የአውሮፓ ትልቁ የኒውክሌር ተቋም ለማቀዝቀዝ የሚልከውን ውኃ መጠን አሳንሷል፡፡ እንደ ክሪሚያ ላሉ የሩሲያ ግዛቶችም የሚያመነጨውን የመጠጥ ውኃ ቀንሷል፡፡

ዘ ጋርዲያን፣ ቢቢሲ፣ አልጀዚራ እና ሌሎች የመገናኛ ብዙሀን ዘገባዎች እንደሚያሳዩት የግድቡ መደርመስ ዓለም አቀፍ ቁጣ ጭምር ቀስቅሷል፡፡ ከትላልቆቹ የአውሮፓ ሀገራት መካከል በተለይ እንግሊዝ ጉዳት አድራሹን ሀገር ከመግለጽ ተቆጥባለች። አሜሪካም እንደ ሌሎች ጊዜያት በሩሲያ ላይ ጣቷን መቀሰር አልፈለገችም፡፡

ፈረንሳይ ግን ግድቡን እንደገና ለመጠገን የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ለማዋጣት ዝግጁነቷን አሳይታለች፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸኃፊ በበኩላቸው ጦርነት በሰው ላይ ከሚያስከትለው ውድመት ጋር አያይዘው አውግዘውታል፡፡

በተሰበረው የግድቡ ክፍል በኩል ለዓመታት አምቆ የያዘውን ኩልል ያለ ውኃ ለቆ ያጎረፈው በፎቶ የታየው የካክሆቭካ አካል ቀደም ብሎ በሩሲያ ወታደሮች እጅ በነበረችና በቅርቡ ዩክሬናዊያን ኃይሎች መዳፍ ላይ ዳግም በወደቀችው ከርሰን ከተማ በስተ ምሥራቅ ይገኛል፡፡ እስከ ሦስት ኪሎ ሜትር የሚደርስ ርዝማኔም አለው፡፡

እስከ 30 ሜትር ከፍታ ድረስ ውኃ መያዝ ይችላል ተብሎ የተነገረለት ግድብ 18 ኪየብክ ኪሎ ሜትር ውኃ መያዝ የሚችልና በደቡባዊ ዩክሬን የሚገኝ ነበር፡፡ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት አስቀድሞ በሶቪዬት ወታደሮች ጉዳት የደረሰበት ሲሆን ቀጥሎ ደግሞ አካባቢውን እየሸሹ በነበሩ የናዚ ጀርመን ወታደሮችም ጉዳት ደርሶባቸዋል ተብሏል፡፡

የጦርነት እሳቶች ተደጋግሞ የወደቀበት ይህ ግድብ አሁን የሞት፣ መፈናቀልና ውድመት ማዕከል ሆኗል፡፡ ብዙ ሰዎችና እንስሳትን ለጉዳት ሲዳርግ የነበሩ የእርሻ መሬቶችን በማጠብ አካባቢውን መላጣ አድርጎታል፡፡ በአካባቢው ተቀብረው የነበሩ ፈንጂዎችን ከቦታ ወደ ቦታ ማጓጓዙም በሥጋት ላይ ሌላ ሥጋትንም ደቅኗል፡፡

አሁን በአካባቢው እየተደረገ ያለውን ከባድ ጦርነት ከወሰድንም ግድቡን ጠግኖ ዳግም ለአገልግሎት የማዋል ተስፋዎችን ያጨልማል፡፡ ምክንያቱም አንደኛው ተፋላሚ የሌላውን ስም እየጠሩ የህይወት አድን ሥራዎችን አደናቅፎብኛል የሚሉ ስሞታዎችንም እያወረወረ ስለሆነ፡፡

የግጭቱ አድማስ እየሰፋ ከመሆኑ ጋር ተያይዞም አስጊ ሁኔታ አለ —ምክንያቱም ዩክሬን በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ የመልሶ ማጥቃት እርምጃ ስትወስድ ሩሲያ ደግሞ ይህንን ጥቃት ለማክሸፍና ጠላቴ የምትላትን የዩክሬንን ግሥጋሴ ለመግታት ስትል አይታ፤ፉም ያለቻቸውን እንቅፋቶችን እየደቀነች እንደመሆኗ፡፡

ስለሆነም የወደመውን ግዙፍ የውሃ ማዘያ ጀርባ ከነአንቀልባው ለመጠገንና በአካባቢው ዘላቂ ልማትን ለማምጣት ግጭቶች በሠላማዊ መንገድ እልባት ማግኘት ይኖርባቸዋል፡፡ ምንም እንኳን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር ይህንን ማሰብ አስቸጋሪ ቢሆንም፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ በተለይ ቱርክና ደቡብ አፍሪካ ሰሞኑን ያቀረቡት የሠላም ሀሳብ ተስፋ ቢያጭርም ያለውን ሂደት መቀየር ስለመቻሉ አጠራጣሪ ነገሮችም አሉ፡፡

በተለይ ከ10 የአፍሪካ ሀገራት በተውጣጣ የሠላም ልዑክ አማካይነት የማሸማገል ሥራዎች ለመጀመር የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማ ፎሳ ላደረጉት ጥሪ የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቪላድሚር ፑቲን አዎንታዊ ምላሽ ቢሰጡም ጦርነቱ ተባብሶ ከመቀጠሉ ጋር ተያይዞ ተስፋውን አመናምኖታል፡፡

በተጨማሪም አካባቢያዊና ዓለም አቀፋዊ ችግሮችም ሠላም ለመፍጠር በሚደረጉ ጥረቶች መስመር እንዲይዙ ከወዲሁ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል፡፡