ሎቱሩሲ ካሬ

በተመስገን አበራ (ከጂንካ ቅርንጫፍ)

“ስሜ ሎቱሩሲ ካሬ ይባላል፡፡ 1981 ዓ.ም ነው በደቡብ ኦሞ ዞን ካንጋቴ ከተማ የተወለድኩት፡፡ ከ1 እስከ 6ኛ ክፍል በኪቢሽ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት፡፡ ከ7 እስከ 8ኛ ክፍል ኩራዝ መለስተኛና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምሬያለሁ፡፡ ከ9ኛ እስከ 10ኛ ጂንካ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው የተማርኩት ዲፕሎማ አለኝ-በኮፐሬቲቭ አካውንቲንግ ሙያ፡፡ ዲፕሎማውን የወሰድኩት ከአርዳይታ ግብርና ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኮሌጅ ነው፡፡ በኢኮኖሚክስ ከሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ድግሪዬን ተቀብያለሁ።

ሁለተኛ ዲግሪዬን ደግሞ በDevelopment Communication & Media Studies ከአፍርካ የአመራር ልዕቀት አካዳሚ አግኝቻለሁ፡፡ ከልጅነቴ ጀምሮ ኳስ መጫወት በጣም እወዳለሁ፤ እጫወታለሁ። ለብዙ አመታት ወረዳ፣ ደቡብ ኦሞ ዞንን እንዲሁም ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲን ወክዬ ተጫውቻለሁ።

“ነገር ግን እንጀራ ሊሆነኝ አልቻለም፡፡ በዚህም በሙያዬና በአመራርነት ለማገልገል ወስኜ ለስፖርት ያለኝን ትኩረት ገደብኩ፡፡

“ራሴን ከስፖርቱ ከገደብኩ ወዲህ ከወረዳ እስከ ዞን በከፍተኛ የፓርቲና የመንግስት ሀላፊነቶች ላይ ስሰራ ቆይቻለሁ፡፡ በኋላም የመንግስትን ስራ ላለመበደል ወደ ቤተሰብ ቀረብ ብዬ ለመስራት ወሰንኩ፡፡ ስልጣኑን ለቂቄ ወደ ወረዳ ተመለስኩኝ።

“የኛንጋቶም ወረዳ ውስጥ ከማከናውነው የልማት ማህበር ፅ/ቤት ስራ ጎን ለጎን እንጀራ ሳይሆነኝ የቀረውን ስፖርት እንደገና ማተኮር አለብኝ ብዬ ያመለጠኝን ዕድል ለመመለስ በታዳጊ ወጣቶች ላይ መስራት ጀመርኩኝ።

“በስፖርቱ የማደግ ህልሜ ተጨዋች ሆኜ ባይሳካልኝም ወጣቶች ላይ በመስራት በክልልና በሀገር እንዲሁም በአለም ደረጃ ተወዳዳሪና ኩራት የሚሆኑ ስፖርተኞችን የመፍጠር ጊዜው አልረፈደም ነበር።

“ይህንን ህልሜን በማሳካት ሂደት ብዙ ተፅዕኖዎች እንደሚኖሩና እንደሚገጥሙኝ አስቀድሜ አውቅ ነበር። ብዙ ተፅዕኖም ገጥሞኝ መጥቻለሁ። ከተጫዋቾቼ፣ ከወረዳ አመራሮቹ፣ ከተወሰኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ሁሉ ጎታች አስተሳሰቦች ይሰነዘሩብኝ ነበር። በስፖርቱ ይዤ የተነሳኋቸውን ልጆቼን (ስፖርተኞቼን) ሀገርን እስከማስጠራት፣ እንዲሁም እንጀራ እንዲሆናቸው እስከማድረስ የመስራት ትልቅ ህልሜ በተለያዩ ንፋሶች መደናቀፍ አልነበረበትም፡፡ በቡድኔ የጀመርኩት ስራ በዞናዊና በክልል አቀፍ ክለቦች ሻምፒዮና እስከመሆን አደረሰኝ።

“የተወለድኩበት ማህበረሰብ ለኬንያና ለደቡብ ሱዳን አጎራባች ማህበረሰብ ነው። ከአጎራባችነቱ ባለፈ ኬንያ ከሚኖረው ቱሩካና፣ ደቡብ ሱዳን ከሚኖረው ቶፖሳ እንዲሁም ዩጋንዳ ከሚኖረው ካራሞጆ ማህበረሰብ ጋር የጠነከረ ማህበራዊ ትስስር አለው፡፡

“የታሪክ ሙሁራን እንደሚገልፁት በሰው ሰራሽ የድንበር ከለላ እንዲለያዩ የተደረጉ ነገር ግን በሁሉም ባህል፣ ቋንቋና ሌሎች ማህበራዊ መስተጋብሮች አንድ ማህበረሰብ እንደሆኑ ነው፡፡

“ይህ ማህበራዊ መስተጋብር በድንበር አካባቢዎች በነበሩ ግጭቶች ለረዥም ጊዜ ዝግ የነበረ ቢሆንም የወረዳው አመራሮችና ማህበረሰቡ በከፈሉት ዋጋ ለሦስት ተከታታይ አመታት አንፃራዊ ሰላም መፈጠሩን ተከትሎ የተለያዩ ስፖርታዊ ውድድሮች ይካሄዳሉ። በዚህ አመት በኛንጋቶም አዘጋጅነት በተካሄደው የኤኩሞሞር ክብረ በዓል ላይ ከኬንያና ከኢትዮጵያ በተውጣጡ ክለቦች መካከል የእግር ኳስ ውድድር ተደርጎ አሸናፊ በመሆን ዋንጫ አንስተናል።

“እንደዚያ አይነት ትስስሮች ለቀጠናው ሰላም ትልቅ ሚና አላቸው፡፡ ስፖርት ለጤንነት ከሚለው መርሆ ባሻገር ለሰላሙም ተመራጭ መሳሪያ ነው፡፡

“ታዳጊ ወጣቶች ላይ ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ በጎና መልካም ነገር በመዝራት ከራሳቸው አልፈው ለሀገር መልካም ፍሬ የሚሰጡ እንዲሆኑ መምከር፣ ማስተማርና በጎ ተፅዕኖ የመፍጠር ፍላጎት አለኝ።

“አሁን በጀመርኩት መንገድ በስፖርቱ ለሀገር አቀፍ ሻምፒዮና የሚወዳደረውን ቡድን በመልካም ስነ ምግባር በመቅረፅ ለብሔራዊ ሊግ ከፍ እንዲሉ ማድረግ። በታዳጊዎች ላይ ተመልሼ መስራት የቅርብ ጊዜ ፍላጎቴ ነው።

“ሰው ሆነን ስንፈጠር አንዳችን ለሌላችን መኖር ትልቅ ቦታ አለን። የሚሳሳተው ሁሉን ነገር ከራሳችን፣ ከቡድናችን፣ ከብሔራችን… ወዘተ ጥቅም ጋር ብቻ በማሰብ መስራት የጀመርን ቀን ነው። የማስተላልፈው የመጀመሪያ መልዕክቴ በእኛ እንዲሆን የማንፈልገውን ነገር በሌሎች ሰዎች ላይ ሲሆን መደሰት የለብንም።

“አንዳንዴ ዝንባሌያችንና ትኩረታችንን በአንድ ነገር ላይ ብቻ እያደረግን ስኬት ላይ ሳንደርስ እንቀራለን። የሚገጥሙን ፈተናዎች የሚመስሉ ነገሮች ሲያጋጥሙን ከአዲሱ አካባቢው ጋር በመላመድ፣ ችግሮችም ለበጎ መምጣታቸውን በማሰብ ወደ አዲስ ስኬት በመቀየር ለስኬት መብቃት እንደሚቻል እኔ ምስክር ነኝ፡፡ ይህን ፈጥኖ አድስ ነገርን የመላመድ ባህል የሚለው ሀሳብ መሰናበቻ መልእክቴ ነው”