ድርጅቱ ፈርሷል፣ ችግሩ ግን ሰፍቷል

ድርጅቱ ፈርሷል፣ ችግሩ ግን ሰፍቷል

በደረሰ አስፋው

የበለፀጉ ሀገራት ወባና ሌሎች ተላላፊ የጤና ጠንቆችን በመቆጣጠር የኑሮ ደረጃቸውን አሻሽለዋል፡፡ የአፍሪካ ሀገራት ግን ካሉባቸው የድህነት ጫናዎች በተጨማሪ ለበርካታ ተላላፊ በሽታዎች የተጋለጡ ናቸው፡፡ በታዳጊ ሀገራት ከሚገኙ የጤና ጠንቆች መካከል የወባ በሽታ ደግሞ በግንባር ቀደምትነት ይነሳል፡፡

40 በመቶ የሚሆነው የዓለም ህዝብ ለወባ በሽታ የተጋለጠ ነው፡፡ 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን የሚሆነው ህዝብ በየዓመቱ በወባ በሽታ ምክንያት ይሞታል፡፡ በእያንዳንዱ ሰኮንድ 10 ሰዎች በወባ በሽታ እንደሚያዙም መረጃው ይጠቁማል፡፡ በበሽታው ህይወታቸውን ከሚያጡት ሰዎች መካከልም 90 በመቶ የሚሆኑት የሚኖሩት በአፍሪካ ውስጥ ነው። ጠና አበረ በኢትዮጵያ የወባ በሽታ ታሪካዊ ሂደቶች በሚለው ተከታታይ ዕትም ቁጥር 2 ላይ እንደተመላከተው፡፡

አፍሪካ በየዓመቱ በወባ በሽታ እስከ 400 ሺህ ሞቶችን የሚቆጠሩባት ሲሆን አብዛኞቹ ደግሞ እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ነው። ነፍሰጡር እናቶችና በእድሜ የገፉ አዛውንቶችም ተከታዩን ቁጥር ይሸፍናሉ። ይህ የጥናት ውጤት ‘በኒው ኢንግላንድ ጆርናል ኦፍ ሜድሲን’ የህክምና መጽሔት ላይ የታተመ ነው፡፡ ወባ አሁንም ከሳህራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት ዋነኛ የጤናና የማህበራዊ እድገት ችግር ሆኖ እንደቀጠለ ነው። በአፍሪካ በወባ በሽታ ስርጭት መስፋፋት ተለይተው የሚታወቁት ኢትዮጵያ፣ ናይጄሪያ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ታንዛንያና ኬንያ ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ የወባ በሽታ የጤና፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ችግር ክፍተት ሆኖ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ የችግሩ መንስኤ በውል ባልታወቀበት ጊዜ የኢንፍሎዌንዛ፣ የወረርሽኝ በሽታ እየተባለም ለብዙ ሰዎች ህልፈት ምክንያት ሆኗል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ በሳይንስ የተደገፈ የወባ በሽታ የምርምር ጥናት የተጀመረው ከ1929 እስከ 1934 ዓ.ም በኢጣሊያ ወረራ ወቅት ነው፡፡ በጥናቱም በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በወባ በሽታ ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለህመም፥ በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩም ሞት ምክንያት ሆነ፡፡ ይህ አሰቃቂ አደጋ ደግሞ በኢትዮጵያ የወባ ማጥፊያ ድርጅት እንዲቋቋም አስገደደ፡፡

የወባ ማጥፊያ ድርጅት በ1951 ሲቋቋም የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት ቀዳማዊ ኃይለስላሴ አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነበር፡፡ በእሳቸው ትዕዛዝ እራሱን ችሎ የተቋቋመው የብሄራዊ የወባ ማጥፊያ ድርጅት በግብአትም ይሁን በሰው ሀይል የተደራጀ ነበር፡፡ የድርጅቱ መቋቋም ወባን ከሀገሪቱ ለማጥፋት በተደረገው ጥረት ያበረከተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነበር፡፡ የብዙ ኢትዮጵያዊያንን ሞትና ስቃይ በማስቀረት የሀገር ባለውለታ እንደነበርም በብዙዎች ዛሬም ይታወሳል፡፡

ዛሬም ቢሆን ይህ በሽታ የጤናና ማህበራዊ ችግር እንደሆነ ቀጥሏል፡፡ በቅርቡ በተደረገ አንድ አውደ ጥናት ላይ እንደተጠቆመው ለተመላላሽ ህክምና ወደ ጤና ድርጅት ከሚሄዱት ህሙማን መካከል 16 በመቶ የሚሆኑት የወባ በሽተኞች ናቸው። ሆስፒታል ተገኝተው ከሚታከሙት ህመምተኞች መካከል 22 በመቶ የሚሆኑትም የሚሞቱት በወባ በሽታ ምክንያት እንደሆነ በጥናቱ ላይ ተገልጿል፡፡

ይሁንና የኢትዮጵያ የወባ ማጥፊያ ድርጅት ባልታወቀ መንገድ እንዲፈርስ ተደርጓል፡፡ ወባም የሀገሪቷ ግንባር ቀደም ገዳይ እንደሆነ ቀጥሏል፡፡ በዚህ ተቋም ውስጥ ተቀጥረው ለ39 ዓመታት አገልግለው ጡረታ ከወጡ አንድ ሰው ጋር ቆይታ አድርገን ነበር። ስለድርጅት አመሰራረት፣ ተግባር፣ ለምን እንደፈረሰ እና የድርጅቱ መፍረስ ያመጣው ተጽእኖስ ምንድነው? ስንል ሰፋ ያለ ጊዜ ወስደን ውይይት አደረግን፡፡

አቶ ግርማ ገብራይ በሆሳዕና ከተማ ተወልደው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በሻሸመኔ በአጼ ናኦድ ትምህርት ቤት ተምረዋል፡፡ ከ11ኛ ክፍል በኋላ ግን ትምህርታቸውን አቋርጠው ወባ ማጥፊያ ድርጅት ውስጥ ተቀጠሩ። ለስራቸው እንዲያገለግላቸው በናዝሬት የወባ ማጥፊያ ድርጅት ማሰልጠኛ በደም ጥናት ቴክኒሺያንነት ለ6 ወር ሰልጥነዋል፡፡ ከ1959 ዓ.ም ጀምሮ ጡረታ እስከወጡበት ድረስ በወባ ማጥፊያ ድርጅት በደም ምርመራ ቴክኒሺያንነት፣ በሱፐርቫይዘርነት እና በአሰልጠኝነት ህዝብንና ለማገልገል ያልረገጡት የኢትዮጵያ ምድር የለም፡፡

በ1950 ዓ.ም በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ የወባ ወረርሽኝ ተከስቶ 3 ሚሊዮን ህዝብ ለህመም 150 ሺህ ህዝብ ለህልፈተ ህይወት መዳረጉን የዓለም የጤና ድርጅት ይፋ ስለማድረጉም ያስታውሳሉ፡፡ ችግሩ በወቅቱ በነበሩት የሀገሪቱ መሪ ቀዳማዊ አጼ ኃይለስላሴ ላይም ድንጋጤን ፈጥሮ ነበር። በዚህ ምክንያት ከዓለም የጤና ድርጅት ጋር በመመካከር በናዝሬት የነበራቸውን ቤተ-መንግስት ወደ ማሰልጠኛነት ቀይረው የወባ ማጥፊያ ድርጅት ተቋቁሞ ስልጠናው እንደተጀመረ አቶ ግርማ ይናገራሉ፡፡

የወባ ማጥፊያ ድርጅት በተቋቋመበት ጊዜ 70 በመቶ የሚሆነው የሀገሪቱ የቆዳ ስፋት ወባማ እንደነበር ነው መረጃውን የሰጡን አቶ ግርማ የሚጠቁሙት፡፡ በወቅቱ 50 በመቶ የሚሆነው ህዝብ ለወባ በሽታ የተጋለጠ እንደነበርም ተናግረዋል፡፡ የበሽታው አሳሳቢነት በንጉሱ ዘንድ ትኩረት እንዲያገኝ ያደረገውም ይሄው ምክንያት ነበር፡፡ የብሄራዊ የወባ ማጥፊያ ድርጅት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት በ1951 ዓ.ም ናዝሬት ላይ ሊከፈት ችሏል።

ማሰልጠኛው በመስኩ የሰለጠነ የሰው ሀይል ለማፍራት አግዟል፡፡ ትምህርት ቤቱ ወባን ብቻ መሰረት አድርጎ በአራት የስልጠና መስኮች ማለትም በደም ጥናት፣ ካርታና ርጭት፣ በትንኝ ጥናትና የጤና ትምህርት ባለሙያዎችን በብቃት በማሰልጠን ወባን ለማጥፋት በትኩረት ይሰራ እንደነበር ነው የተናገሩት፡፡

ከየትምህርት ቤቱ የተሻለ ውጤት ያላቸው ተማሪዎች እየተመረጡ ስልጠናውን በአራቱ የትምህርት ዘርፎች ይወስዱ እንደነበርም ነው የገለፁት፡፡ በዚህም አቶ ግርማ በማሰልጠኛው ገብተው እንዲሰለጥኑ ዕድሉን ካገኙት መካከል አንዱ ሊሆኑ ቻሉ፡፡ ወባን ለማጥፋት የተሰራው መዋቅራዊ አደረጃጀትና የሰለጠነ የሰው ሀይል በማፍራቱ ያስገኘው ለውጥ አመርቂ ነበር ሲሉ ከዛሬ 39 ዓመታት በፊት የተሰራውን እና የተገኘውን ለውጥ ያብራሩት፡፡

ከ1970ዎቹ ወዲህ ግን ማሰልጠኛ ተቋሙ ባለሙያዎችን ማሰልጠን አቋረጠ፡፡ ወባን ብቻ ለማጥፋት ተብሎ የሰለጠነው የሰው ሀይል እንደዋዛ ተበተነ፡፡ የጠለቀ እውቀት፣ ልምድና ምርምር ያደረጉ ከፍተኛ ባለሙያዎች ዕውቀትም መና ቀረ፡፡ ወባን ለማጥፋት የሚደረገው ጥረትም መሰናከል ገጠመው፡፡ እሰከ ደርግ መውደቅ ድረስ ተጠናክሮ ይሰራ የነበረው የወባ መቆጣጠርና መከላከል ስራ በኢህአዴግ ዘመን ደግሞ ጭራሽ ተዘነጋ፡፡ በአንጻሩ ግን የወባ በሽታ የበርካቶችን ህይወት መቅጠፉን ቀጠለ፡፡

በየጊዜው በተደረጉ መዋቅራዊ ለውጦች የበሽታው የጤና፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ቀውስ ከግምት ውስጥ ሳይገባ ከሌሎች የጤና አገልግሎቶች ጋር በውህደት እንዲንቀሳቀስ ተደርጓል፡፡ የተደረገው ድርጅታዊ ውህደት ግን አካላዊ እንጂ ተግባራዊ ባለመደረጉ የድርጅቱን መዋቅር፣ የሰው ሀይልና የንብረት ምንጮችን አዳከመ ይላሉ አቶ ግርማ፡፡ የወባ በሽታ ቁጥጥር ዘርፈ ብዙና የባለሙያ ድጋፍ የሚጠይቅ በመሆኑ ይህ ባልተሟላበት ሁኔታ አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ ሳይችል ቀርቷልም ነው የሚሉት፡፡

የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በቅርቡ ባወጣው መረጃ ካለፈው ዓመት ሐምሌ እስከ ህዳር ወር 2014 ዓ.ም በወባ በሽታ ተጠረጥረው ምርመራ ከተደረገላቸው 6 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሰዎች ውስጥ፤ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት በሽታው እንደተገኘባቸው ማስታወቁ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ የተገለፀው የችግሩ መጠን ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸርም 10 በመቶ መጨመሩን የሚያሳይ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስፋፋ በመጣው የወባ በሽታ የደቡብ ክልል ደግሞ በቀዳሚነት ተጠቅሷል።

የጤና ሚንስቴር በ2009 ዓ.ም ወባን ለመቆጣጠርና ለመከላከል እንዲረዳ የነደፈው ስትራቴጂ በተወሰነ ደረጃ ውጤታማ መሆን የጀመረ መስሎ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በአብዛኞቹ ክልሎች የወባ በሽታ ሥርጭት እየሠፋና በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥርም እየጨመረ እንደሚገኝ ከየክልሎቹ የሚወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የሀገራችን መልከዓምድር እና የአየር ፀባይ ሁኔታ ለወባ ትንኝ መራባት ምቹ በመሆኑ 75 በመቶ የሚሆኑት አካባቢዎች ለወባ በሽታ ስርጭት አመቺ ሲሆኑ 60 በመቶ የሚሆነውን ህዝብም የበሽታው ተጋላጭ አድርጎታል፡፡

ለችግሮቹ ሁነኛ መፍትሄው የቀድሞ የወባ ማጥፊያ ድርጅት መልሶ መቋቋም እንደሆነም አበክረው ይናገራሉ አቶ ግርማ፡፡ ወባ የሌሎች ተቋማት ተለጣፊ መሆኑንም ይኮንናሉ። እሳቸው በዚህ ተቋም ውስጥ በሚሰሩበት ጊዜ ሁነኛ ለውጥ ታይቶ እንደነበር በመጠቆም። የወባ መከላከልና ቁጥጥር የሰርክ የመስክ ጥናት ክትትል የሚያስፈልገው እንጂ ወቅት ጠብቆ በሚሰራው የዘመቻ ስራ ብቻ መቆጣጠር አይቻልም ሲሉም ይከራከራሉ፡፡

መንግስት በጤናው ዘርፍ በምዕተ ዓመቱ አሳካቸዋለሁ ብሎ ከተነሳባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ወባን መከላከልና የመቆጣጠር ተግባር ነው፡፡ ይሁን እንጂ የአለም ጤና ድርጅት በበኩሉ፤ ሀገሪቱ የወባ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በቂ ጥረት ባለመደረጉ አሁንም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በወባ በሽታ እየተያዙ እንደሚሞቱ ጠቁሟል፡፡

በሽታው ታይቶባቸው በማያውቁ አካባቢዎች ሳይቀር መታየቱንና ወባ የጠፋባቸው ቦታዎችም እንደገና ማገርሸቱንም ጭምር ነው አቶ ግርማ የሚያስረዱት፡፡ ሰፈራ፣ የህዝብ ቁጥር መጨመር፣ ፍልሰትና የአካባቢ መራቆትና ሌሎች ተዛማች ችግሮች ለስርጭቱ መስፋፋት ምክንያቶች እንደሆኑ ጠቅሰዋል። የልማት ስራዎች ለሀገር ጠቀሚ ሆነው ሳለ የወባ መከላከልና ቁጥጥርም ስራውም በተጓዳኝ አለመከናወኑ በወረርሽኝ መልክ ጉዳት እያሳደረ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

የወባ በሽታ ስርጭት ለመከላከል የበሽታ አስተላላፊ ትንኞችን ባህሪ በአግባቡ ማወቅ ይገባል፡፡ በቀድሞው የወባ ማጥፊያ ድርጅት ስልጠናውን ከሚወስደው ሃይል መካከል የትንኞቹን ባህሪ ለይቶ ጥናት የሚያካሂደው ዘርፍ አንደኛው ነበር፡፡ ድርጅቱ ባልፈረሰ ጊዜ ባህሪያቸውን ማወቅ፣ መተንተን፣ በሽታውን መከላከልና ማጥፋት ላይ ትኩረት ተደርጎ ይሰራ ነበር። በዚህም የወባ ማጥፊያ ድርጅት መቋቋም ሁነኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ማዕከሉ በአፍሪካ ቀንድ ጠንካራ የወባ ምርምርና የስልጠና ማዕከል በመባልም ይታወቅ እንደነበር ነው ያነሱት፡፡

እ.አ.አ በ2030 የወባ በሽታን ከሀገራችን ለማጥፋት ግብ ስለመጣሉ የጠቆሙት አቶ ግርማ ግቡን ለማሳካት ግን ከፍተኛ ጥረት መደረግ አለበት ባይ ናቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ ዓለም አቀፍ የዘርፉ ተቋማትና ባለድርሻ አካላት ትብብርና ርብርብ ወሳኝ ነው ብለዋል። በተለይ እራሱን የቻለ የሰለጠነ የሰው ሀይል፣ የምርምር ላብራቶሪዎችን ማስፋፋትና በግብአት የተደራጀ ተቋም መመስረት ቀን የሚሰጠው አለመሆኑን አበክረው ይገልጻሉ።

የሀገሪቷን አንገብጋቢ ችግር እየቀረፈ የነበረው ግዙፉ ተቋም መፍረስ ችግሩን አሰፋው እንጂ አልቀነሰውም፡፡ የድርጅቱ መፍረስ ጎልቶ የታየው በኢህአዴግ የአመራርነት ዘመን ቢሆንም በደርግ ዘመን ማሰልጠኛ ተቋሙን የኢሰፓ ማሰልጠኛ ሲሆን ነው ወባን ከሀገሪቱ ለማጥፋት የሚደረገው ጥረት ላይ ጥላ ማጥላት የጀመረው፡፡

በደርግ ዘመን ዘመናዊ የተባሉ መሳሪያዎችም ባከኑ፡፡ ምርምርና ጥናት የሚደረግበት ቦታ እንዲሁ እንደዋዛ ጠፋ፡፡ ይህም በጤናው ዘርፍ የነበረው አስተዋጽኦ ከቁብ ሳይቆጠር መና ቀረ፡፡ በዚህም መዋቅራዊ ለውጥ ተደረገ። በ1972 ዓ.ም የኢትዮጵያ የወባ ማጥፊያ ድርጅት ከጤና ሚኒስቴር ጋር እንዲዋሃድ ተደረገ፡፡

ድርጅቱ ከመፍረሱ በፊት ከፍተኛ ድጋፍ ነበረው፡፡ የወባ ማጥፊያ ድርጅት ምርመራውና የምርመራው ውጤትም ትኩረት ማግኘቱ ብቻ አልነበረም፡፡ የደም ናሙናው እስከ ጤና ሚኒስቴር ድረስ ሄዶ ድጋሜ የምርመራው ውጤት ይረጋገጥ ነበር፡፡

ማሰልጠኛው ከሀገር ባለፈ የአፍሪካ እና የሌሎች ሀገራት የህክምና ባለሙያዎች ጭምር የሚሰለጥኑበት ቦታም ነበር፡፡ በተግባር የተደገፈ ጥናትና ምርምርም ይካሄድበት ነበር። የሀገሪቷን ወባማ አካባቢዎች በ6 አብይ ጣቢያያዎች ወይም ዞን ማዕከል የተዋቀረው የወባ ማጥፊያ ድርጅት ከርጭቱ በተጨማሪ የምርመራ፣ የመድሃኒት እደላና የጤና ትምህርት አብሮ በመስጠት የተለየ ትኩረትና ድጋፍ ነበረው፡፡ ቤት ለቤት ሳይቀር በተመረጡ ወባማ አካባቢዎች ባለሙያዎች በበሽታው አስተላላፊ ትንኞች ላይ ጥናት ያደርጉ ነበር። ናሙና ይወስዳሉ፡፡ የጥናታቸውንም ትንተና ያቀርቡ ነበር፡፡ ከሁሉም የሚልቀው ደግሞ የትንኝ እርባታ ጭምር ነበር፡፡ ይህም ወባን ለማጥፋት ለሚደረገው ምርምርና ጥናት አስተዋጽኦው የጎላ እንደነበር ነው የተናገሩት።

የቀድሞ የወባ ማጥፊያ ድርጅትን ንጉሱ በ1951 ከዓለም የጤና ድርጅት ጋር ምክክር አድርገው ማቋቋማቸው እንዲሁ በዋዛ አልነበረም፡፡ የወባ በሽታ ገዳይነትና መስፋፋት ስለተገነዘቡ እንጂ፡፡ አሁንም ችግሩ ሰፋ እንጂ አልተገታም፡፡ መላ ሊበጅለት ይገባል፡፡ ከሌሎች ተቋማት ተለጣፊነት በማውጣት በግብአት፣ በስልጠናና በሰው ሀይል በማደራጀት ስራውን በሀላፊነት ሊሰራ የሚችል ተቋም መልሶ ማቋቋም ያስፈልጋል፡፡

ኢትዮጵያ የወባ በሽታን ለመከላከልና ለማጥፋት የያዘችው ግብ እንዲሳካ የምርምር ቴክኖሎጂን ማስፋት አስፈላጊ ነው፡፡ ጥራት ያላቸው የምርምር ግብዓቶችን ጨምሮ የጤና ባለሙያዎች አቅም ማብቃትም በተመሳሳይ። ህብረተሰቡ በሽታውን በራሱ እንዲከላከል ግንዛቤ ማዳበር ላይ ድጋፍ ማድረጉንም መዘንጋት የለበትም ሲሉ ያሳስባሉ፡፡

ይህ ሁሉ ሲሆን ታዲያ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አዳጊ ሃገራት ውስጥ የሚቋቋሙ ጠቃሚ ተቋማት ለምን ይፈርሳሉ ብሎ መጠየቅ ተገቢ ይሆናል፡፡ የበሽታው ስርጭት እየሰፋ ገዳይ መሆኑ ለተመሰከረለት ለዚህ ጠንቅ ወረርሽኝ ስለምን በዘርፍ የሰለጠነ ባለሙያዎችን ያውም በአሁኑ ጊዜ ማፍራት ተሳነን? የዚህና መሰል የሰለጠኑ የሙያ ማህበራት ዝምታችሁ ስለምን በረታ ? የጤና ስልጠና ዘርፎች እየተስፋፋ ባለበት በዚህ ወቅት የወባ ወረርሽኝ ጉዳይን በተመለከተ ለቁጥር የሚታክቱ የጤና ተቋማቶቻችንና የታሪክ ሰዎችን ምን ይላሉ? በቀጣይ በክፍል ሁለት የምንመለስበት ይሆናል፡፡