ስደተኞችን በመከላከሉ ላይ ትኩረት ያደረገው ትብብር

በፈረኦን ደበበ

በዓለም መግታት ካልተቻሉ ማህበራዊ ቀውሶች አንዱ ነው ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር፡፡ መነሻውን በብዙ አካባቢዎች ይደረጋል፡፡ የተሻለ ህይወት ማስገኘት ይችላሉ ወደሚባሉ ሀገራት ያልማል፡፡ በእንዲህ አስተዳደርና ሌሎች አገልግሎቶችንም ያወሳስባል፡፡

ባህሪው ከአንድ የዓለም ክፍል ተነስቶ በግለሰብ ደረጃ ከሚደረጉ ጉዞዎች በህብረት ወደ ሌሎች ሀገራት የሚደረግን ግስጋሴ የሚያካትት ሲሆን የሂደቱ መደጋገም በተቀባይ ሀገራት ላይ ጫና አሳርፏል፡፡ በተለይ እያሳለፍን ባለነው ዓመት እንደተመለከትነው ከተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ችግሮች ጋርም ተገጣጥሟል፡፡

መዳረሻውን አውሮፓና አሜሪካ እያደረገ ያለው ጉዞ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ከፍተኛ ተቃውሞ ነው በተቀባይ ሀገራት ውስጥ እያስነሳ የሚገኘው፡፡ በዚህ ህግ ከማውጣት ጀምሮ በርካታ የመከላከያ እርምጃዎችንም እየወሰዱ ይገኛሉ፡፡ ወደ ሀገሮቻቸው እንዳይገቡ መንገድ ከመዝጋት አልፎ ከገቡ በኋላ አገልግሎት እስከ መከልከልም ተዳርሷል፡፡ ይህ ሁሉ ግን በጉዞ ላይ ከሚደርሱ አደጋዎች ተርፈው በህይወት በሚገቡት ላይ መሆኑ አሳዛኝ ያደርገዋል፡፡

በተቀባይ ሀገራት የሚነሱ ፖለቲካዊ ተቃውሞዎችን መነሻ በማድረግ በተለይ በአሜሪካ ወደ ድንበር መመለስ፣ በእንግሊዝ ወደ ሌላ ሀገር አዛውሮ ማስፈር፣ በካናዳ “ከአሁን ወዲያ አትምጡብን” የማለት ውሳኔና እንዲሁም አሁን በአውሮፓ ህብረት በኩል በሰሜን አፍሪካ ማቋቋሚያ የማድረግ እሳቤዎች በተቀባይ ሀገራት የሚወሰዱ እርምጃዎችን ያሳያል፡፡

ሰሞኑን የአውሮፓ ህብረት ከቱኒዚያ መንግሥት ጋር የደረሰው የትብብር ስምምነት የዚህ እሳቤ አንድ ማሳያ ነው፡፡ የአውሮፓ ህበረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ኡርሱላ ቮን ደር ለየን፣ የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጂወርጂያ ሜሎኒ እና የኒዘርላንድስ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ሩቴ በቱኒዚያ ሰፊ ውይይት አድርገዋል፡፡

“ስደትን በተመለከተ የአውሮፓ ህብረት ትብብርን ለማጠናከር ፈልጓል” በሚል ርዕስ አፍሪካ ኒውስ የተባለው የዜና ምንጭ ሲዘግብ ከማን ጋር እንደተገናኙና በምን በምን ጉዳዮች እንደተወያዩም ገልጿል፡፡ ችግሩን መቋቋም እንድትችል ለሀገሪቱ የተለያዩ ድጋፎችን ለማድረግ መስማማታቸውንም አስታውቋል።

በሳምንቱ አጋማሽ በተገናኙበት አጋጣሚ ለሀገሪቱ ከ1 ቢሊዮን የሚበልጥ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግና በባህር ውስጥ የሚዘረጋ የመረጃ ማቀባበያ መሥመር ለመገንባትና እንዲሁም ታዳሽ ኃይል ለመገንባት ተስማምተዋል፡፡

በሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር የሚታየውን የምጣኔ ሀብት መዋዠቅ ማስቀረት ያስችላል የተባለለትን ውይይት ያዘጋጁት የተቀባይዋ ሀገር መሪ ከይስ ሰይድ ሲሆኑ እንግዶቹ የሚፈልጉትን ዓላማ ለማሳካት ቁልፍ ሰው ተብለውም ነው የታዩት፡፡

የሀገሪቱ ሌላ ገጽታ በቅርቡ ከተለያዩ ከሰሀራ በታች ካሉ ሀገራት ስደተኞች ጋር የገቡበት ውዝግብ ሲሆን ውይይቱ ልማትና የምጣኔ ሀብት መረጋጋትን በማምጣት ፍጥጫዎችን ለማብረድ እንደሚረዳም ተገልጿል፡፡

ውይይቱ በሚጀምርበት ዋዜማ ላይ ፕሬዝዳንት ሰይድ ስፋክስ በተባለችው የባህር ዳርቻ ከተማ ላይ ድንገተኛ ጉብኝት በማድረግ በቦታው ላይ ወደ አውሮፓ በጀልባ ለመሸጋገር ተሰናድተው የተቀመጡ ስደተኞችን የተመለከቱ ሲሆን ለእነሱ ስለሚያስፈልገው ድጋፍም አንስተዋል ምንም እንኳ ሀገራቸው “ለአውሮፓ ድንበር ጠባቂ” አለመሆኗን ቢገልጹም፡፡

በዕለቱ ፕሬዝዳንቱ ያንጸባረቁት አቋም በቅርቡ በአፍሪካዊያን ስደተኞች ላይ ከሰነዘሩት የዘረኝነት አስተሳሰብ ለየት ያለና የሀገራቸውን የዓረብ ማንነት ያንጸባረቀ ተብሎም ነው የተወሰደው ከጠቅላይ ሚኒስትራቸው ናጅላ ቦደን ጋር እንግዶችን በተቀበሉበት ጊዜ፡፡

ከውይይቱ በኋላ የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ለሀገሪቱ የተዘጋጀውን የገንዘብ ድጋፍ ይፋ አድርገዋል፡፡ አምስት ዓላማዎችን ይዟል የተባለው ይህ ድጋፍ 1.05 ቢሊዮን ዩሮ( 1.1 ቢሊዮን ዶላር) የበጀት ድጎማ ያካትታል፡፡ በቀጣይ ጊዜ የህብረቱ 27 አባል ሀገራት መሪዎች ተወያይተው ያጸድቁታልም ተብሏል፡፡

ከበጀት ድጋፍ በተጨማሪ ህብረቱ በኢንቨስትመንት ዘርፎችም ድጋፍ የሚያደርግለት ሲሆን ከእነዚህ መካከል ከፍተኛ ፍጥነት ያለው ብሮድ ባንድ፤ እንዲሁም ሌሎች ድጂታል መሠረተ- ልማቶችንም ይገነባሉ 300 ሚሊዮን ዩሮ የሚያወጡ የሀይድሮጂን እና ሌሎች ታዳሽ የኃይል ምንጮችን ጨምሮ፡፡

ፍለጋና ህይወት አድን ሥራዎችም የፕሮጀክቱ አካል ሲሆኑ ለእነዚህ የተመደበው የገንዘብ መጠንም 100 ሚሊዮን ዩሮ ነው ህገ- ወጥ የሰዎች ዝውውር መግታትን ጨምሮ፡፡ ስደተኞችን በኃይል ወደ ሀገራቸው መመለስን በተመለከተ ለተነሳው ቅሬታም የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትርና የኒዘርላንድስ ጠቅላይ ሚኒስትሮች “ሰብአዊ መብት የሚጋፋ አይደለም” በማለት መልስ ሰጥቷቸዋል፡፡

ህገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች የሚፈጥሩትን መረብ መበጣጠስም የፕሮግራሙ አንዱ አካል ሲሆን ችግሩን በማስመልከት የኒዘርላንድስ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ሩቴ ሲናገሩ “በአሁኑ ጊዜ ሁላችንንም እያጨናነቀን ያለ ችግር ነው” ብለዋል፡፡

በሳምንቱ ውስጥ ሁለት ጊዜ ወደ አፍሪካ ለመጡት ለጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒም ችግሩ ግንባር ቀደም አጀንዳ ነው ተብለዋል ምክንያቱም ሀገራቸው ከብዙ የአፍሪካ ሀገራት ለሚነሱ ስደተኞች መዳረሻና እነዚህም በምጣኔ ሀብት ከደቀቀችው ቱኒዚያ ስለሚነሱ፡፡

ከዚህ አንጻር ውሳኔዎችን አድንቀው ቱኒዚያ የ1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር የዓለም ገንዘብ ተቋም ድጋፍ እንድታገኝም መንገድ ተጠርጎላታል ብለዋል ምንም እንኳን የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ካይስ ሰይድ በዓለም ገንዘብ ተቋም ውሳኔዎች ብዙ ባይደሰቱም፡፡

ዱቄትና ነዳጅ በመሳሰሉት ምርቶች ላይ የሚደረገው ድጎማ እንዲቋረጥ ያልፈለጉት ፕሬዝዳንቱ በግዙፍ የመንግሥት አስተዳደር ሠራተኞች ላይ የሚደረገውን ቅነሳና ትርፋማ ያልሆኑ የመንግሥት ድርጅቶችን ወደ ግል በማዞሩ ሥራም አልተደሰቱም፡፡

ይልቁንም በምዕራባዊያን የሚዘወሩ የፖሊሲ አቅጣጫዎች ማህበራዊ ቀውስ እንደሚያስከትሉ አስጠንቅቀዋል፡፡ በፖሊሲያቸው ያልተደሰቱ የህብረተሰብ ክፍሎችን ማነሳሳት ሀገሪቱ ረዘም ላለ ጊዜ ተግባራዊ ያደረገችውን የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዳያሰናክልም ሰግተዋል፡፡

የዚህ ዓይነት ችግሮች በርካታ ቱኒዚያዊያንን ለተሻለ ህይወት ፍለጋ ወደ ባህር ማዶ እንደሚያሸጋግራቸው የገለጸው አፍሪካ ኒውስ ከሰሀራ በታች የሚገኙ አፍሪካዊያንን ጨምሮ ሀገሪቱ የብዙዎች መተላለፊያ እንደሆነችም አስታውቋል፡፡

ይህንን በማስመልከት የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጂዮርጂያ ሜሎኒ ጠንከር ያለ መልዕክት ነው ያስተላለፉት፡፡ በቱኒዚያ ያለ ያለመረጋጋት ለሁሉም የሰሜን አፍሪካ ሀገራት እንደሚተርፍና ይህም በሌላ በኩል ወደ ጣሊያን እንደሚሸጋገር ሲጠቅሱ የቱኒዚያው ፕሬዝዳንትም መፍትሄ የሚሆኑ መንገዶችን ገልጸዋል ከሠላምና ደህንነት ባለፈ የጭንቀት መንስኤ የሆኑትን እንደ ድህነትና ጉስቁልና ማጥፋት እንደሚያስፈልግ በመጠቆም፡፡

ስለ ቱኒዚያ ፍቼ የተባለው የደረጃዎች መዳቢ ተቋም ያወጣው ሪፖርትም እንዲሁ ተስፋ አስቆራጭ ነው ምክንያቱም ካለባት የዕዳ ጫና አንጻር ሀገሪቱ መክፈል ወዳለመቻል እየደረሰች ስለሆነ፡፡ መንግሥት ለውጦችን ያለማምጣት እራሱ ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋም ብድር እንዳታገኝ በማድረግ ለባሰ ውድቀት እንደሚዳርጋትም ተገልጿል፡፡

ለበጀት ጉድለቱ ሌሎች ምክንያቶች ተብለው የተገለጹት ኮሮና ቫይረስ፣ የዩክሬን ጦርነት፣ በፖለቲካ ውጥረቶች መነሻ የዓለም ገንዘብ ተቋም ብድር መከልከል እና የፕሬዝዳንት ሰይድ ለውጥን የማዘግየት አዝማሚያዎች ተጠቃሽ ናቸው ተብሏል፡፡

ፕሬዝዳንቱ ሥልጣናቸውን ለማጠናከር ሲባል ህገመንግሥቱ እንደገና እንዲጻፍ ማዘዛቸውና እንዲሁም ከተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች እና ነጻ ሚዲያ ጋር ወደ ውዝግብ መግባታቸውም እንዲሁ፡፡ አልጀዚራም በስፋት እንዳብራራው ከሆነ ወደ አውሮፓ የሚሄዱ ስደተኞች ችግር በቱኒዚያ ካለው ፖለቲካዊ ቀውስ ጋር ተያይዟል፡፡