ዛዉ ፥ አሳዛኙ ተዋናይ

በጌቱ ሻንቆ

ደግሜ ደግሜ አይቼዋለሁ፡፡ ነገር ግን ደጋግሜ አይቼውም ያልጠገብኩት ፊልም ቢኖር እሱ ነው፡፡ የሰው ልጆች ሰላማዊ ህይወት እንዴት በአንዲት አካባቢያቸው ላይ ሆና በወደቀች ቁስ ምክንያት መናጋት እንደሚገጥመውም ያየሁበት ጥበብ ነው፡፡

በአፍሪካ ውስጥ ከዘመናዊነት መነካካቶች በራቀ ስፍራ የሚኖሩ የቡሽሜን ጎሳዎች በሳላም ኑሯቸውን ይገፉ ነበር፡፡ አንዲት ባዶ የኮካኮላ ጠርሙስ ከሰማይ፣ ከአውሮፕላን ላይ ወድቃ ግን ሰላማቸውን ድፍርስ አደረገችው፡፡ ይህች ሳትፈለግ የመጣች ቁስ ሰላማቸውን ብጥብጥ በማድረጓ ምክንያት የጎሳው መሪ የሆነው አባወራ ጠርሙሷን፣ ወደ መንደራቸው ጥሏታል ብሎ ወዳመነው የሰማይ አምላክ፣ ፈጣሪ፣ ሽቅብ ወርውሮ በመመለስ ዳግም ወደ ሰላማቸው እንዲመለሱ ጥረት አድርጎ ነበር፡፡ ነገር ግን አልቻለም፡፡

በፊልሙ ውስጥ ያለውና ሰላማዊውን የጎሳ አባላት ኑሮ ያመሰው የኮካኮላ ጠርሙስ የሚወክለው ሀሳብ አለው፡፡ ዓለማችን የተሸከመችውን፣ ፕላስቲክ የሆነውን የህብረተሰብ ክፍል ይጠራል፡፡ ይህ ላስቲክ የሆነ የህብረተሰብ ክፍል እንዴት ሰላማዊ ኖሮን እንዳይመለስ አድርጎ እንደሚበክል በተምሳሌቱ በኩል ያሳያል፡፡

እናም ዘመናዊነት ጥሩ ቢሆንም ከዘመናዊነት ጋር ተስበው የሚመጡ አንዳንድ ነገሮች ደግሞ መጋኛዎች ናቸው የሚል እንድምታ እንድንይዝ ያደርገናል- ፊልሙ፡፡

እኔ ፊልሙን ከማየቴ በፊት ጅብ ሊበላኝ ቢያሯሩጠኝ እንዴት አስፈራርቼ ልመልሰው እችላለሁ የሚለው ዕውቀቱ የለኝም ነበር። ለካ ጀብን በቀላሉ አስፈራርቶ መመለስ ይቻላል፡፡ ጅብ ላይ የዛፍ ቅርፊት ጭንቅላትህ ላይ አቁመህ ወደ ራሱ ብትሮጥበት፣ በዚያ ላይ ኮስተር ቆጣ ብትልበት ሊበላህ ማባረሩ ቀርቶ ፈርቶህ ይሸሻል፡፡ ይህንን የተረዳሁት አይቼም፣ እንደገና አይቼውም ካልጠገብኩት ፊልም ነበር፡፡

ፊልሙ ‘‘ጋድ መስት ቢ ክሬዜ’’፣ ነው፡፡ የዚህ ፊልም መሪ ገፀ ባህሪ ደግሞ ኒ ዛዉ ቶማ ነው፡፡ ኒዛዉ ቶማ በ1944 ተወለደ የሚሉ አሉ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ የተወለደበት ዕለት አይታወቅም ይላሉ ፡፡

ይህንን ናሚቢያዊ፣ የካልሀሪ በረኸኛ ሰው፣ አስሶ ያገኘው ጃሚ ዩይስ የተባለ ደቡብ አፈሪካዊ የፊልም ዳይሬክተር ነው፡፡ ኒ ዛዉ እና ዩይስ በተገናኙ ጊዜ ኒ ዛዉ ከዘመናዊነት ጋር ንክኪ አልነበረውም፡፡ ዳይሬክተሩ ለዚህ የቡሽሜን ሰው ‘‘ጋድ መስት ቢ ክሬዚ ’’ በተሰኘውና ታሪኩን ባጭሩ ጠቆም ለማድረግ በሞከርነው ፊልም ውስጥ ከፍተኛ ሀላፊነት ጥሎበት ነበር፡፡ ሃፊነቱን በሚገባ ተወጥቷል- ከዘመናዊነት ጋር የነበረው ንክኪ በጣም ውስን ስለነበር ነው ይህንን ሀላፊነት በብቃት መወጣት የቻለው፡፡

ለፊልሙ ስራ ከመታጨቱ አስቀድሞ በነበረው ህይወት ዘመኑ ሶስት ነጭ ሰዎችን ብቻ ነበር በዓይኑ የተመለከተው፡፡ እናም ‘‘ጋድ መስት ቢ ክሬዜ’’ በኒ ዛዉ ብቃት ያለው ትወና አለማቀፍ ተዋዳጅነት አገኘ፡፡ እራሱ ዛዉም በፊል ተቀርፆ፣ መልሶ ራሱን ባየው ጊዜ እጅግ ነበር የተደነቀው፡፡

የፊልም ስራውን በመሪ ገፀ ባሀሪነት ለመጫወት ከፍተኛ መጠን ያለው የገንዘብ ስምምነት ነበር ያደረገው፡፡ ነገር ግን ለውለታው ሽልማት የሚገባው ይህ ምስኪንና ገራገር ናሚቢያዊ፥ በረኻ ውስጥ የሚኖር ሰው፥ በጥቂት ዶላሮች ክፍያ ብቻ ነበር ልፋቱን የተነጠቀው፡፡

ኒ ዛዉ የተወለደበትን ዕለት በትክክል እርሱም አያውቀውም፡፡ የመጀመሪያ ባለቤቱ ኮራ ትባላለች፡፡ እሷም የተወለደችበት ዕለት አይታውቀውም፡፡ ሌላም አውቃለሁ የሚል ሰው የለም፡፡ እናም በባልና ሚስቶቹ የልደት ቀን መፃፊያ ስፍራ ላይ ሁሌም የጥያቄ ምልክት እንዳረፈ ነው፡፡ ዛዉ የተለያዩ ቋንቋዎችን ይናገር ነበር፡፡ የተወለደበትን ማህበረሰብ ቋንቋ ንዋፃ ቋንቋ፣ ጁሊሆዋን የተባለ ቋንቋ፣ ኦትጂሄረሮ እና ሌሎች አፍሪካዊ ቋንቋዎችንም ይችላል፡፡

ኒ ዛዉ ስድስት ልጆች አሉት በህይወት። ወደ ፊልም ስራው ከመምጣቱ በፊት የሚኖርበት የፃን ማህበረሰብ ከሚቀልሳት ጎጆ ከፍ ያለ ቤትም ተመልክቶ አያውቅም። ስለወረቀት ገንዘብም ፈፅሞ የሚያውቀው ነገር አልነበረም፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የወረቀት ገንዘብን ያያት ‘‘ጋድ መስት ቢ ክሬዚ’’ ፊልም ላይ በመሪ ገፀ ባህሪነት ተሳትፎው 300 ሺ ዶላር የወዝ ዋጋ ሲከፈለው ነበር። እርግጥ ነው ይህ ገንዘብ የተሻለ መኖሪያ ቤት ሰርቶለታል፡፡ የውሃ መሳቢያ ሞተር ገዝቶለታል፡፡ መብራት አብርቶለታል። ለሶስቱም ሚስቶቹና ለተወለዱት ልጆቹ እነዚህ ነገሮች ተርፈዋል፡፡

ይሁንና ፊልሙ 60 ሚሊዮን ዶላሮች ትርፍ ያስገኘ ቢሆንም ዛዉ ግን የተሰጠችው ሶስት መቶ ሺ ዶላር ብቻ ነበረች፡፡ ይህም የሆነው የወረቀት ገንዘብን ጥቅም ባለማወቁ የተነሳ በተፈፀመበት ማታለል ነው፡፡

ዛዉ የከተማ ኑሮ ጀምሮ ነበር፡፡ ነገር ግን አስር ዓመት ከተማ ውስጥ ከኖረ በኋላ ወደ ካልኻሪ በረሃ ነው እንደገና የተመለሰው፡፡ በሰለጠነው ዓለም ውስጥ መኖር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ያተረፈው ነገር ቢኖር ጭንቀት ብቻ ነበር፡፡ እናም አልተመቸውም ፡፡ ከካለሀሪ በረሃ የህይወት ዘዬ ተነጥሎ መቆየቱ፥ ላስቲክ ከሆነ ህብረተሰብ ጋር መኖሩ እንደ ላስቲክ ጫማ አቃጠለው እንጂ የደመረለት ነገር አልነበረም፡፡ በዚህ ምክንያት ነው ወደ መንደሩ የተመለሰው፡፡

ጎሳውን ከተቀላቀለ በኋላ ወደ ግብርና ስራ ነው የገባው፡፡ በቆሎ ይዘራ፣ ዱባም ያበቅል፣ ባቄላም ያዘምር ነበር፡፡ የሚያረባቸው ከብቶችም ነበሩት፡፡ ከብቶቹ ግን ከሀያ አይበልጡም ነበር፡፡ ዘመናዊው ግብርና እየተስፋፋ በመሄዱ ከዚያ ቁጥር በላይ ከብቶች የማርባት እድል እንዳይኖረው አደረገው። ዛዉ የክርስትና ሀይማኖት ተከታይም ሆኖ ነበር። የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን አጥምቃ ነበር ወደ ሀይማኖቷ የቀላቀለችው፡፡

ዛዉ ወደ ቀደመ ኑሮው ሲመለስ ድህነት ተጭኖት ነበር፡፡ የሳንባ በሽታም ይዞት ነበር፡፡ በመጨረሻም በጁላይ 5/2003 ከቤቱ ወጥቶ ለዕንጨት ለቀማ በተሰማራበት ህይወቱ ህልፈት አጋጠማት የሚሉ አሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ለአደን በተሰማራበት ነው የሞት ጥላ ተጠግቶ የያዘው ይላሉ፡፡

ዛዉ ይህችን ዓለም ጥሎ ሲሄድ ዕድሜው ሀምሳ ስምንት ወይም ሀምሳ ዘጠኝ እንደሆነ ይገመት ነበር፡፡ በመኖሪያ አካባቢው የፁሙክዌ ማህበረሰብ መለስተኛ ባህላዊ የአሸኛኘት ስነስርዓት ተደርጎለታል፡፡ ተዋናዩ የባላገር ሰው፣ ስርዓተ ቀብሩ የተፈፀመው ሁለተኛ ሚስቱ መቃብር አጠገብ ነበር፡፡ ነፍስ ይማር!!