ፊንቴክስ የፈርኒቸር፣ የቤተ ውበትና የግንባታ አጨራረስ ምርቶች፣ የአገልግሎቶች እና ቴክኖሎጂ ዓለም አቀፍ አውደ ርዕይ መካሄድ ጀመረ

ፊንቴክስ የፈርኒቸር፣ የቤተ ውበትና የግንባታ አጨራረስ ምርቶች፣ የአገልግሎቶች እና ቴክኖሎጂ ዓለም አቀፍ አውደ ርዕይ መካሄድ ጀመረ

ሀዋሳ፡ ሰኔ 08/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) ፊንቴክስ የፈርኒቸር፣ የቤተ ውበትና የግንባታ አጨራረስ ምርቶች፣ የአገልግሎቶች እና ቴክኖሎጂ ዓለም አቀፍ አውደ ርዕይ በአዲስአበባ ሚሊኒየም አደራሽ መካሄድ ጀመረ።

ለ4ኛ ጊዜ ከሰኔ 8 እስከ 11 ቀን 2015 ዓ.ም ለአራት ቀናት የሚካሄደው አውደ ርዕዩ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚመጡ እቃዎችን በማስቀረት በኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት እድገት ላይ የጎላ ሚና ይጨወታል የሚል ተስፋ የተጣለበት መሆኑ ተመላክቷል።

የዓለም ባንክ ጥናት እንደሚያሳየው ከሆነ ኢትዮጵያ በርካታ ለፈርኒቸር የምርት ግብአት የሚሆን ዛፍ በብዛት የሚገኝባት ብትሆንም የደን ጥበቃውና የአቅርቦት መጠኑ በተቀናጀ መልኩ ስለማይሰራ ለፈርኒቸር ማምረቻ የሚሆነው ጥሬ እቃ ከሌሎች ሀገራት በማስመጣት እንደሚሰራው ተገልጿል።

የፈርኒቸር ምርቶችን ከውጭ አገር በማስገባት ኢትዮጵያ ከአፍሪካ በ5ኛ ደረጀ የተቀመጠች ሲሆን ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ደግሞ ከኬኒያ ቀጥሎ በ2ኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የ2016 ጥናት ያሳያል።

እንደ ኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብአት ልማት ጥናት እ.አ.አ 2018 ዓ.ም ኢትዮጵያ የ10 ቢሊየን ብር የፈርኒቸር ግዥ የፈጸመች ሲሆን ከዚህ ውስጥም 20 በመቶ ብቻ ከአገር ውስጥ አምራቾች የተፈጸመ ግዥ ነው።

ስለሆነም አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች እንዲሁም አነስተኛና መካከለኛ የንግድ ተቋማት ለፈርኒቸር ዘርፉ እድገት ብሎም ለሥራ ዕድል ፈጠራ የጀርባ አጥንት መሆናቸውን ተሳቢ በማድረግ የዘርፉን ምርቶች በመግዛት ዘርፉን መደገፍና ማነቃቃት ያስፈልጋል ተብሏል።

ይህንን መነሻ በማድረግ ፕራና ኤቨንትስ እና አፍሪካ ትረስትድ ፓርትነርስ በጋራ ባዘጋጁት አውደ ርዕይ በዘርፉ ጥናት ያደረጉ ምሁራን ጥናታዊ ጽሁፍ የሚያቀርቡበት ሲሆን በኢንዱስትሪው የተሰማሩና ለመሠማራት በጥናት ላይ የሚገኙ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች ከሚመለከታቸው የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ጋር ስለ ኢንደስትሪው ተግዳሮቶችና ቀጣይ የእድገት አቅጣጫ ምክክር የሚያደርጉበትን ዕድል የሚፈጥር ነው።

የአፍሪካን ትረስትድ ፓርትነርስ ማናጀር አቶ አክሊለ በለጠ እንደገለፁት በቀጣይ ዓመታት ምርቶቹን የማምረት አቅም በማሳደግ ወደ ምስራቅ አፍሪካ ሀገር ኬኒያ ናይሮቢ አውደ ርዕይ በማዘጋጀት የውጭ ሀገር ፋይናንስ ለማግኘት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ይሰራል።

አውደ ርዕዩን በይፋ ያስጀመሩት የኢንደስትሪ ሚኒስትር ዋና አማካሪና የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ አስፋው አበበ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ትልቁ ዓለማ የሀገር ውስጥ የማምረት አቅም በማሳደግ ወደ ውጪ የሚላኩ ምርቶችን ጥራትና ብዛት ማሳደግ ነው።

ስለሆነም የፈርኒቸር፣ የቤተ ውበትና የግንባታ አጨራረስ ምርቶችን ውጤታማነትና የአገር ተቀባይነትን ብሎም ወደ ውጪ የመላክ አቅምን ለማሳደግ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ አቶ አስፋው አረጋግጠዋል።

አውደ ርዕዩ ትብብርንና እውቀት መጋራትን ትኩረት ባደረገ መልኩ መከናወን እንዳለበትም አስገዝበዋል።

በአውደ ርዕዩ በርካታ የሀገር ውስጥ አምራቾች የሚሳተፉ ሲሆን ከ400 በላይ ገዥዎችና ከ4000 በላይ የንግዱ ማህበረሰብ አባለትና ጎብኝዎች ይስተናገዱበታል ተብሏል።

የዓለም አቀፉ የንግድ መረጀ እንደሚያሳየው እ.አ.አ በ2020 ዓ.ም አጠቃላይ የፈርኒቸር ንግድ እንቅስቃሴ 175 ቢሊየን ዶላር ገደማ ነበር።

ዘጋቢ፡ ጌታሁን አንጭሶ