እንደ ሀገር የተፈጠሩ አለመግባባቶችን ለመፍታት ሀገር በቀል እሴቶች የጎላ ሚና እንዳላቸው ተጠቆመ

እንደ ሀገር የተፈጠሩ አለመግባባቶችን ለመፍታት ሀገር በቀል እሴቶች የጎላ ሚና እንዳላቸው ተጠቆመ

ሀዋሳ፡ ሰኔ 08/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) እንደ ሀገር የተፈጠሩ አለመግባባቶችን ለመፍታት ሀገር በቀል እሴቶች ትልቅ ሚና እንዳላቸው የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የሀገራዊ ምክክር ቅድመ ውይይት በሲዳማ ክልል ባሉ ወረዳዎች እየተካሄደ ነው።

በቅድመ ውይይቱ አጀንዳ እና የተወካዮች ልየታ ቀዳሚ ተግባር መሆኑን ኮሚሽኑ አመልክቷል።

በይርጋዓለም ከተማ እየተካሄደ ባለው ቅድመ ጉባኤ ከአርቤጎና፣ ከሻፋሞ፣ ከደራራ፣ ከይርጋአለም ከተማ፣ ከዳሌ፣ ከሎካ አባያ እና ወንሾ ወረዳዎች የተገኙ የህብረተሰብ ተወካዮች ተሳትፈዋል።

የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዮናስ አዳዬ ለደቡብ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ድርጅት እንደገለፁት፥ የምክክሩ መነሻም መድረሻም ሰላምን በሰላማዊ መንገድ ብቻ ማምጣት ነው ብለዋል።

ሀገራዊ ምክክር የሚዘጋጀው የአንድ ሀገር ዜጎች በዋና በዋና ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ ልዩነቶች ሲኖራቸው ነው ያሉት ዶክተር ዮናስ፥ በኢትዮጵያ እየታየ ያለውን አለመግባባት በምክክር ብቻ ለማስተካከል እየተሰራ ነው ብለዋል።

ያሉ አመግባባቶችን ለመፍታት ሀገር በቀል ዕውቀቶች ትልቅ ሚና አላቸው ያሉት ዶክተር ዮናስ የሲዳማ “አፊኒ” ስርዓት ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው ብለዋል።

በሁሉም የኢትዮጵያ አከባቢዎች ተመሳሳይ የችግር መፍቻ ቁልፎች ስለመኖራቸው ጠቅሰው ይሄን በአግባቡ መጠቀም ይገባልም ብለዋል።

የሲቪክ ማህበራትን በመወከል በጉባኤው ላይ እየተሳተፉ ያሉት አቶ ገዛኸኝ አሰፋ በሰጡት አስታያየት፥ የኢትዮጵያን ችግር ለመፍታት ምክክር ብቻ መፍትሔ ስለመሆኑ አንስተው በዚሁ መንገድ በሰከነ መንፈስ መቀጠል አለብን ነው ያሉት።

የንግዱን ማህበረሰብ በወከል ከበንሳ የተገኙት አቶ ሙሉነህ ቦኣ ከዚህ በፊት የነበሩብንን ችግሮች ፈጥነን በምክክር እና በውይይት መፍታት ባለመቻላችን አሁን ላለንበት ነባራዊ ሁኔታ ዳርጎናል በማለት ከስህተታችን በመማር የወደፊቱን መንገድ ለማስተካከል በጋራ መስራት አለብን በለዋል።

ዘጋቢ፡ ጀማል የሱፍ