ሁሉም ህብረተሰብ ክፍል አካባቢውን ከብክለት መጠበቅ ይኖርበታል – የሚዛን ግርብርና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኮሌጅ ተማሪዎች እና ሰራተኞች

ሁሉም ህብረተሰብ ክፍል አካባቢውን ከብክለት መጠበቅ ይኖርበታል – የሚዛን ግርብርና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኮሌጅ ተማሪዎች እና ሰራተኞች

ሀዋሳ፡ ሰኔ 08/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የሚኖርበትን አካባቢ የመጠበቅና የመንከባከብ ሀላፊነት እንዳለበት ተገንዝቦ አካባቢውን ከብክለት እንዲጠብቅ የሚዛን ግርብርና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኮሌጅ ተማሪዎች እና ሰራተኞች ገለጹ፡፡

የኮሌጁ ተማሪዎችና ሰራተኞች የከተማ ጽዳት ማካሄዳቸውና ለ5ኛ ዙር የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ፕሮግራም ቅስቀሳ ማድረጋቸውም ተጠቁሟል፡፡

በጽዳት ዘመቻው ላይ ተሰማርተው እያሉ ካነጋገርናቸው ተማሪዎችና የኮሌጁ ሰራተኞች መካከል ወ/ሮ ሔዋን መብራቱ፣ ተማሪ ቢኒያም ታምራት፣ ተማሪ አስራት አማኑኤል እንደገለጹት የአካባቢ ብክለት በዋነኝነት የሚከሰተው ሁሉም ህብረተሰብ ሀላፊነቱን በአግባቡ ባለመወጣቱ ምክንያት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የአካባቢ ብክለት ለጤና ጠንቅ ስለሆነ ከተማውን በማጽዳት ህብረተሰቡ ከበሽታ ራሱን እንዲከላከልና ለአካባቢ ጥበቃ ሚናውን እንዲወጣ ለማስተማር በዘመቻው መሰማራታቸውን አብራርተዋል፡፡

በኮሌጁ የተፈጥሮ ሀብት ክፍል መምህር የሆኑት መምህር ሁሴን ከድር በኮሌጁ የአካባቢ ጥበቃ ክበብ ተመስርቶ ተማሪዎች ስለ ኣካባቢ ጥበቃና እንክብካቤ የተለያዩ ስራዎችን እእየሰሩ እንደሆነ ገልጸው፤ ይኸውም ተማሪዎች ከኮሌጁ ስልጠና አጠናቀው ወደ የአካባቢያቸው ሲመለሱ ያገኙትን ልምድ ማካፈል እንዲችሉ ይረዳቸዋል ብለዋል፡፡

በዕለቱ “ስለምንኖርበት አካባቢ ይመለከተናል፣ የአካባቢ ብክለት መንስኤ ሳንሆን የመፍትሄ አካል እንሁን” በሚል መሪ ቃል ከ6መቶ በላይ የኮሌጁ ተማሪችና ሰራተኞች በሚዛን ከተማ የጎዳና ላይ ጽዳት ማድረጋቸውንም ገልጸዋል፡፡

በዚህ ጽዳት ወቅት አንዳንድ የከተማው ማህብረሰብ አባላት ከእነሱ ጋር በዘመቻው ሲሳተፉ መታየታቸውን አቶ ሁሴን ጠቁመው የከተማ ጽዳት ፕሮግራም በዚህ ብቻ እንደማያበቃና ሌላ ፕሮግራም በማዘጋጀት ህብረተሰቡን ለማስተማር ግብ መያዙንም አስረድተዋል፡፡

የኮሌጁ ዲን አቶ ሀብታሙ ካፍቲን በበኩላቸው ኮሌጁ ከሚተገብራቸው ቁልፍ ተግባራት አንዱ የተፈጥሮ ሀብትና አካባቢ ጥበቃ ስራ እንደሆነ ገልጸው አሁን ወቅቱ ቸግኝ የሚተከልበት ወቅት ስለሆነ ህብረተሰቡ በየአካባቢው የተዘጋጁትን ችግኞች በነቂስ ወጥቶ እንዲተክል ከአካበቢ ጽዳት ጋር በማያያዝ ቅስቀሳ መደረጉን አብራርተዋል፡፡

ኮሌጁ የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ጠቃሜታ ያላቸው ከ3መቶ ሺህ በላይ ችግኞችን ለተከላ ማዘጋጀቱንና እነዚህን ችግኞች ከተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች ጋር በመሆን እንደሚተክሉም ገልፀዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በቤንች ሸኮ ዞን ሰሜን ቤንች ወረዳ ተለይቶ ለኮሌጁ በተሰጠው የተጎዳ መሬት ላይ ለሁለት አመት ደን በመትከል ስፍራው እንዲያገግም መደረጉን አቶ ሀብታሙ ተናግረው በዘንድሮ አረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ወቅትም በቀሪ ቦታዎች እንተክላለን ብለዋል፡፡

ህብረተሰቡ አረንጓዴ አሻራ በሚያኖርበት ጊዜ በሌላ ዓለም እንደሚደረገው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ላይ በማተኮር እንዲተክልም አሳስበዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ወሰኑ ወዳጆ – ከሚዛን ጣቢያችን