የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ምቹ የትምህርት አካባቢን መፍጠር ወሳኝ መሆኑ ተመላከተ

የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ምቹ የትምህርት አካባቢን መፍጠር ወሳኝ መሆኑ ተመላከተ

የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ምቹ የትምህርት አካባቢን መፍጠር ወሳኝ መሆኑን በደቡብ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዲላሞ አቶሬ አመላክተዋል::

በስልጤ ዞን ምዕራብ አዘርነት በርበሬ ወረዳ በዱና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ15ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ለደረጃ ማሻሸያ የተገነቡ ህንፃዎች ምረቃ ፕሮግራም ተካሂዷል።

የምዕራብ አዘርነት በርበሬ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሽኩረቶ አደም እንደተናገሩት፤ ለሰው ልጅ ማንም ሊወስድበት የማይችለው ውድና ተንቀሳቃሽ ንብረቱ የአዕምሮ ልማቱ ነው።

ከባለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በወረዳው በህብረተሰብ ተሳትፎ ብቻ በተገኘ ከ1 መቶ ሚሊዮን ብር በላይ በሚገመት ወጪ በትምህርት ዘርፉ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ገልፀው በቀጣይ አዳዲስ ፕሮጀክቶች እንደሚጀመሩም ጠቁመዋል።

የስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ ከድር በበኩላቸው ከባለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አንስተው ባለፈው ዓመት በህብረተሰቡ ተሳትፎ ከ1 መቶ 18 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ በሥራ ላይ ለማዋል መቻሉን ጠቁመዋል።

የዞኑ ህዝብና ተወላጆች ለልማት ተግባራት ያለውን ሳይሰስት በመስጠት ከድህነትና ኋላ ቀርነት ለመውጣት የሚተጋ ህዝብ መሆኑን  የዚህ ትምህርት ቤት ደረጃ ማሻሻል ተግባር አንዱ ማሳያ ነውና ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ።

በእለቱ በክብር እንግድነት የተገኙት በደቡብ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዲላሞ አቶሬ አሁን ባለንበት በቴክኖሎጂ ዘመን ተወዳዳሪ ለመሆን ትምህርት ወሳኝ ነው ብለዋል።

የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ምቹ የትምህርት አካባቢን መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን በመረዳት የትምህርት ቤቱን ደረጃ በማሻሻል ተግባር የአከባቢው ህብረተሰብና ተወላጆች ያደረጉትን አስተዋጽኦ አድንቀዋል።

ተማሪዎች ከአካባቢና ከሀገር አልፈው በአለም ደረጃ ተወዳዳሪ በመሆን በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ሚና መጫወት የሚችሉት በትምህርት ቤቶች ውስጥ መሆኑን ያነሱት ዶክተር ዲላሞ በትምህርት ቤቱ አስፈላጊ ቀሪ ግብአቶችን ለማሟላት በክልሉ በኩል እንደሚሰራም አሳውቀዋል።

በትምህርት ቤቱ ደረጃ ማሻሻል የተለያዩ አአስተዋጽኦ ያደረጉ አካላትና የአካባቢው ነዋሪዎችም በህብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ በተከናወነው ተግባር መደሰታቸውን ገልፀው ድጋፋቸውን በሌሎች ፕሮጀክቶችም አጠናክረው እንደሚያስቀጥሉ ተናግረዋል።

ከምረቃ ስነ-ስርዓቱ ጎን ለጎን በህብረተሰቡ ተሳትፎ የሚገነቡ አጠቃላይ የጤና ኬላ እና የልዩ መዋዕለ ህፃናት ትምህርት ቤት ግንባታ መሠረተ ድንጋይ የማኖር ተግባር የተከናወነ ሲሆን በትምህርት ቤት ማሻሻል ተግባር የላቀ ሚና ለነበራቸው አካላትም ዕውቅና ተሠጥቷል።

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ በደቡብ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪ አቶ ኡስማን ሱሩርን ጨምሮ የክልልና የዞን ከፍተኛ አመራሮች የአከባቢ ህብረተሰብና ተወላጆች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።

ዘጋቢ: ኤርጡሜ ዳንኤል – ከሆሳዕና  ጣቢያችን