በክልሉ የሚገኘውን የመልማት አቅም በመጠቀም የአመራር አካላት በመፍጠንና በመፍጠር የተጣለባቸውን ሃላፊነት መወጣት አለባቸው – አቶ ጸጋዬ ማሞ

በክልሉ የሚገኘውን የመልማት አቅም በመጠቀም የአመራር አካላት በመፍጠንና በመፍጠር የተጣለባቸውን ሃላፊነት መወጣት አለባቸው – አቶ ጸጋዬ ማሞ

ሀዋሳ፡ ሰኔ 06/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) በክልሉ የሚገኘውን የመልማት አቅም በመጠቀም የአመራር አካላት በመፍጠንና በመፍጠር የተጣለባቸውን ሃላፊነት መወጣት እንዳለባቸው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጸጋዬ ማሞ አሳሰቡ፡፡

የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ በለውጡ ዓመታት የተገኙ ትሩፋቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠልና በሂደቱ ባጋጠሙ ተግዳሮቶች ዙሪያ ከአመራር አካላት ጋር በቦንጋ ከተማ ውይይት እያካሄደ ነው፡፡

የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጸጋዬ ማሞ እንደገለጹት ብልጽግና ፓርቲ በሀገር አቀፍ ደረጃ በለውጡ ዓመታት የተገኙ ውጤቶችንና ባጋጠሙ ተግዳሮቶች ዙሪያ ግምገማ ነክ ስልጠና በማካሄድ ሂደቱ በየደረጃው ባሉት መዋቅሮች እንዲደርስ በመደረጉ የአመራር ዉይይትና ስልጠና እየተካሄደ ነው ብለዋል፡፡

ውይይቱ በዋናነት ባለፉት የለውጡ ዓመታት የተገኙ ውጤቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠልና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በመፍታት አመራሩ የሚጠበቅበትን መወጣት እንዲችል ትኩረት ያደረገ መሆኑን አቶ ጸጋዬ አመላክተዋል፡፡

ከለውጡ ጋር ተያይዞ የመጣውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት መፍትሄው ምርትና ምርታማነት ማሳደግ ነው ያሉት አቶ ጸጋዬ ክልሉ ያለውን ሰፊ መሬት፣ የሰው ኃይልና የተፈጥሮ ጸጋዎችን መጠቀም እንደሆነ የአመራር ሃይሉ ተገንዝቦ መከወን አለበት ብለዋል፡፡

በየደረጃው የሚገኘው የሕብረተሰብ ክፍል ከአመራሩ በርካታ ጉዳዮችን የሚጠብቅ በመሆኑ የአመራሩ ጥንካሬና የለውጥ ሃይል ሆኖ በመገኘት በየአካባቢው ለሚከሰቱ ችግሮች ምላሽ ለመስጠት መዘጋጀት እንዳለበት አቶ ጸጋዬ አስታውቀዋል፡፡

አመራሩ የህዝብን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በመለየት፣ ፈጣን ምላሽ ለሚፈልጉ ጉዳዮች መፍትሔ መስጠት እንዲያስችለው የውይይት መድረኩ ትልቅ አቅም ይፈጥራል ያሉት ኃላፊው ከፊታችን የሚታየው ብሩህ የብልፅግና ዘመን ዕዉን እንዲሆን አመራሩ በቅንጅትና በመናበብ እንዲሰራ አሳስበዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ 345 የሚሆኑ የክልል፣ የዞን፣ የወረዳና የከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች እየተሳተፉ ሲሆን ለአምስት ተከታታይ ቀናት እንደሚቆይም አቶ ጸጋዬ ማሞ ገልጸዋል።

ዘጋቢ፡ መለሰ ገብሬ – ከቦንጋ ጣቢያችን