በእንቅፋታቸው ክምር የስኬታቸውን ማማ እየገነቡ የሚገኙት ዐይነ ስውሩ አርሶ አደር

በእንቅፋታቸው ክምር የስኬታቸውን ማማ እየገነቡ የሚገኙት ዐይነ ስውሩ አርሶ አደር

የጌዴኦ ዞን ዲላ ዙሪያ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት ዐይነ ስውሩ አርሶ አደር አንተነህ ጥላሁን በእንቅፋታቸው ክምር የስኬታቸውን ማማ እየገነቡ ይገኛሉ።

የሰው ልጆች ሕይወት ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ በሆኑ ብርቱ ፈተናዎች የታጀበ ነው፡፡

ሰነፎች በፈተናዎቻቸው ተደነቃቅፈው መውደቅ ብቻም ሳይሆን ውድቀታቸውን እንደ እጣ ፈንታ ተቀብለው ከሁኔታዎች ጋር ራሳቸውን አዋህደው ይኖራሉ፡፡

ብርቱዎች ከውድቀታቸው ተምረው በአዲስ ጉልበት ዳግም በመቆም የሕይወትን ጉዞ በብርታት ይጀምራሉ፡፡

ቀድመው የነቁ ብልሆች ደግሞ ከድል በፊት አይቀሬ ስለሆነው የሕይወት ፈተና ራሳቸውን ያዘጋጃሉ የሚገጥሟቸውን የእንቅፋት ድንጋዮች ተጠቅመውም የስኬት መንገዳቸውን አስጊጠው ይገነባሉ፡፡

የ15 ላምና ጊደሮች እንዲሁም የሁለት ሄክታር ማሳ ባለቤት የሆኑት አርሶ አደር አንተነህ ጥላሁን በጉልምስና ዕድሜ የገጠማቸውን የዐይን ብርሀን የማጣት ብርቱ ፈተና በመንፈስ ጥንካሬ አሸንፈው በእንቅፋታቸው ክምር የስኬታቸውን ማማ እየገነቡ የሚገኙ ልበ ብርሀን ናቸው፡፡

ትውልድና ዕድገታቸው በጌዴኦ ዞን ዲላ ዙሪያ ወረዳ አንዲዳ ቀበሌ የሆነው አርሶ አደር አንተነህ ከልጅነታቸው ጀምሮ ባደጉበት ቀዬ በመንፈሳዊ ህይዎት ሲያገለግሉ የእሳቸው ፈተና ዓይነ ስውርነት ነበርና “ሬቲና” የተሰኘው የዐይናቸው ክፍል በመጎዳቱ በሂደት የዐይን ብርሀናቸውን አጡ፡፡

“የዐይን ብርሀንን ማጣት መንፈሳዊ ጥንካሬ እንደማይነጥቅ አስረግጠው የሚገልፁት አርሶ አደር አንተነህ እንዲህ አይነት ከባድ የሕይወት መሰናክል ሲገጥም በእንግዳ ስሜት መናወጥ፣ መብሰልሰልና መረበሽ ሰውኛ ባህሪ ነውና ለጊዜውም ቢሆን ከጓደኞቼ ተነጥዬ ወደኋላ እቀር ይሆን የሚል ስሜት ተሰምቶኛል” ነው ያሉት፡፡

ሆኖም የኋሊት የሚጎትታቸውን ስሜት አሸንፈው የሚያገለግሉትን ፈጣሪያቸውን በፀሎት ጠይቀው መክሊታቸውን ፍለጋ እንደገቡ ከኢዜአ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

“በሰጠኝ ነገር ምንም አልተማረርኩም ግን ለጊዜው ይሰማሀል የሰው ልጅ ነህና አንድ ነገር ሲገጥምህ እንዴት ከጓደኞቼ ወደኋላ ቀረሁ የሚል ነገር ተሰምቶኛል” ሲሉ ይገልጻሉ።

አባታቸው ጎበዝ አርሶ አደር እንደነበሩ የሚያስታውሱት ባለታሪካችን፤ እሳቸውም አባታቸውን በማገዝ በልጅነት የቀሰሙት የግብርና እውቀት ወደዚሁ ሥራ እንዲያማትሩ ምክንያት ሆኗቸዋል፡፡