የሥነ ምግባር መጓደል ለበርካታ ቀውሶች እንደሚዳርግ ተገለፀ

የሥነ ምግባር መጓደል ለበርካታ ቀውሶች እንደሚዳርግ ተገለፀ

ሀዋሳ፡ ሰኔ 01/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) የሥነ ምግባር መጓደል ለበርካታ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውስ እንደሚዳርግ ተገለፀ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥነ ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን በአስተዳደሩ ሥር ከሚገኙ የሀይማኖት አባቶች እና አባገዳዎች ጋር በሥነ ምግባር፣ በሌብነት ጠንቆች እና በሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት እያደረገ ነው።

የአስተዳደሩ ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀማል ረዲ እንደገለፁት ሌብነት የአገርን ኢኮኖሚ ከማናጋቱ ባሻገር በከፍተኛ ሁኔታ ሰላምን ያናጋል።

ሌብነትን የሚጸየፍ ትውልድ በመገንባት ረገድ የሀይማኖት አባቶች ኃላፊነታቸውን በተገቢው ሊወጡ እንደሚገባ ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የእምነት ሀገር መሆኗን ገልጸዋል።

ሆኖም ግን አሁን አሁን የሥነ ምግባር መጓደል እና ሌብነት በቤተእምነቶች ጭምር እየተንሰራፋ ስለሆነ የእምነት አባቶች በሥነ ምግባር የታነጸና ከክፉ ድርጊት የራቀ ትውልድ እንዲገነባ አበክረው ሊሰሩ ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል።

ሌብነት እየነገሰ ሲመጣ መንግስታት ሥርዓት አልባ ይሆናሉ ያሉት አቶ ጃንጥራር አባይ የሥነ ምግባር መጓደልንና ሌብነትን በጋራ መከላከል ይገባልም ብለዋል።

የሥነ ምግባር መጓደል ለሌብነት መስፋፋት፣ ለአድሎአዊ አሠራር፣ ለአሠራር ጥሰት፣ ብሄርተኝነትን ለማቀንቀን እና መሰል ችግሮች መስፋፋት መንስኤ እንደሚሆንም አስታውቀዋል።

ችግሮቹን መፍታት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያም ከሃይማኖት አባቶች ጋር ውይይት ተደርጓል።

ዘጋቢ፡ ጌታሁን አንጭሶ