የሥራ ትንሽ የለውም

የሥራ ትንሽ የለውም

በማቱሳላ ኃይሉ

ወ/ሮ መብራት ዘውዴ ይባላሉ፡፡ የተወለዱት በወላይታ ዞን ሶዶ ከተማ ማርያም ሠፈር በ1966 ዓ.ም ነው፡፡

ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል የተማሩት በከተማው ጊዮርጊስ በሚባል ትምህርት ቤት ነው፡፡ መለስተኛ 2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አቋርጠው ትዳር መያዛቸውን ይናገራሉ፡፡ ከዚያ በኋላ ነው ወደ ሀዋሳ ከተማ የመጡት፡፡

አሁን የ4 ልጆች እናት ናቸው፡፡ እንጀራ በመጋገር ሥራ ልጆቻቸውን እያስተዳደሩ መቆየታቸውን የሚናገሩት ወ/ሮ መብራት በሀዋሳ ከተማ በ02 ቀበሌ በሚገኘው የቀበሌ ቤት ሲኖሩ እንደነበሩ አስረድተዋል።

የመጀመሪያ ልጃቸው በዲግሪ ተመርቆ ሥራ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ ሁለተኛውም እንዲሁ በዲግሪ ተመርቆ ሥራ ይዟል፡፡ ሦስተኛው ልጃቸው በምህንዲስና ትምህርት ተመርቆ በመምህርነት ሥራ ተቀጥሮ እየሠራ ነው፡፡ አራተኛው ልጃቸው ዘንድሮ የ12ኛ ክፍል ፈተና ሊወስድ እየተዘጋጀ እንደሆነም ነግረውናል፡፡

ወ/ሮ መብራት ትዳር ከያዙ በኋላ እንጀራ በመጋገር ሥራ ላይ ነበር የተሰማሩት፡፡ ከደርግ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ የተሰማሩበት ይኸው ስራ ትልቁ መተዳደሪያቸው ሆኖ ቆይቷል። የሚጋግሩትንም እንጀራ ለአንድ ትልቅ የመንግስት ተቋም ያስረክቡ ነበር፡፡ በዚያ ጊዜ ከሚያገኙት ትርፍ ዕቁብ እየጣሉና እየቆጠቡ በከተማዋ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ቦታ እስከ መመራት ደረሱ፡፡

ስለቁጠባ ሲናገሩ፡- “ሰው ዕድርን እንጂ ቁጠባን ብዙም አያውቅም፡፡ ቁጠባ ያሳድጋል። ቆጥቦ ትልቅ ደረጃ መድረስ ይቻላል” ይላሉ። እርሳቸው ከዚህ ቀደም በቁጠባ ዙሪያ እንዲማሩ ያደረጋቸውን ግለሰብ ተሞክሮ በማንሳት፡፡ የግለሰቡም ተሞክሮ ትንሽ ገንዘብ ሲያገኝ በየወቅቱ እየቆጠበ አሁን ወደ ባለሃብትነት እንደተቀየረ የሚያመላክት ነው፡፡

ወ/ሮ መብራት በግላቸው በአንድ ወቅት ወደ 20 ሺህ ብር መቆጠባቸውን ያስታውሳሉ። ያላቸውን እየተበደሩ፣ እየሠሩና እየነገዱም እዚህ መድረሳቸውን ይናገራሉ። በዚህ ቁጠባ ነው ቤት ሊሠሩ የቻሉት፡፡

በኋላ ይህንን ቤታቸውን በባለቤታቸው ህመም ምክንያት ሸጠው ገንዘቡን ለሕክምና ለማዋል ተገደዱ፡፡ በተረፈው ገንዘብ በዳቶ ኦዳሄ ቀበሌ፣ ቤት ሠርተው መኖር ጀመሩ። ይህን ያደረጉት የሚረዳቸው ሰው ባለመኖሩና ራሳቸውን ያልቻሉ ህጻናት ስለነበሯቸው ችግራቸውን ባለው አጋጣሚ ለመወጣት በማሰብ ነበር፡፡

በገዙበት ቤት እስካሁን እየኖሩበት ነው። ከባለቤታቸው ሕልፈት በኋላም ሠርቪስ ቤቶችን ጨምረው ሠርተው እያከራዩ የሚጠቀሙ ጠንካራ ሴት ለመሆንም በቅተዋል፡፡

ይህን ሁሉ ነገር መሥራት የቻሉት በንግድ ነው፡፡ ከዚያ የሚያገኙትን ገንዘብ በመቆጠብ ለዛሬው ስኬት መብቃታቸውን ያስረዱናል። ከዚያ ውጭ ሌላ ገቢ እንደሌላቸውም ይገልጻሉ፡፡

ወ/ሮ መብራት ሠርተውና ነግደው በራሳቸው ጉልበት ተጣጥረው መኖራቸው ባስገኘላቸው ሀብት ደስተኛ ሆነው ኑሯቸውን እየመሩ ይገኛሉ፡፡ በገቢያቸውም ምንም ሳይቸገሩ ልጆቻቸውን አስተምረው ለትልቅ ደረጃ እያበቁ ስለመሆናቸውም ይናገራሉ፡፡

ታዲያ ለዚህ ስኬት ከመብቃታቸው በፊት በብዙ ጥረትና ጥንካሬ ማሳለፋቸውን ያስታውሳሉ፡፡ እንጀራ በሚጋግሩበት ወቅት የደቡብ ኦሞ ስኳር ፋብሪካ ሥራ ሊጀምር ሲል ሠራተኛ እንደሚፈልግ ይሰማሉ፡፡

ጊዜም ሳይፈጁ በሰፈራቸው ከሚገኙ ሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ወደ ስፍራው አቀኑ፡፡ ኮንትራት ወስደውም መስራት ጀመሩ፡፡ በሥራቸውም ውጤታማ ሆኑ፡፡ ታዲያ ይህ ሥራ ተጨማሪ መነገጃ ገንዘብና ሌሎችንም ጥሪቶች ቋጥረው ወደ ሀዋሳ እንዲመለሱ ረዳቸው፡፡

ሥራውን በሚሰሩበት ወቅት የአየር ፀባዩ በረሃማ ሆኖ ቢፈታተናቸውም ጠንክረው በመስራታቸው ውጤታማ እንዳደረጋቸውም ያስረዳሉ፡፡ ያቺ ያጠራቀሟት ጥሪት ናት እንግዲህ በሀዋሳ ከተማ ንግዳቸውን እንዲያቀላጥፉ የረዳቻቸው፡፡

እስከቅርብ ጊዜ ድረስ እንጀራ እየጋገሩ ይተዳደሩ የነበሩት ወ/ሮ መብራት፤ የበለጠ ለመሻሻል ሲሉ የንግድ መስካቸውን ቀይረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም ብዙ ሰው እንደ ትንሽ የሥራ መስክ አድርጎ የሚቆጥረው የሻሜታ ንግድ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡ ሥራው አዋጭ መሆኑንም ይናገራሉ፡፡ በዝናብ ወቅት እንደሌላው ቀን ባይሸጥም ጥሩ የንግድ መስክ እንደሆነ ይመሰክራሉ፡፡

አንዳንድ ሰዎች ትንሽ ነው ብለው የሚንቁትን ሥራ እሳቸው “የሥራ ትንሽ የለውም” ብለው ከመሰማራት ወደ ኋላ አይሉም፡፡

“አንድ ሰው በንግድ ሲሰማራ ሊከስር ወይም ሊያተርፍ ይችላል፡፡ ከስሬያለሁ ብሎ ሥራውን ማቋረጥ የለበትም፡፡ አትርፌያለሁ ብሎም ብዙ ሊኩራራ አይገባም፡፡ ሥራ ሠርቶ ትልቅ ደረጃ ደርሶም ወደ ኋላ መመለስ አለ፡፡ በዚያን ጊዜ ሌላ ሥራ ቀይሮ መሞከር አለበት እንጂ ሥራን ማቋረጥ ተገቢ አይደለም” የሚል ምክረ ሀሳብ አላቸው፡፡

አክለውም፣ ብዙ ሴቶች ባለቤቶቻቸው ሲሞቱባቸው ተስፋ ይቆርጣሉ፡፡ እኔ ግን ለእነኚህ ዓይነት ሴቶች የምመክረው ነገር አለኝ፡-

“ባል ሞተ ማለት ቤተሰብ በሙሉ ጠፋ ማለት አይደለም፡፡ የቤተሰቡን ኃላፊነት ተሸክሞ መወጣት ይቻላል፡፡ ስለዚህ ጥሩ አርአያ ለመሆን በርትተው ልጆቻቸው የሟች አባታቸውን ስም እስኪያስጠሩ ድረስ ለወግ ማዕረግ ሊያበቁ ይገባቸዋል እንጂ ደካማ ሊሆኑ አይገባም፡፡

“ማንኛውም ሰው ሥራን መምረጥ የለበትም፡፡ ሴቶች የተገኘውን ሥራ ጠንቅቀው መሥራት አለባቸው፡፡ ይህን ሥራ አላውቅም ከማለት ይልቅ ሁሉንም መሞከር ጥሩ ነው፡፡ ሴቶች ለመለወጥ መቆጠብ አለባቸው፡፡

“ሴቶች አብረው ሲሰባሰቡ የሚወያዩበትም ጉዳይ አለ፡፡ አንዳቸው የሌላቸውን ጓዳ የመሸፈንና የመረዳዳት ባህል አለ፡፡ ስለዚህ ሁሉም ተደራጅተው፣ አቅም ለሌላቸው ገንዘብ አሰባስበው በመስጠት፣ አሊያም ጉሊት ቸርችረው ቆጥበው ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ ይችላሉ፡፡” ብለዋል፡፡

ወ/ሮ መብራት ሴቶች ስኬቶቻቸውን አደባባይ ማውጣት እንዳለባቸው ያምናሉ። ለዚህ ምክንያታቸው ደግሞ ሌሎች ሰዎች ከእነሱ ብዙ ሊማሩ ይችላሉ በሚል ነው። ከዚህ አንጻር እርሳቸው ባሉበት ቀበሌ ለመገናኛ ብዙሃን ያላቸውን ልምድ በማካፈል አንቱ የተባሉ እንደሆኑም ይገልጻሉ፡፡ ሴቶችንና ህጻናትን በሚመለከቱ ጉዳዮች ሀሳብ በመስጠት በኩልም የተዋጣላቸው ናቸው፡፡

ወ/ሮ መብራት ወደ አራት የሚሆን ዕድር በሥራቸው ይመራሉ፡፡ በአብዛኛው ዕድር ትኩረት የሚያደርገው ለቅሶ ላይ ማስተዛዘን ቢሆንም የእርሳቸው ዕድር ግን የታመሙትንና የተጎዱትን በሕብረት እንደሚረዳ ይናገራሉ፡፡

ወ/ሮ መብራት፡- “ኢትዮጵያዊያን ተባብሮ መኖር፣ የተራበን ማጉረስና መርዳት ልማዳችን ነው፡፡ ይህንን ሰናይ ምግባራችንን አጠናክረን መቀጠል አለብን፡፡ ያለችን አንድ ሀገር ኢትዮጵያ የሁላችን መጠጊያ ናት። ስለሆነም መገፋፋት የኋላ ኋላ አቅመ ደካሞችን፣ ሴቶችንና ህጻናትን የሚጎዳ ስለሆነ በፍቅር እንኑር” የሚል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡