በሚዛን አማን ከተማ እየጨመረ የመጣውን የወባ በሽታ ለመከላከል ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለፀ

በሚዛን አማን ከተማ እየጨመረ የመጣውን የወባ በሽታ ለመከላከል ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለፀ

ሀዋሳ፡ ሰኔ 01/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) በሚዛን አማን ከተማ እየጨመረ የመጣውን የወባ በሽታ ለመከላከል ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ የከተማ አስተዳደሩ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ገልጿል።

በመጪዎቹ ክረምት ወራት በከተማዋ ሊከሰት የሚችለውን የወባ ወረርሽኝ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል የንቅናቄ መድረክ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

በንቅናቄ መድረኩ ላይ በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈውበታል።

የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ግርማዬ ቤርሙስ እንደተናገሩት፤ በወረዳው የወባ በሽታ ስርጭት በስፋት እየተስፋፋና ለማህበረሰቡም ጤና ስጋት እየሆነ መጥቷል።

በከተማው በወባ የመያዝ መጠኑ ከ56 በመቶ በላይ መድረሱን አመላክተዋል።

በተለይ ክረምት ወራትን ተከትሎ የወባ በሽታ ይበልጥ የሚጨምር በመሆኑ ለመራቢያነት የሚያገለግሉና በሽታው ይበልጥ እንዲስፋፋ ምቹ ሁኔታዎች የሚፈጠሩ ስፍራዎችን ቀድሞ ለመከላከል እንዲቻል የንቅናቄ መድረኩ አስፈላጊ ነው ብለዋል።

የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ በላቸው ጎንደር በበኩላቸው ህብረተሰቡ እየጨመረ የመጣውን የወባ በሽታ በመከላከል በኩል የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች የአልጋ አጎበር አጠቃቀም ባህል ማዳበርና የመከላከያ ዘዴዎች ላይ በቁርጠኝነት መስራት እንዳለባቸው አንስተው የወባ በሽታን ለመከላከል ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ይበልጥ በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በንቅናቄ መድረኩ የከተማ አስተዳደሩ አመራርና ባለሙያዎች የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችና የትምህርት ቤት ርዕሰ መምህራንና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

ዘጋቢ፡ ጦያር ይማም – ከሚዛን ጣቢያችን