“ገዳዩ ኬሚካል”

በደረሰ አስፋው

የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው ትንባሆ በየዓመቱ የ8 ሚሊየን ሰዎችን ሕይወት እንደሚቀጥፍ ነው፡፡ ከነዚህ መካከል 900 ሺው ቀጥተኛ አጫሾች አይደሉም። በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2000 ሃያ ሰባት በመቶ ደርሶ የነበረው የአጫሾች ቁጥር በ2016 ወደ 20 በመቶ ዝቅ ብሏል፡፡ ይህ ትልቅ ለውጥ ነው ያለው ድርጅቱ፤ አሁንም ቢሆን የዓለም አቀፍ ስምምነት ከተደረሰበት ቁጥር ላይ ለመድረስ ብዙ ስራዎች እንደሚቀሩ ነው ያስገነዘበው።

ባለፉት 30 ዓመታት ሲጋራ በጤና ላይ ስለሚያደርሰው ጉዳት ብዙ ጥናቶች ይፋ ተደርገዋል፡፡ ሰዎችም ጉዳቱን በመገንዘብ ጥንቃቄ ማድረግ ጀምረዋል። ብዙ ሃገራት ህዝብ በተሰበሰበባቸው ቦታዎች ሲጋራ ማጨስ የሚከለክሉ ህጎችን እንዲያወጡ አስገድዷቸዋል። ዓለማችን ካጋጠሟት ወረርሽኞች ሁሉ ትልቁ ትምባሆ ነው በማለት የዓለም ጤና ድርጅትም በማሳሰብ ላይ ይገኛል፡፡ የትምባሆ አምራች ድርጅቶች ላይም ከበድ ያለ ግብር እንዲጣልባቸው ሃሳብ አቅርቧል።

በሩሲያ በየዕለቱ በአማካኝ እያንዳንዱ ሩሲያዊ 17 ሲጋራ እንደሚያጨስ የአገሪቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ይፋ አድርጎ ነበር። በዓለም ትንባሆን በከፍተኛ ደረጃ ከሚጠቀሙ ሀገራት ግንባር ቀደም በተባለችዉ ሩሲያ ማጨስ ለበርካቶች የጤና ችግር ምክንያትና ያለዉንም ህመም በማባባስ ለሞት የሚዳርግ እንደሆነ ይጠቀሳል። የትንባሆ ቸብቻቢ ነጋዴዎችም የ400 ሺህ ሩሲያዎችን ነፍስ የእነሱን ገቢ ለማስጠበቅ ባሪያ አድርገዋል ሲል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በምሬት መናገሩን የጀርመን የዜና ወኪል ዘግቧል።

አሁን የሚታየዉ በትንባሆ መዘዝ የሚከሰተዉ የጤና እክል ተባብሶ ከቀጠለም ከአዉሮፓዉያኑ አቆጣጠር ከ2030 ዓ,ም ጀምሮ በየዓመቱ የሚያልቀዉ ሰዉ ብዛት ከስምንት ሚሊዮን እንደሚልቅ ነው። በ21ኛዉ ክፍለ ዘመን የሰዉ ልጅ ሊቆጣጠረዉ በሚችል እክል ይህን ያህል ሰዉ በየዓመቱ እንደዋዛ ህይወቱ ማለፉ ያሳሰበዉ ተመድ ከአምስት ዓመታት በፊት ሀገራት የትንባሆ ተጠቃሚዎችን ቁጥር የሚቀንሱበትን መንገድ እንዲቀይሱ በማሳሰብ ላይ ይገኛል፡፡

ዓለም የጤና ድርጅት ትንባሆ ላይ ቁጥጥር እንዲደረግ የተደረሰውን ስምምነት ብዙ ሃገራት ተቀብለውታል። ኢትዮጵያም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ተመሳሳይ ድንጋጌ አውጥታለች። በአተገባበሩ የታሰበውን አሳክቷል ለማለት ባያስደፍርም፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት በ135 ሃገራት ላይ ጥናት አካሂዶ ነበር፡፡ ከነዚህም ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ናት፡፡ የጥናቱ ግኝት ከጎረቤት ኬንያ 26%፣ ከቻይና 29% አንዲሁም ከአሜሪካ 23% ጋር ሲነጻጸር በኢትዮጵያ የአጫሾች ቁጥር አነስተኛ የሚባል ነው፡፡ ይህ አሀዝ ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተቀየረ ይገኛል፡፡ የአጫሾች ቁጥር እያሻቀበ መሄዱ ነው የሚታየው። ከማጨስ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ ካንሰርና ሌሎች የመተንፈሻ አካላት ህመሞችም እየጨመሩ ይገኛል፡፡ በሕዝብ መሰባሰቢያ ሥፍራዎች ሲጋራ እንዳይጨስ የሚከለክል አዋጅ ቢጸድቅም ከመቀሌና አዲስ አበባ በቀር የረባ ለውጥ አልታየም፡፡

በደቡብ ክልል ያለውን ሁኔታ ስንመለከትም ተመሳሳይ ችግር ያለበት ነው፡፡ ባለማጨሰዎ እናመሰግናለን! አለያም ማጨስ ክልክል ነው! የሚሉ ማባበያዎችና ትዕዛዞች በየቦታው ተለጣጥፈው ቢታዩም ገቢራዊነቱ ግን ያን ያህል ነው፡፡ ጉዳዩን አስመልክተን የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ የሚመለከተውን አካል አነጋግረናል፡፡ ከዓለም አቀፍ ነበራዊ ሁኔታ ጋር በማነጻጸር፣ ትንባሆ ማጨስ የሚያስከትለው የጤና፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስና በሀገርም ይሁን በክልል እየተወሰዱ ባሉ እርምጃዎች ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

አቶ ወልደሰንበት ሸዋለም የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ የጤና እና ጤና ነክ ግብአት ቁጥጥር ባለስልጣን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ናቸው። ትንባሆ እንደማንኛውም እጽዋት ተክል ሲሆን በተለያዩ ዘዴዎች ሊወሰድ እንደሚችል ያስረዳሉ፡፡ ሰዎች ደስታ ለማግኘት ሲሉ ቢወስዱትም በጤና ላይ ግን ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያስከትል ነው የሚገልጹት፡፡ ወደ ሱስነት በማደግ በሚያስከትለው ድብርት ወይም ጭንቀት ከፍ ያለ ቁጥሩ ትንባሆ ለመውሰድ ይገደዳሉ፡፡ ይህም ለጤና መታወክ ተጋላጭነቱን ያሳድገዋል አልፎም ኢኮኖሚያዊ ጫናን ያሳድራል ብለዋል፡፡

በትንባሆ ውስጥ ከ4 ሺህ እስከ 7 ሺህ የሚደርስሱ ኬሚካሎች ይገኛሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ ወደ 450 የሚሆኑት ለጤና ጎጂ ናቸው ይላሉ፡፡ ወደ 69 የሚደርሱት ደግሞ ካንሰርን ሊያስከትሉ የሚችሉ ኬሚካሎች እንደሆኑ ነው የሚገልጹት፡፡ በዓለም በገዳይነቱ በግንባር ቀደምትነት የሚታወቀው በሽታ ደግሞ በቂ የሆነ የካንሰር ህክምና በሌለበት ሀገር ከጤና መታወክ ባሻገር የማህበራዊ ቀውሱ ከፍተኛ ነው ባይ ናቸው፡፡

ነፍሰ ጡር ሴቶች በእርግዝና ጊዜ ትንባሆ ካጨሱ በራሳቸውም ሆነ ልጆቻቸውን ሊመርዙ ይችላሉ፡፡ ፅንሱ ሊሞት፣ አለ ቀኑ ሊወለድና ክብደቱ በጣም አነስተኛ ሊሆን ይችላል ብለዋል። በአመት ከ65 ሺህ በላይ ህጻናት የችግሩ ሰለባ እንደሚሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ ብለዋል፡፡ ትንባሆ ማጨስ በባዮሎጂያዊ ባሕርዩ ልዩ በመሆኑ ምክንያት በመርዛማ ነገሮች በቀላሉ ሊጎዳ በሚችለው የሴት አካል ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያስከትልም አስገንዝበዋል፡፡

በጣም አስደንጋጭ የሆነው እና በምርምር ሊረጋገጥ እንደተቻለው በእርግዝና ወቅት የሚያጨሱ እናቶች የእትብት ቅርጽ የተበላሸ መሆኑ ነው። ፅንሱ የሚያስፈልገውን ሁሉ ከእናቱ ማኅጸን የሚያገኘው ደግሞ በእትብት በኩል ነው። እናቲቱ በፀነሰች ከሁለት እስከ ሦስት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ትንባሆ ብታጨስ ከሁሉም በላይ የሚጎዳው የፅንሱ የማዕከላዊ ነርቭ አውታር ነው። በአራተኛው ወይም በአምስተኛው የእርግዝና ሳምንት የልብና የደም ዝውውር አውታር ይዳብራል። በዚህ ጊዜ የሚመረዘው ደግሞ ይህ ክፍል ይሆናል። ስለዚህ ትንባሆን ከማጨስ ሊታቀቡ ይገባል ሲሉ ምክራቸውን ሰጥተዋል፡፡

በዓለም 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ሰዎች ትንባሆ ተጠቃሚዎች እንዳሉ ያስታወቁት ዳይሬክተሩ ከነነዚህ ውስጥ ከ7 እስከ 8 ሚሊዮን የሚሆኑት ለሞት እንደሚዳረጉ ነው፡፡ 80 በመቶ የሚሆኑትም በዝቅተኛ ኑሮ ውስጥ በሚገኙት ከሰሃራ በታች በሚገኙ በታዳጊ የአፍሪካ ሀገራት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በ2006 ዓ.ም በተደረገው ጥናት በኢትዮጵያም 3 ነጥብ 4 አጫሾች እንደሚገኙ ነው። የጥናቱ ውጤት እንደሚያሳየውም ወደ 17 ሺህ የሚሆኑት ከዚሁ ጋር በተያያዘ በየዓመቱ ለህልፈት እንደሚዳረጉ ነው አቶ ወልደሰንበት የጠቆሙት፡፡ ከዓለም አቀፉ የጤና ድረጅት መረጃ አኳያ የአጫሾች ቁጥር ከሌሎች ሀገራት ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ ቢሆንም ቀዉሱ ግን ከፍተኛ ነው ሲሉ ነው አቶ ወልደሰንበት የገለጹት፡፡

የትንባሆ አጫሾች ቁጥር ሲጨምር ተያይዞ የካንሰር ህመምተኞችም ይጨምራል ያሉት ዳይሬክተሩ በሀገር ላይ የሚያመጣው ጉዳት ከፍተኛ ነው፡፡ ለትንባሆ የሚያወጡትም ወጪ ከጊዜ ወደ ጊዜ በማደጉ የሰዎችን የኑሮ ሁኔታ ይቃወሳል፡፡ ከታክስ ህጉ ጋር ተያይዞ ዋጋው እያሻቀበ የሚገኝ በመሆኑ፡፡ አብዛኛው አጫሾች ወጣትና አምራች ሀይሉ ጤንነታቸው በመታወኩ ለሀገር ማበርከት የሚገባቸውን ሳይወጡ ለከፋ ችግሩ ተጋላጭ ይሆናሉ፡፡

ችግሩ አሳሳቢ ነው ያሉት አቶ ወልደሰንበት በሀገር ደረጃ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛል፡፡ 181 ሀገራት የተስማሙበትን ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽኖችን መሰረት በማድረግ ኢትዮጵያም ስምምነቱን ተቀብላ በተወካዮች ምክር ቤት በአዋጅ 822/2006 የህዝብ ተወካዮች አጽድቃ በስራ ላይ አውላለች። በዚህም በትንባሆ ምርቶች ላይ ታክስን በመጨመርና ቁጥጥር በማድረግ አቅርቦትን መቀነስ፣ ህገ-ወጥ ምርቶች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ በማድረግ ትንባሆ በሀገር የሚያደርሰውን ችግር ለመቀነስ እየተሰራ እንደሆነ ነው የገለጹት፡፡

ችግሩ ሀገርንም የከፋ ጉዳት ላይ የሚጥል መሆኑን የተገነዘበው የኢትዮጵያ መንግስትም የቀድሞውን አዋጅ የሚያጠናክር አዋጅ 1112/2011 በኢፌድሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቆ በስራ ላይ እንዲውል ተደርጓል። የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን ከአዋጁ ጋር በተያያዘ ከግንቦት ወር 2011 ዓ.ም ጀምሮ ትንባሆ በመገናኛ ብዙሃን ጭምር እንዳይተዋወቅ እገዳ እንደተደረገም ነው የገለጹት፡፡ ህዝብ በስፋት በሚገኝባቸው ትምህርት ቤቶች፣ መዝናኛ አካባቢዎች፣ የመንግስትም ሆነ የግል መስሪያ ቤቶች፣ መናኸሪያዎች፣ የወጣት ማዕከላት፣ ኮሌጆችና ዩኒቨርስቲዎች፣ እስከ 10 ሜትር ድረስ ባለው ርቀት ሙሉ ለሙሉ ማጨስ የተከለከለባቸው አካባቢዎች እንደሆኑ ህጉ ያስረዳል፡፡

የፀረ ትንባሆ ቀን በኢትዮጵያም ሆነ በዓለም በየአመቱ ግንቦት 23 መከበር አጫሾችም ሆነ ሌሎች የህበረተሰብ ክፍሎች ስለትንባሆ የጤና ጠንቅ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ያስችላል። የዓለም የጤና ድርጅት የትንባሆ ኮንቬንሽን ስምምነት ሲወጣ እና ሀገራት ሲፈራረሙ ከተካተተው ውስጥ ቀኑን በማክበር የህዝቡን ግንዛቤ መፍጠር እንደሚገባ በመስማማት ነው፡፡ በዚህም እሰካሁን በተሰራው ስራ ለውጦች እየመጡ እንደሆነ ነው አቶ ወንደሰን የተናገሩት፡፡

የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ትኩረት አድርጎ የሚሰራባቸው አካባቢዎች አሉ፡፡ ጥናትን መሰረት በማድረግ በክልሉ 4 ከተሞች አርባ ምንጭ፣ ወላይታ ሶዶ፣ ሀላባ እና ሆሳዕና ላይ እየተሰራ ነው። በተሰራው ስራም 65 በመቶ መሻሻል ታይቷል ብለዋል፡፡ አሁንም ቢሆን የትንባሆ ማጨስ በማህበረሰቡ ብሎም በሀገር ላይ የሚያመጣው ተጽእኖ ከፍተኛ በመሆኑ ግንዛቤ የመፍጠሩ ሁኔታ የሚገታ አይደለም፡፡

የአዋጁ ተሻሽሎ መውጣት ለጉዳዩ ትኩረት ከመሰጠቱ የመነጨ ነው፡፡ በክልሉም አዋጁን በህግ ተግባራዊ ለማድረግ በህግ ባለሙያ ጥናት ተደርጎ ግብረ ሀይል ተቋቁሞ ችግሩን እልባት ለመስጠት እየተሰራ እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡ የክልሉ ምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን፣ የክልሉ ፍትህ አካላት፣ በክልሉ ተዋቀረው ግብረ ሀይል፡- የአካባቢ ጥበቃ፣ ፖሊስ፣ ንግድና ገበያ ልማት፣ ሠላምና ፀጥታ ባሉበት የተዘጋጀ ሲሆን የክልሉ ምክር ቤትም በአዋጅ እንዲያጸድቀው እየተጠበቀ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ከሚወሰዱ እርምጃዎች ምርቱ በአካባቢዎች እንዳይመረት ነው፡፡ በዚህም በክልሉ ሁለት አካባቢዎች በ550 ሄክታር መሬት ላይ ትንባሆ በማምረት የተሰማሩ ኢንቨስተሮች መኖራቸውን ጠቁመዋል። ይህንንም በሌላ ምርት በመተካት የማህበረሰቡን የጤና ችግር መቅረፍ ይገባል። አስተዳደራዊ እና ህጋዊ እርምጃ ከመውሰድ ቅድሚያ ግንዛቤ የመፍጠር ስራው ይቀድማል፡፡ ለዚህም መገናኛ ብዙሃንን ጭምር በመጠቀም ጉዳቱን የማስገንዘብ ስራ እየተሰራም እንደሆነ ተናግረዋል። ለቁጥጥሩም ከክልል እስከ ወረዳ የደንብ አስከባሪዎችንም እየተጠቀሙ እንደሚገኝ አቶ ወልደሰንበት ተናግረዋል፡፡