የጣልነው መክሊት አለ

የጣልነው መክሊት አለ

በአዲስሰው ተወልደ

ምዕራፍ በቅርበት የማውቀው ወዳጄ ነው። በአንድ ወቅት አብረን ክፉውንም ደጉንም አሳልፈናል። ብዙዎች በቁልምጫ ስሙ “ማፊ” ብለው ይጠሩታል። በሀያዎቹ መጨረሻ ዕድሜ ላይ የሚገኝ ወጣት ነው።

እሱን ላስተዋውቃችሁ አይደለም የጽሁፌ መነሻ። ይልቅስ ዛሬ ላነሳ ካሰብኩት ሃሳብ ጋር የተያያዘ ታሪክ ስላለው እንጂ። ለነገሩ ከእርሱ ጋር ባሳለፍኳቸው ጊዜያት ምዕራፍን በተለየ መልኩ አይቼው አላውቅም ነበር። አንድ ቀን ግን የሆነ ነገር አነቃኝ። ነገሩ እንዲህ ነው:-

ከምዕራፍ ጋር ሁለታችንም በራሳችን ስራ በመያዛችን እንደበፊቱ ቀን በቀን ተገናኝተን ማውጋታችንን አቁመን ነበር። አንድ ቀን እናዘወትርበት በነበረው ሆቴል ለመገናኘት ቀጠሮ ያዝን። በቀጠሯችን መሰረት ቀድሜ ተገኘሁና ትኩስ ነገር አዝዤ እየጠጣሁ እጠብቀው ጀመር።

የቀጠሯችንን ሰዓት ሳይሸራርፍ ብቅ አለ። የማውቀው ራሱ ቢሆንም ብዙ ነገሩ ተቀይሯል። ከሆቴሉ በራፍ ጀምሮ እስከተቀመጥኩበት ስፍራ እስኪደርስ ድረስ ዓይኔን ሳልነቅል በአንክሮ ተመለከትኩት። አረማመዱ፣ አለባበሱ፣ ተገናኝተን ስንጨዋወትም ንግግሩ የማላውቀው ምዕራፍ ሆነብኝ።

ፀጉሩን ያለወትሮ አጎፍሮ ቡናማ ቀለም ተቀብቷል። ጺሙን ፊቱን እስኪሸፍነው ድረስ አሳድጎ በወጉ አበጥሮታል። እጅጌ ጉርድ ረጅም ቲሸርት ከላይ ለብሷል። ከታች የውጭ የራፕ ሙዚቃ አቀንቃኞች እንደሚለብሱት አይነት ሰፊ ጂንስ ሱሪ አጥልቋል። የጫማው ግዝፈት ደግሞ አይጣል ነው።

በዚህ አላበቃም፤ በተፈጥሮ ቀይ ተብሎ በሚጠራው ቆዳው ላይ በተለይም ግራና ቀኝ እጆቹ በንቅሳት ተዥጎድጉደዋል። ጆሮው ላይ ገመድ አልባ ማዳመጫ ጣል አድርጎ የሚሰማውን ሙዚቃ እየተከተለ ያነበንባል። ጭራሽ ማውራት ሲጀምር በቀላሉ ከሚያግባባን አማርኛ ይልቅ እንግሊዘኛ ቃላትን መቀላቀሉ የተለየ ግርምትን ጫረብኝ።

ከዚህ በፊት ምዕራፍን ሳውቀው እንዲህ አልነበረም። አለባበሱ፣ አረማመዱም ሆነ ንግግሩ እንደ ማንኛውም ጨዋ ኢትዮጵያዊ ስክነት የተሞላው ነበር። በእርግጥ ድሮም ቢሆን የውጪ ሙዚቃ መስማትና ፊልም ማየትን ያዘወትራል። ወደ ውጭ ሀገር ለመሄድ ካለው ፍላጎት አኳያ ከሀገር ለመሰደድ ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም አልተሳካለትም እንጂ።

ይሁን እንጂ በጊዜ ሂደት ጭራሽ ኢትዮጵያዊነቱን እስኪረሳ ድረስ የማንነት ቀውስ ይገጥመዋል ብዬ አስቤ አላውቅም። ስንጨዋወትም የሚያወራው ሁሉ ስለማያውቀው ስለነጮቹ አኗኗር ዘይቤ ነው። እንደ አወራሩ የሚመስለው ውጪ ሀገር ለዓመታት ከርሞ ለእረፍት ሀገር ቤት የመጣ ዳያስፖራ ነው። በምን ስራ ላይ እንደሚገኝ ጠየኩት። በፊት ይሰራ የነበረውን የጋራዥ ስራ እንዳልተወ ነገረኝ።

አሁን መገረሜ ጨመረ። “ታዲያ ምንድነው ይህ ሁሉ ለውጥ” አልኩት። “ያው መኖር ምመኘውን ስታይል እየኖርኩ ነው በቃ” አለኝ። ይሄኔ እኔም በምናቤ መነጎዴ አልቀረም። በአዕምሮዬ ብዙ ሃሳቦች ይመላለሱ ጀመር። “በዚህ ወቅት ስንት ምዕራፎች ይኖሩ ይሆን?” ራሴን ጠየኩ?

ይኸው ነው ዛሬ ማንሳት የፈለኩት ሃሳቤ። አዎ! ስንት ምዕራፎች ከሀገራቸው ባህል እና እሴት አፈንግጠው ራሳቸውን ዘመናዊነት በሚል ማታለያ አስተሳሰብ ሸብበው በምናብ ከሀገር ተሰደዋል? አያሌ ናቸው።

ስንቶች ናቸው ኢትዮጵያዊ የሚባል ማንነት የሌለ ይመስል በምዕራባዊያን አስተሳሰብ ተጠፍንገው ከማህበረሰቡ ጋር በፍቅር መኖር የተሳናቸው? ቤት ይቁጠራቸው።

አሁንማ ዘመናዊነት የምዕራባዊያኑን አለባበስና አኗኗር መኖር ነው የተባለ እስኪመስል ድረስ ብዙ ነገራችን ተቀያይሯል። ከምንለብሳቸው አልባሳት ጀምሮ የኑሮ ዘይቤያችን ሁሉ የምዕራባዊያን ከሆነ ሰነባብቷል። በእርግጥ መልካሙን ነገር ወርሶ ለሀገር በሚጠቅም መልኩ ጥቅም ላይ ማዋሉ ባልከፋ። የአብዛኞቻችን ግን ከዚህ ለየቅል ነው።

አብዛኛውን የሰውነት ክፍላችንን፣ አንዳንድ ጊዜም ሃፍረተ ስጋችንን በማይሸፍን መልኩ አካላችንን አደባባይ የሚያሰጣ አለባበስ አሁን አሁን በስፋት ይታያል። ይሄ በአብዛኛው በሴቶች ዘንድ ይስተዋላል። በወንዶች ደግሞ ጥቁር አሜሪካዊያኑ የሚያዘወትሩት ከላይ እስከታች እንደ በርሜል የሰፋ ልብስ፣ አሊያም ደግሞ በተቃራኒው ሰውነትን ውጥር የሚያደርግ ቃሪያ የሚባለው አለባበስ ማዘውተሩም ተመራጭ የሆነ ይመስላል።

ከሁሉም ቅር የሚያሰኘኝ ህጻን አዋቂው ፈጣሪ ውብ አድርጎ የሰራው የቆዳ ቀለሙ ላይ የሚሳለው ስዕል ወይም ንቅሳት ነው። አንዳንዶች ከአንገታቸው ጀምሮ መላው የሰውነት ክፍላቸውን በዚህ ንቅሳት(tatoo) ይሸፍኑታል። ንቅሳቱ ሰውነታቸውን የሚሸፍን ከሆነ፣ ታዲያ ልብስ መልበሱ ለምን አስፈለገ? አሁንማ ፋሽን ነው የሚመስለው።

ሌላው የታዘብኩት የቀንና የተለያዩ ሁነቶች አከባበር ነው። በእርግጥ ከእነርሱ ከተዋስናቸው የእናቶች፣ የአባቶችና ሌሎች ማህበራዊ መስተጋብሮቻችንን የሚያጠናክሩ ቀኖችና በዓላትን ማክበራችን ቢያስመሰግን እንጂ አያስነቅፍም።

ከዚህ አለፍ ሲል ከባዕድ አምልኮ ጋር የተያያዘው ሃሎዊን ቀን(halloween day) በተለይም የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ በሚመረትባቸው የግል ት/ቤቶች በየዓመቱ መከበሩ በእጅጉ የሚያሳዝን ነው።

እኛ ኢትዮጵያዊያን እኮ የየራሳችንን እምነት የምንከተል ፈርሃ እግዚአብሄር ያለን ህዝቦች ነን። እንዴት የትውልድን እድገት በአጭሩ የሚያስቀር ሰይጣናዊ በዓል በት/ ቤቶቻችን እንዲከበር እንፈቅዳለን? ፍርዱን እናንተው ስጡት። ለማንኛውም ሌሎች የእብደት እና ከኢትዮጵያዊ ስነምግባር ያፈነገጡ ቀኖችን ማክበርም የዘመናዊነት ጥግ አድርገን እየተመለከትን ነው።

ሴቶች ደግሞ የሙሽራነት(bridal show­er) እንዲሁም የወሊድ(baby shower) ቀን አከባበር እያሉ እርቃናቸውን እርግዝናቸውን የሚያሳይ ፎቶ እየተነሱ በየማህበራዊ ሚዲያው መለጠፍን ተያይዘውታል። ይህ ለተመልካች ምን ትርጉም እንደሚሰጥ የገባቸውም አይመስለኝም። አንዲት ታዋቂ የውጭ ዘፋኝ ወይም ተዋናይት ይህን ስላደረገች ብቻ ማድረጉ በአስተሳሰብ ምን ያህል ወደ ኃላ እንደቀረን የሚያሳብቅ ነው።

ሌላው ምዕራባዊያን ያመጡብን ጣጣ ብዬ የማስበው ክብረ ነክ የሆኑ ጉዳዮች ናቸው። አሁን አሁን ከጋብቻ በፊት ሩካቤ ስጋ መፈጸም እንደ ብዙዎች ንግግር “ኖርማል” እየሆነ መጥቷል።

ታዳጊዎች ገና ለአቅመ አዳምና ሄዋን ሳይደርሱ ግንኙነት ይፈጽማሉ፤ ገና በት/ቤት እያሉ በሆሊዉድ ፊልሞች የሚመለከቷቸውንአስነዋሪ ድርጊቶች እየፈጸሙ ያድጋሉ። ከዚያ ጋብቻ ከፈጸሙ በኋላ ከትዳር አጋራቸው ጋር ሳይስማሙ ይቀሩና ለፍቺ ይበቃሉ። ፍቺውንም ቢሆን ጋብቻው እንደ ቤተ ሙከራ አይጥ በጊዜያዊነት ስለሚታይ በአንድ ጀንበር ለመፈጸም ብዙም አይከብድም።

ብቻ እኔ ጥቂቱን አነሳሁኝ እንጂ ውድ አንባቢዎቼ ይህን ጽሁፌን ስታነቡ እናንተም ብዙ ማህበረሰባችን ከምዕራባዊያኑ የወረሳቸው ያልተገቡ መጤ ባህሎችን እግረ መንገዳችሁን በአዕምሯችሁ እንደምታሰላስሉ ጥርጥር የለውም። ከቁጥር በላይ ናቸው።

ለዚህም ይመስለኛል ዛሬ ላይ ድህነት በትሩን እያሳረፈ የሚያንገላታን። የእኛን እያረከስን፣ እንደ አላዋቂነት እየቆጠርን አሽቀንጥረን መጣላችን ብዙ ዋጋ አስከፍሎናል። ይህ የሆነው ደግሞ ኢትዮጵያዊነት ባህል፣ እሴትና ማንነታችን ምን እንደሆነ በቅጡ ባለማወቃችን ነው።

አባቶቻችን እኮ ለሀገራችን ክብር የተዋደቁት ሁለንተናዊ የራሳችንን ማንነት አውርሰውን፣ በአንጻሩ የውጪውን ወራሪ ባህል አሻፈረኝ ብለው ነው። ኢትዮጵያዊነት ከአለባበስ ጀምሮ የራሱ የአኗኗር ዘይቤ ያለው ድንቅ ቀለም ነበር። የውጪውም የሚወረሰው ደግ ደጉ እንጂ የራስን የሚያስጥለው አልነበረም።

ልጅ በወጉ ተቀጥቶ፣ መልካም ስነምግባርን ተላብሶ ያድጋል። በምግባሩ ያፈነገጠ ቢኖር እንኳን ጎረቤት እየመከረውና እየዘከረው መስመር እንዲይዝ ይደረጋል። ከወላጅ ትዕዛዝ ማፈንገጥ ነውር ነው። ወጣቶችም ለአቅመ አዳምና ሄዋን ቢደርሱም እንኳን በአደባባይ አይታዩም።

መቼም ፍቅር ተፈጥሯዊ ነውና አንድ ወጣት የፍቅር ግንኙነት ከጀመረና ግንኙነቱ እያደገ ከሄደ በአግባቡ በኢትዮጵያዊ ባህል መሰረት ለፍቅረኛው ቤተሰብ ሽምግልና ይልካል። ሽምግልናው የፈጀውን ጊዜ ከፈጀ በኋላ ይጋባሉ።

እንደ ተጋቡም ሙሽሪት ክብረ ንጽህናዋን ጠብቃ እንደ ምትቆይ ስለሚታመን የጫጉላ ምሽት በጉጉት ይጠበቃል። በአብዛኛው በጫጉላ መልካም ዜና የሚሰማበት በመሆኑ “ብር አንባር ሰበረልዎ…” ተብሎ ይዜማል። አንዴ ወደ ትዳር ዓለም ከገቡ በኋላ ተቻችሎ መኖር ነው እንጂ ፍቺ መፈጸም በፍጹም በማህበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት የለውም።  ይሄ ነው ኢትዮጵያዊ ባህል፤ ኢትዮጵያዊ ማንነት። ዛሬ ላይ ግን ይህ መልክ ተቀይሯል። ብዙ ነገሮቻችን ተበራርዟል። ስልጣኔ መስሎን የተከተልነው የምዕራባዊያኑ የአኗኗር ዘይቤ ኢትዮጵያዊ መልካችንን አጥፍቶታል። ጉዟችንን የኋሊት አድርጎብናል።

ከሁሉም የሚከፋው የራሳችንን ትተን የሌሎቹን ስንከተል ኑሯችን የምናብ እንጂ የእውነት አለመሆኑ ነው። ምዕራባዊያኑ እኮ የስልጣኔን ጣሪያ የነኩ ስለሚመስላቸው ነው ከሰብዓዊነት ያፈነገጠ ህይወት የሚለማመዱት። እኛ ግን ከ90 በመቶ በላይ ጠግቦ ውሎ ማደር የተሳነው ሕብረተሰብ አካል ሆነን፣ ውጪዎቹን ለመሆን መንጠራራት በሁለት ዛፍ ላይ በአንዴ ለመውጣት የመሞከር ያህል ቅብጠት ነው።

ስለዚህ ወደ ረሳነው፣ ግን ደግሞ ወደሚያዋጣን የራሳችን ወደ ሆነው የቀድሞ ማንነታችን እንመለስ። ከኋላ እንጀምርና ወደ ፊት ለመጓዝ እንጣር። ያኔ የጣልነው ሁሉ ወደ ከፍታው ይመራናል። በሌሎች ሳይሆን የራሳችን በሆነው ማንነት አዲሲቷንና የምንመኛትን ኢትዮጵያ እውን እናደርጋለን። አለበለዚያ ግን…