ጭራ ፣ አሽሙርና ቅርንጫፍ

በጌቱ ሻንቆ

እንዴት ናችሁሳ ? አለን እኛም – ጭራ የለንም እንጂ፡፡ ‘‘ለምን ጭራ የለኝም?’’ ፣ ሰው ነው ጭራ ያሳጣኝ፡፡

ያኔ ጭራ በሚታደል ዕለት ሰው ‘‘ቆይ በኋላ ሄጄ እወስዳለሁ፣ ቆይ በኋላ ….’’ ፣ እያለ ጭራዎች በሙሉ፣ ለባለጭራዎች ታድለው አለቁ፡፡

የጭራ ዕደላ እለት የመጨረሻውን ጭራ ማን እንደወሰደ ታውቃላችሁ? ፍየል፡፡ ገመና የማይሸፍን ቁንጥሎ ጭራ ወሰደች፡፡ አርፍዳ ነበር የተሰለፈችው፡፡

ከጭራዎች ሁሉ የሚገርመኝ የዝንጀሮ ጭራ ነው፡፡ የኃላ ‘‘መላጣ’’ አይሸፍንም። አናቱ የተቦደሰ ባርኔጣና የዝንጀሮ ጭራ አንድ ናቸው፡፡ የፀሐይ ጥብስ ያደርጋሉ፡፡

ግንኮ ዝንጀሮ ጭራውን ጎበብ አርጎ ይኮፈስበታል፡፡ ዝንጀሮ የሚኮፈሰው በጭንቅላቱ ሳይሆን በጭራው ነው፡፡ በተሳቢው፡፡ በአጃቢ ማለት ነው፡፡

አንዳንድ ሰዎች ገብቷቸውም ይሆን ሳይገባቸው አይገባኝም ሳቢን ሳይሆን ተሳቢን ያፈቅራሉ፡፡ ‘‘እባብ’’ የሚወድ ስንት ሰው አለ መሰላችሁ?

አንዳንድ ሰው በጎታች ሳይሆን በተጎታች ይኮፈሳል-እንደ ዝንጀሮ፡፡ ከጭራነት ባህሪ ግን ባለ ጭራነት ይሻላል፡፡

አይ ዝንጀሮ!! ከመንጠልጠል ውጪ ምን ስራ አለው? በዚህ ምክንያት ዝንጀሮ ጭራውን ዛፍ ላይ ቋጥሮ ዥዋዥዌ ይጫወትበታል። የዝንጀሮን ጭራ ትኩር ብዬ ሳየው ደግሞ ወፍራም ገመድ ይመስለኛል፡፡

በዚህ ምድር ላይ ሰው ላይ ተንጠልጥሎ ‘‘የሚጫወት’’ ስንት አለ መሰላችሁ! እንዲህ ያለው ሰው ጭንቅላቱን፣ ጭራነቱን፣ የሚጠቀምበት በሰው ላይ ተንጠልጥሎ ዥዋዥዌ ለመጫወት ነው፡፡ ምን ያድርግ ብላችሁ ነው? ብቸኛ ሙያው መንጠልጠልና ዥዋዥዌ መጫወት ነው፡፡

አይ የዝንጀሮ ጭራ! ወልጋዳ ነገር ነው። ስሩ ላይ ወደ ሰማይ አንጋጦ ስንዝር ሳይርቅ ወደ መሬት ያጎነበሰ ጭራ፡፡ ጭንቅላቱን ጭራው ወስዶበታል፡፡ ከሰማይ አልሆነ ከምድር -ዝንጀሮ፡፡ ከዛፍ የለ ከመሬት!

እንዲህም ዓይነት ሰው አለ፡፡ ወልጋዳ ሀሳብ ያለው፡፡ እርግጥ ነው ፤ ዝንጀሮ ጭራውን ይኮፈስበታል- ቢያንስ፡፡ የሰው ወልጋዳ ሀሳብ ግን ያደናቅፋል፡፡ እንዲህ ያለው ሰው የሚያጌጠው በእንቅፋት ነው። የሱ ጌጥ እንቅፋትነት ነው፡፡

ቆዩኝማ፡፡ ሰው ጭራ የሌለው የሆነው ‘‘ቆይ በኋላ እያለ ነው ….’’ ፣ ብያችሁ አልነበር፡፡ ሌላም የሚባል ነገር አለ፡፡ ጭራ በሚታደልበት ዕለት የጭራ ፈላጊዎች ሰልፍና ብዛት ጭራው አይታይም ነበር አሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ሰው፣ ‘‘ምን አሰለፈኝ ራሴ ጭራ አልሰራም!’’፣ አለና ትቶ ሄደ፡፡ የሰራው ግን የጭራ ጭራ ነው ፣ ኦርጅናል መሆኑ ቀርቶ ‘‘ሀይ ኮፒም’’ ፣ የማይባል ጭራ፣ ከፈረስ ወስዶ ፡፡

መግዛትም አስቦ ነበር – አሉ ጭራ ከደረሰው ሰው ላይ፡፡

የግዢ ነገር ደግሞ አያስተማምንም! ትርፉ ሸክምና በሽታ ነው፡፡ የግዢ እንጀራ በሽታ ሆነብን – የጨጓራ፡፡

አንድ ጊዜ፣ ‘‘ ጤና የእንጀራ መሸጫ ’’ ፣ የሚል ማስታወቂያ አነበብኩ፡፡ ምንም ያህል አልቆየም ፣ በወራት ልዩነት፣ አጠገቡ ፣ ‘‘ጤና ክሊኒክ ‘‘ የሚል ማስታወቂያ አየሁ፡፡ ቀጠለና ‘‘ጤና መድሀኒት ቤት’’ ተከፈተ፡፡ ጤና ቀብር አስፈፃሚ ቀጥሎ ይከፈታል፡፡

ሀይ ባይ በሌለበት ሀገር በቅርንጫፍ ገለው በቅርንጫፍ ይቅበሩን እንጂ፡፡ በዚሁ ከቀጠለ የቀብር ስፍራውም “ጤና የሀብታምና ድሀ ቅርንጫፍ” ተብሎ ሊሰየም ይችላል፡፡

ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስ፡፡ የጭራ እደላው እለት፡፡ ጭራ ለመቀበል የቆሙ ጭራቸው የማይታዩ ረጃጅም ሰልፎች ነበሩ ብያችሁ አልነበር፡፡ ከሰው ሌላ ጭራ ለመቀበል ዘግይቶ የመጣው አንበሳ ነበር። አንበሳ ዘግይቶ መጣና ሰልፉን ብጥብጥ አደረገው፡፡ መጋኛ ይበጥብጠው!

ሰልፉ ሲበጠበጥ ጭራ መነጣጠቅ ጭምር ነበር፡፡ እርስ በርስ በመነጣጠቁ መሀል የያዘው ጭራ የተጎመደበትም አለ፡፡ የተጎመደውን ጭራ፣ ጭራ የለሽ ሆኖ ጭር ከማለት ይሻላል አለና ወደቤቱ ይዞት ተመለሰ- ጉማሬ፡፡

ሰልፉን አንበሳ ሲረብሸው ጉንዳኖች ነበሩ፡፡ የረበሸውን፣ አንበሳን፣ ከበው መቆንጠጥ ጀመሩ፡፡ እየተቆነጠጠም አመለጠ- የዘረፈውን ሎጋና ሸበላ ጭራ፡፡ ይኸው ዛሬ ድረስ አንበሳ ጉንዳንን ባየ ጊዜ ሁሉ ጭራውን ጥሎ የሚፈረጥጠው ጭራ ዘርፎ መሮጡም ፣ መነከሱም ትዝ እያለው ነው አሉ፡፡ አሉ ነው እንግዲህ እኔ በቦታው አልነበርኩም፡፡

ጉንዳኖች አንበሳን ሲያባሩት ሰውንም፣ ‘‘ተሰለፍ ምን ትገተራለህ!’’ ፣ ብለውት ነበር።

ጦጣም የእደላው ዕለት ነበረች፡፡ ቀድማ በመሰለፏ ጥሩ ጭራ ወስዳ፣ ከወሰደች በኋላ ዛፍ ላይ ሆና ለጭራ በተሰለፉት ግርግርና ረብሻ ታላግጥ ነበር፡፡

ጉንዳኖች ፣ ‘‘ተሰለፉ ! ተሰለፉ ! …’’ ፣ እያሉ ሲጮሁ ፤ ‘‘ጭራ የሌላችሁ የጭራ አሳላፊዎች ’’ ፣ ብላ አሸሞረቻቸው፡፡

ሰው ነገረኛ አይደል! ‘‘አሽሙር ምንድነው?’’ ፣ ብሎ ጦጣን መልሶ ጠየቃት፡፡

‘‘ጉንዳን ነው !’’ ፣ ብላ መለሰችለት፡፡

‘‘አሽሙር የግራር እሾክና የመርፌ ልጅ ፣ ‘ምንትስ! ’፣ ነው’’፣ ያለችው ማን ብትሆን ጥሩ ነው፡፡ በቅሎ፡፡ ተሳቀባት! ‘‘፣ ከባለቤቱ ያወቀ ‘ምንድነው’ ’’ ፣ አለቻት -ጦጣ፡፡

የግራር እሾክና መርፌ ሲባል ሰምታ በተራዋ አትነሳም ግመል!

‘‘ምግባችን ነው!’’ ፣ አለች ሻኟዋን እየሰበቀች፡፡

አይጥም ከማን አንሼ ሆነች፡-

‘‘አሽሙር መርዝ ነው፣ የእባብ መርዝ!’’፣ ከማለቷ ከፊት እግሮቿ መካካል አንዱን ብድግ አድርጋ መሬት ከደቃች በኋላ ፣ ‘‘እባብን አትንኩብኝ፡፡ የምች መዳኒታችን ነው! እንበላዋለን!! ’’ ፣ አለች፡፡

አሁንም እንደገና፡፡ ሰው ጭራ አልባ የሆነው በነዚህ በነዚህ ምክንያቶች ነው ብያችኋለሁ አይደል፡፡ ግን ደግሞ እንኳንም ጭራ አልኖረው፡፡ እንደ ዝንጀሮ በጭራ ከመጫወት፣ ወይም እንደ አይጥ ጭራ ረስቶ ከመደበቅ፣ ጭራ የለሽ መሆን ይሻላል! በዚያ ላይ የሚከራይ ቤት እየጠበበ ሄዷል፡፡ ጭራ ማሳደሪያ ቦታ፣ ጭራ ተሸክሞ መተኛት፣ ለጭራ የማይመች ብርድ ልብስ… እንኳንም ጭራ ቀረብኝ! ምን ቀረብኝ ጭራነት ቀረብኝ እንጂ፡፡ ትርፉ መቆላት ነበር፡፡

አንዳንድ ሰው ጭራ ባይኖረውም እኮ እንደጭራ የመቆላት ባህሪ አለው፡፡ እንደውሻ ጭራ የሰው ድግስ እያሸተተ ጭራውን የሚቆላ ሰው አጋጥሟችሁ አያውቅም?

‘‘ የሰው ዓመል ዘጠኝ ፣ አንዱን ለኔ ስጠኝ ’’