የዕድገት ምሰሶ

በአለምሸት ግርማ

ትምህርት ለአንድ ሀገር የዕድገትና ስልጣኔ መሰረት ነው። በአንፃሩ ደግሞ የትምህርት አለመስፋፋት ለኋላቀርነት ቀዳሚ ምክንያት እንደሆነ ይታወቃል። በመሆኑም ጠንካራ የትምህርት ፖሊሲ ለዚህ አላማ ስኬት ትልቁን ሚና ይጫወታል።
ትምህርት ለሰው ልጆች ኑሮ ቅልጥፍና፣ ለሀገራት ዕድገትና ልማት፣ ባህልንና እውቀትን ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማሸጋገር እንደ ድልድይ ሆኖ የሚያገልግል ስለመሆኑም ብዙ ተብሏል። የዓለም ተምሳሌቱ የመጀመሪያው ጥቁር የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝደንት ኔልሰን ማንዴላ በአንድ ወቅት ስለትምህርት ሲናገሩ፣ “ትምህርት ዓለምን ለመለወጥ ልትጠቀምበት የምትችለው እጅግ በጣም ኃይል ያለው መሣሪያ ነው” ብለው ነበር።
የስልጣኔ መንገድ የሆነው ትምህርት ጥራቱን በጠበቀ መንገድ ለዜጎች ካልተሰጠ ፍሬው የተበላሸ መሆኑ አይቀርም። በግብርናው ዘርፍ ምርጥ ዘር እንደሚባለው በትምህርትም ዘርፍ ብቃት ያለው ዜጋ ለማፍራት ጥራት ያለው ትምህርት በተገቢው መንገድ መሰጠት መቻል አለበት።
ከዚህ ቀደም በነበረው የትምህርት ስርዓት ውስጥ በነበረው የጥራት መጓደል ምክንያት ሀገሪቱ ላይ የተፈጠረው ጫና የሚታወቅ ነው። ትምህርት ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት ምሰሶ ነውና ጥራትን ቀዳሚ ማድረግ ይገባል።
ለዚህም ነው የሀገራችን መንግስት አዲስ የትምህርት ፖሊሲ መተግበር የጀመረው። ይህም የትምህርት አሰጣጥ ስርዓቱን፣ የትምህርት መርጃ መሳሪያዎችን፣ የፈተና አሰጣጥና የመምህራን ብቃት ቁጥጥርን ያካትታል።
የትምህርት ጥራት ዝቅተኛነት የተማረ ዜጋ ማፍራት አለመቻሉ አንድ ነገር ሆኖ የሞራል ጉድለት ስለሚያስከትል ከፍ ያለ ዋጋን ሊያስከፍል ይችላል።
ሀገራችን በስልጣኔ ቀዳሚ እንደነበረች ታሪክ ይመሰክራል። ታሪክ እንደሚያስረዳው ከሆነ የቀደሙ የሀገራችን መሪዎች ለትምህርት ልዩ ትኩረት ነበራቸው። ለዚያ ማስረጃ የሚሆኑት ደግሞ በዘመኑ የነበሩ የስነፅሑፍ፣ የቅርፃቅርፅ እና ሌሎችም የጥበብ ውጤቶች ናቸው።
ትምህርት ለግል አእምሮአዊ እድገት ከሚሰጠው ጥቅም በላይ ለአገር ትልቅ ፋይዳ አለው። አገር በትምህርት ውስጥ የሚያልፉ ዜጎቿ በጨመሩ ቁጥር፣ ምክንያታዊ ትውልድን እያፈራች እድገትና ልማቷን የማፋጠን እድሏ እየጨመረ ይሄዳል። እነዚህ ዜጎቿ ችግሯን የሚሸሹ፣ ሲከፋም ችግር የሚፈጥሩባት ሳይሆን መፍትሄ የሚያመነጩና የችግርን መፍቻ ቁልፍ የያዙ ናቸው።
ይህንን ግብ ማሳካት ካልተቻለ ግን ዜጎች የሀገር ሸክም ይሆናሉ። የተሠራን የሚያጠፋና የሚያወድም ትውልድም ይፈጠራል፤ ይበራከታል። ይህንን ችግር የሚገታው በዋነኛነት የትምህርት ሥርዓት ነው። ብዙ አገራት የትምህርት ስርዓቶቻቸውን እንደ ዱላ ቅብብል እያሻገሩ ብሎም እያሻሻሉ ማስቀጠል ሲችሉ፣ አንዳንዶች ደግሞ ከፖለቲካ ለውጥ ጋር የቀደመውን እየጣሉ፣ አዲስ መሠረት ለመጣል እየሞከሩ፣ እንደ አዲስ ይጀምራሉ።
ትምህርት የአንድን ማኅበረሰብ እሴቶች እና የተከማቸ እውቀት ማስተላለፊያ መንገድ ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችል በትምህርት ላይ የተሠሩ ጥናቶች ያመላክታሉ። ከዚህ አንጻር የማኅበራዊ ሳይንስ ሊቃውንት ማኅበረሰባዊነት (so­cialization) ከሚሉት ጋር አብሮ የሚሄድ መሆኑን ይገልጻሉ። ማኅበረሰባዊነት የኅብረተሰቡን ደንቦች እና ርዕዮተ ዓለሞች ወደ ውስጥ የማስገባት ሂደት ሲሆን፣ ማኅበራዊነት መማርን እና ማስተማርንም ይጨምራል።
አንድ ማኅበረሰብ ለትምህርት የበለጠ ቦታ ሲሰጥ፣ አጠቃላይ የትምህርት ዓላማዎችን፣ ይዘቶችን፣ አደረጃጀቶችን እና ስልቶችን ለመንደፍ እንደሚሞክርም ጥናቶች ያመላክታሉ።
ጥራት የሌለው ትምህርት ጉዳቱ ብዙ ነው። ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት በሌለበት ጥራቱን የጠበቀ ህክምና ማግኘት አይቻልም። ደረጃውን የጠበቀ የህንፃ ግንባታ አይኖርም፤ ለሀገሩ ፍቅር የሌለው፤ ኪሳራን የሚያስከትል፤ ‘በልቼ ልሙት’ የሚል ሙሰኛ ዜጋ እንዲበራከት በር ይከፍታል። ይህም ዜጎች ፍትሕን እንዳያገኙ የሚያደርግ ስለሆነ የተረጋጋ ሰላም እንዳይኖርም ያደርጋል።
በመሆኑም ሀገራችን በስልጣኔዋ ትቀጥል ዘንድ የተጀመረው የትምህርት ጥራት ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። መንግስትም ዛሬ ከገነባቸው በርካታ የትምህርት ተቋማት በተጨማሪ የትምህርት ጥራት ላይ በትኩረት መስራት ይኖርበታል፡፡
የትምህርት ጥራትና የተማሪዎች ስነ-ምግባር ላይ ቀጣይነት ያለው ስራ መሰራት አለበት። ይህም ለአንድ አካል ብቻ የሚተው ባለመሆኑ ሀገር ትለወጥና ታድግ ዘንድ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ኃላፊነት አለበት። በተለይም ቤተሰብ የሁሉም ነገር መሰረት ነውና ልጆቹን በመልካም ስነምግባርና በዕውቀት እየታገዙ እንዲያድጉ ሃላፊነት መውሰድ ይኖርበታል።
በማይመች ሁኔታ ውስጥም ሆነን ዛሬም ከእውቀት፣ ከትምህርትና ከምርምር አምባ የሚገኙ ለአገራቸው ተስፋ የሚሆኑ ዜጐች እንዲበራከቱ ተግተን እንስራ!!