የቅርብ ሩቅ የሆነው ምርት

የቅርብ ሩቅ የሆነው ምርት


በገነት ደጉ


በተለምዶ “በጓሮው ውስጥ ያለ ላም የጠረጴዛው ላይ ምግብ ነው” ይባላል። ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን ለማራመድ ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ መጠነ ሰፊ የፍላጎት እና የአቅርቦት አለመጣጣም ዋናው እክል የወተት ተዋጽኦዎችን ለምግብነት አለመጠቀም ነው፡፡
ከሁሉም በላይ ከወተት ፍጆታ ጋር የተቆራኙት ልጆች ናቸው፡፡ የእናት ወተትን አንድ ሕፃን መብላት የሚጀምረው ተቀዳሚው ምግብ ነው፡፡
በሀገራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የወተት ፍላጎት ከአቅርቦት አለመመጣጠን ጋር ተያይዞ ያለውን ችግርና የወተት ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰሩ ባሉት ጉዳዮች ዙሪያ የሰበሰብነውን መረጃ እናስቃኛችሁ፡፡
ወ/ሮ አበራሽ ሌጋሞ የሀዋሳ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ ባለትዳርና የሁለት ልጆች እናት ናቸው፡፡ እኚህ እናት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣውን የወተት ዋጋ ጭማሪ እንዲህ ሲሉ በምሬት ይገልፃሉ፡፡
ወተት ለልጆቻችን አስፈላጊ መሆኑ ቢታወቅም ከአቅሜ አንፃር ልጆቼ መጠጣት አየፈለጉ ማቅረብ ግን አልቻልኩም ይላሉ።
ባሳለፍነው ዓመት አንድ ሊትር ወተት 30 ብር የነበረ ሲሆን በያዝነው ዓመት በአማካይ እስከ 70 ብር ደርሷል ይላሉ። በዚህም የወተቱ ዋጋ መጨመር ብቻ ሳይሆን ከጥራትም አንፃር ወሃ የተከለሰበትን ወተት ለማጠጣት ተገደናል ብለዋል፡፡
የወተት አቅራቢዎች ዋጋ ለመጨመር ዋነኛ ምክንያታችን የእንሰሳት መኖ መወደድ ነው ይላሉ፡፡ በ70 ብርም ከጠዋቱ 12 ሰዓት ማምሻ ላይ ከ11 ሰዓት ጀምሮ ዕቃ ማሳለፍ ካልተቻለ ወተት የማግኘት ዕድላቸው ጠባብ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
ሌላው በመንግስት ስራ የሚተዳደሩ አቶ ብዙነህ አበራ በበኩላቸው የወተት አቀርቦት ችግር በሀዋሳ ከተማ የከፋ መሆኑን ነው፡፡
ይህም ብቻ አይደለም፤ የእንሰሳት መኖ ለአብነት ፉርሽካ ዋጋ ከ5 መቶ እስከ 2ሺ ብር ድረስ መድረሱን ይናገራሉ፡፡ አንድ ሁለት ላሞችን በቤታቸው ቢያረቡም እንኳን በአሁኑ ሰዓት ከመኖ ዋጋ መናር ጋር ተያይዞ ማርባት ለማቆም እንደተገደዱም በግልጽ ያስረዳሉ፡፡
የወተት እጥረት ብቻም ሳይሆን ሙሉ ለሙሉ የአቅርቦት ችግሮች በስፋት እየተስተዋለ እንደሆነም ያነሳሉ፡፡ እርባታም ከአዋጪነት ይልቅ አክሳሪ እንደሆነ በመግለፅ።
ሌላው የአካባቢ ነዋሪ አቶ አሰፋ አባተ ወተት ከዋጋ ጭማሪም ባሻገር ለልጆቻቸው ጥራት የሌለውን ወተት ለማጠጣት ተገደናል ይላሉ፡፡
ጥንት አባቶቻችን የግጦሽ ቦታ በበቂ ነበራቸው የአሁኑ ትውልድ ግን መሬቱን እየሸጠ የጨረሰ ይመስላል። የግጦሽ ቦታዎችም እንደቀድሞው በቂ ባለመሆናቸው ለመኖ እጥረቱ ምክንያት ሆኗል፡፡
በዚህም የሚቀጥል ከሆነ ልጆቻችንን ወተት አጠጥተን ለማሳደግ እንቸገራለን ሲሉም ምሬታቸውን አሰምተውናል፡፡
እኛም ከህብረተሰቡ አንደበት ይነሳ የነበረውን የወተት ችግር ለመቅረፍና ምርታማነቱን ለማሳደግ ምን እየተሰራ ነው? በሚሉ ጉዳዮች ዙሪያ ምላሽ ይሆነን ዘንድ ያነጋገርናቸውን ባለድርሻ አካላት ምላሽ ይዘን ቀርበናል፡፡
በደቡብ ክልል ግብርና ቢሮ የእንሰሳት ዝሪያ ማሻሻያ መኖ ልማት ዘርፍ ኃላፊ እና ምክትል የቢሮ ኃላፊ አቶ ኢያሱ ተረፈ እንዳሉት የወተት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በክልሉ በዳልጋ ከብቶች ላይ መሰረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በክልሉ የዳልጋ ከብቶች ቁጥር ወደ 9 ነጥብ 1 ሚሊየን እንዳሉ መረጃዎች ያሳያሉ። ከነዚህም ውስጥ ወደ 3 ነጥብ 1 አካባቢ ወተት ሊሰጡ የሚችሉ ላሞች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
እስካሁን 7 መቶ 71 ሺህ ሊትር ዓመታዊ የወተት ምርት እንዳለን መረጃዎች ሲያመላክቱ በሀገራችን የነፍስ ወከፍ የወተት ፍጆታ 66 ሊትር ነው፡፡ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ እስከ 2 መቶ ሊትር መሆኑ ይነገራል፡፡ ከዚህም በመነሳት ልዩነቱን መገመት አያዳግትም፡፡

እንደ ክልል ከቁጥር አንፃር ትልቅ ሀብት መሆኑን የሚያሳይ ቢሆንም እንኳን ከምርታማነት አንፃር ግን ጉድለት እንዳለም አስረድተዋል፡፡ በዚህም የፍላጎትና አቅርቦት አለመጣጣም በስፋት እንደሚስተዋልም ተናግረዋል፡፡
መንግስት የሌማት ትሩፋት ፕሮግራም ይፋ በማድረግ ስራዎች ተጀምረዋል። ከዚህም መካከል በተለይ የእንሰሳት ሀብት ስራዎች ውስጥ የወተት ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ቀዳሚውን ስፍራ ይዟል በማለት ንግግራቸው አስፍረዋል፡፡
ከዚህ አጀንዳ አንፃር በጣም ትኩረት የተሰጠው ወተት ነው፡፡ የወተት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ሶስት መሰረታዊ ጉዳዮች አሉ፡፡ በዚህም መሰረት የመጀመሪያውና ዋነኛው የመኖ ልማት ስራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በተለይም በወተት እና በሌሎች እርባታዎች ውስጥ ከ70 በመቶ በላይ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው የመኖ ልማት ስራ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡

ይህንንም በተመለከተ በግብርና ቢሮ በኩል ባለው ተዋረድ እንደ ክልል ሰፊ ስራዎች በንቅናቄ መልክ በዓመቱ መጀመሪያና መሀል ላይ ተሰርተዋል። በዚህም መሰረት የመኖ ልማት ስራዎችን ለማጠናከር ጥረቶች መደረጋቸውን አንስተዋል፡፡
ወተት የሚገኘው በሁለት መልኩ ነው፡፡ አንዱ ከአካባቢ ላሞች ዝሪያቸውን በማሻሻል ሲሆን ሌላው ዝሪያቸው ከተሻሻሉ ከብቶች የሚገኝ የወተት ምርት ነው፡፡ ለእነዚህ ሁለቱም ስራዎች የመኖ ልማት ሀብታችን ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡

በዚህም በተፈጥሮ ትልቅ አቅም ያለው የግጦሽ ሳር ሲሆን ከዚህም ጋር ተያይዞ የዝርያ የማሻሻል ስራዎችን መስራት ነው። በተለይም በቆላማ አካባቢዎች አርብቶ አደሩ የሚጠቀመው የተፈጥሮ ግጦሽ ነው፡፡ በመሆኑም በተደጋጋሚ ከብቶቹ ስለሚጠቀሙ የመኖ ምርቱ ይጎዳል፡፡ ይህንንም በተሻሻሉ የሳር ዝሪያዎች ጭምር ማልማትን ይጠይቃል፡፡
ሁለተኛውም የተሻሻሉ መኖ ተከላ ሲሆን በዚህ ዓመት ከ58 ሺ ሄክታር በላይ ለመትከል ጥረት ተደርጎ ስራው በጥሩ ሁኔታ ተከናውኗል፡፡
እንደ ክልላችን በዋናነት የምንጠቀማቸው የሳር ዓይነቶች አሉ። ለዓብነትም ዲንሾ ሳር፣ የእርግብ አተር እና አልፋ አልፋ የሚባሉ በዘርም ይሁን በችግኝ የተሻሻሉ መኖዎችን የመትከል ስራዎች መሰራታቸውን የዘርፉ ኃላፊ ተናግረዋል፡፡

በአርሶ አደሩ አካባቢ ከሰብል የሚገኙትን ተረፈ ምርት በአግባቡ በመሰብሰብ እና የመጠቀም ልምድ እንዲኖራቸው የማድረግ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውንም አንስተዋል።

ዘንድሮ እንደ ክልል በአንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረው ድርቅም የመኖ ልማት ስራዎችን ቀላል በማይባል ደረጃ ጎድቷል፡፡ በዚህም አግባብ የመኖ እና የተፈጠሮ ግጦሽ ሰራዎችን በአግባቡ በማልማትና ከሰብል የሚገኘውን ተረፈ ምርት በአግባቡ ለመያዝ ጥረት ተደርጓል ብለዋል፡፡

ከጤናም አንፃር በተለያዩ ጊዜያት የሚከሰቱ በሽታዎች የወተት ምርታማነት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ የቅድመ መከላከል ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ በተለይም ክትባት በመስጠት ምርታማነት እንዳይቀንስ ጥረት መደረጉንም በማንሳት፡፡ የዝሪያ ማሻሻል ስራዎች በስፋት መሰራታቸውንም እንዲሁ።

ለአርሶ እና አርብቶ አደሩ የወተት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የእንሰሳት እርባታው ከቁጥር ይልቅ ጥራት ላይ እንዲያተኮር በማድረግ በተሻሻሉ ዝሪያዎች በሶስት ላሞች እስከ ዘጠና ሊትር ድርስ የሚገኝ መሆኑን ተገንዝቦ ከብዛት ይልቅ ጥራት ላይ በማተኮር ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ አለባቸው የሚል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡