የሰንደቁ ወንድም!

የሰንደቁ ወንድም!
በይበልጣል ጫኔ
ከልጅነት ጓደኞቼ ጋር በብዙ ጥረት ተገናኘን። ልጅ እያለን የሚከብደን መለያየት ነበር። ከትምህርት ቤት እንደተመለስን በሩጫ ነበር መገናኛ ቦታችን ጋ የምንደርሰው። አንድ ቦታ ላይ እንደተኮለኮልን ጊዜው ይመሻል። እንደዚያ ተሰብስበን ምን እናወራ እንደነበር ዛሬ ላይ ትዝ አይለኝም። ብቻ ስለ ፊልም፣ ስለ ሰፈራችን ቆንጆ ሴቶች፣ ስለ ትምህርት ቤታችን መምህራን፣ ስለ ኳስ … ብዙ ብዙ ነገር ነበር የምናወራው።
አንዱ ወሬውን ይጀምራል። የጀመረውን ወሬ አጣፍጦ ካላወራው÷ ወይም ካንዛዛው ሌላኛው ይነጥቀዋል። ልክ እንደ ቅኔ ቤት ተማሪ÷ ሚስጥሩን ደረስኩበት አይነት። ጨዋታውን ነጥቆ ቀድሞ እንደጀመረው አይነት ሲቀጥልበት÷ የጨዋታው ጀማሪ አይደብረውም። ይልቅስ እየሳቀ አድማጭነቱን ይቀላቀላል።
የሆነ ቀን ግን ያልጠበቅነው ሆነ-
ከአብሮ አደግ ጓደኞቻችን መካከል አንዱ÷ ያውም ጥርስ የማያስከድነው ተጫዋች ልጅ ደረሶ ፀጥ አለ። እኛ የባጥ የቆጡን እንዘባርቃለን÷ እሱ እቴ ሃሳቡም ከኛ ጋር የለም። ዝም÷ ጭጭ አለ። ሁኔታው ደስ ስላላሰኘን፦
«ምን ሆንክ?» አልነው።
«ምንም!» አለ÷ ፈርጠም ብሎ።
በስንት ማግባባት እና ልመና÷ ለስብስባችን እንግዳ የሆነ ርዕስ ሰጠን። «ፍቅር ይዞኛል» አለን። ሁላችንም ደነገጥን። ለአፍታ ዝም ተባባልን። ተያየን፣ ተያየንና ድንገት መንጫጫት ጀመርን። ሁላችንም የመጣልንን ጥያቄ አዥጎደጎድነው፦
«ከማን ነው ፍቅር የያዘህ?»
«መቼ?»
«እንዴት ነው የያዘህ?»
«ቆይ የያዘህ ነገር ፍቅር መሆኑን እንዴት አወቅህ?» … ብዙ ብዙ ጥያቄዎች አዘነብንበት።
ጥያቄዎቻችንን ይስማ አይስማ እርግጠኞች አልነበርንም። ምክንያቱም ወደ አንዳችንም ዞሮ ጥያቄያችንን አላደመጠም። ፈገግም ኮስተርም አላለም። እንዲሁ አንድ ቦታ የተቸከለ ልሙጥ ፊቱን እያየን ነው ስንንጫጫ የቆየነው።
በድንገት ለመጨረሻው ጥያቄ ምላሽ መስጠት ጀመረ፦
«ትምህርት ቤትም ስሆን፣ ቤትም ስሄድ፣ ስተኛም፣ ስነሳም …. የማስበው ስለ’ሷ ብቻ ነው። ክፍል ውስጥ ስሆን አልማርም። አስተማሪው የሚለው አይገባኝም። ዝም ብዬ የማየው እሷን ነው። እኔ ለራሴ እንኳን ምን እንደሆንኩ ግራ ገብቶኝ ነበር። ኋላ ላይ ሳስበው ግን ፍቅር ነው። ፍቅር»
ሁላችንም ሰባተኛ ክፍል ነበርን ያኔ። አፍቃሪው ወዳጃችን ግን ስምንተኛ ክፍል ነው የነበረው። የክፍሉን ሁኔታ አናውቅም። የሰፈሩን ግን ዛሬ እሱ እንዲህ ሆኛለሁ እስኪለን ድረስ ምንም የተለየ ሁኔታ አይተንበት አናውቅም።
«ማናት?» አልነው፣ በአንድ ድምፅ።
«ማርታ!» ስሟን ጠራው፣ እየተስለመለመ።
ሳቅን በድንገት። አሳሳቃችን ደግሞ እንደተመካከረ ሰው ነው። አንድ ላይ። በህብረት። ኮስተር አለ። ኮስተር አልን እኛም በቶሎ። ከጥቂት ዝምታ በኋላ፦
«ቆይ ምኗን ነው የወደድከው?» አለ÷ ትንሽ ደፈር ያለ ጓደኛችን።
«አይታችኋታል ግን!» አለ÷ ሁልጊዜ የምናያትን ልጅ እንደ አዲስ ሊያስተዋውቀን እየዳዳው።
«አይታችኋታል ግን? … ፀጉሯ፣ አይኖቿ፣ አፍንጫዋ …» መታገስ አልቻልንም። በዚያ ዕድሜያችን የፍቅር ስሜቱ ምን እንደሆነ ባይገባንም÷ ከሆነ አይነት የጤና መታወክ ጋር እንደሚገናኝ ግን ከጓደኛችን ሁኔታ ተረድተናል።
ፀጉሯ አጭር እና ከርዳዳ ነው። እንደውም ወደላይ ሰብስባ አንድ ላይ አስይዛው ስትመጣ÷ ካስነጠሳት ይበተንባታል እያሉ ይፎግሯት ነበር። የዓይኗን ነገር እንለፈውና … ተንጋላ ብታለቅስ ከዓይኖቿ የሚፈልቁት የእንባ ዘለላዎች የሚጋጩባት አፍንጫ ጎራዳ ነበረች። አሳዘነን ጓደኛችን። በፍቅር ስም የሆነ የማይታወቅ ህመም የያዘው መሰለን። በጣም የሚያሳዝነው ግን ይህ ሁሉ ሲሆን እኛ ምንም አለማወቃችን ነው።
እርግጥ ነው እናቷ ከገበያ ሲመጡ÷ ዘምቢላቸውን ተሸክሞ ወደ ቤት ማድረስ ከጀመረ ቆይቷል። ከብቶቻቸው ከሰፈራቸው ርቀው ካየ÷ የራሱን ጉዳይ እርግፍ አድርጎ ጥሎ ወደ ቤታቸው ማድረሱን ከቅንነት እንጂ ከሌላ አላየንበትም ነበር። ወንድሟ ከጎረምሶች ጋር ሲደባደብ ባየንበት ቅፅበት÷ አፍቃሪው ወዳጃችን በምን ፍጥነት የፀቡ አካል እንደሆነ÷ ለማሰብ እንኳን ከብዶን ነበር።
እሱ በማይመለከተው ፀብ ውስጥ ጥልቅ ብሎ የአንዱን ጎረምሳ ወገብ በድንጋይ ነርቶት ተፈተለከ። ትላልቅ ሰዎች ሰብሰብ ብለው ከገላገሉ እና ፀቡን ካበረዱ በኋላ ተደባዳቢዎቹ እንዲታረቁ አደረጉ። የኛው ጅል አፍቃሪ ግን ከዳር ቀረ። በጣም የሚያስቀው ነገር አፍቃሪው ወዳጃችን ለሱ ብሎ ፀብ ውስጥ መሳተፉን ጎረምሳዎቹ እንጂ የማርታ ወንድም አለማወቁ ነው።
በነገራችን ላይ÷ እንደ አፍቃሪው ወዳጃችን ያሉ÷ የጉዳዩ ባለቤት የማያውቃቸው ጉዳይ ገዳዮች ዛሬም በየቦታው አሉ።
ዓለም ለሹመት እና ሽልማት የሚፈልጋችሁ ተፅዕኖ ፈጣሪ ከሆናችሁ÷ የሆነ ጥግ ላይ እናንተ የማታውቁት÷ ግን ደግሞ በስማችሁ የሚምል ሰው አይጠፋም። በተለይ ደግሞ በሆነ አጋጣሚ ድሮ አብራችሁ የተነሳችሁት ፎቶግራፍ ካለው÷ ራሱን አማካሪያችሁ አድርጎ ይሾማል። ከዚህ ከፍ ሲል ደግሞ፦
«ጥናቱን እኮ የጀመርነው አብረን ነበር÷ ኧረ እንደውም በቅድሚያ ሃሳቡን ያፈለቅኩት እኔ ነበርኩ። ምን ዋጋ አለው? … ጮማ ገንዘብ እንደሚያመጣ ሲያውቀው ሸመጠጠኝ» ይልላችኋል።
የዚህ ዓይነት ጠባይ ባለቤቶች የሚደገፉበት ባለዝና ያግኙ እንጂ የዝናው ምንጭ አይገዳቸውም። ስመ ጥር ሌባ ወይም ደግሞ የተፈራችሁ ነፍሰ ገዳይ ብትሆኑም «አውቀዋለሁ እኮ» ብሎ በመፈራታችሁ መፈራት የሚፈልግ ሰው አይጠፋም።
እዚህ ጋ አንድ ጨዋታ ልንገራችሁማ፦
በድሮ ጊዜ ነው አሉ። ሰንደቁ የሚባል የተፈራ ሽፍታ በአንድ ጫካ ውስጥ ይኖር ነበር። ያው ነገሩ ድሮ ሆኖ ሽፍታ አሉት እንጂ ዛሬ ቢሆን የነፃነት ታጋይ ወይም የሰብዓዊነት ዘማች ነበር መባል የነበረበት።
የትኛውም ሹም ህዝቡን ከበደለ ዋጋውን ሳይሰጠው ውሎ ማደር አይችልም። በሃብቱ ወይም በወገኑ የሚመካውንም መመኪያውን ይነሳዋል። በተቃራኒው ድሃ አደግ የሆነውን እና የተገፋውን ደግሞ ቀና ያደርጋል። እንደው በአጭሩ ፍርድ ለማደላደል ነው የሸፈተው ቢባል ይሻላል።
ታድያ በዚያው ወቅት በየመሸታ ቤቱ እየዞረ «የሰንደቁ ወንድም» እያለ መፎከርን ሙያው ያደረገ አንድ ሰው ተነሳ፦
«የሰንደቁ ወንድም» ይላል÷ ሞቅ ሲለው።
አንዳንዶቹ በድንጋጤ ቤቱን ለቀው ይወጣሉ። ሌሎቹ ድምፃቸውን ይቀንሳሉ። ሳያስቡት የጠጣበትን የሚከፍሉለት ሰዎችም ቁጥራቸው ቀላል አልነበረም። ኧረ እንደውም «የሱን ሂሳብ እንከፍላለን» የሚሉ ተገልጋዮችና «ሂሳቡ በኛ ነው» የሚሉ የመሸታ ቤት ባለቤቶች የሚፈጥሩት ክርክር ራሱን የቻለ ድራማ ነው።
ነገሩ እየቆየ ሲሄድ ሰንደቁ ጆሮ ደረሰ። አንድ ምሽት ማንም የማያውቀው ሰንደቁ÷ አንዱ መሸታ ቤት ተሰየመ። ሦስት አጃቢዎቹም አብረው አሉ።
«የሰንደቁ ወንድም» አለ ልማደኛው ሰው። በአንድ አፍታ የቤቱ ድባብ ቅይር አለ።
«ማነህ ወንድሜ÷ ለመሆኑ ሰንደቁን ታውቀዋለህ?» አለው።
ክው አሉ የመሸታ ቤቱ ታዳሚዎች። «ማነው ደግሞ እንዲህ ዓይነት ደፋር÷ የማይነካ ነክቶ ሊያስፈጀን የሚሞክር» ዓይነት ነው አደነጋገጣቸው።

«ማነህ ደግሞ አንተ?÷ የናቴን ልጅ ወንድሜን አውቀው አንደሆነ የምትጠይቀኝ» አለ÷ ጀብራሬው።

«የናቴ ልጅ ስትል?» ሰውየው እንደገና ጠየቀ።

«ታናሼ ነው። አብረን ነው ከብት አግደን ያደግነው። የዛሬን አያድርገው እና እየገረፍኩ ነበር ከብት የማስመልሰው» ንግግሩ አንዳች ውሸት ያለበት አይመስልም። የመሸታ ቤቱ ሰዎች ከወትሮው በተለየ አምነውታል። እስከዛሬ መጋበዛቸውም ትክክል እንደሆነ ተሰምቷቸዋል።

ነገሩ የተበላሸው፦

«ዘራፍ ሰንደቁ!

ዘራፍ መብረቁ!»

ፉከራ ሲሰማ ነው። ሰዉ ሁሉ ግራ ተጋባ።

«ይኼንን ወሽካታ አርባ ግረፉት። እኔስ በጄም አልነካው» አለ። ሰንደቁ ነበር ሰውየው ለካ፡፡

አጃቢዎቹ አርባ ገረፉት። ሰንደቁ እና አጃቢዎቹ ከስፍራው ርቀው ከሄዱ በኋላ እንኳን አርባ ጅራፉን ጠግቦ መሬት ላይ የተኛው ሰው መነሳት አልቻለም ነበር።

«እንዲህ ያለ ውርደት በዘራችሁም አይድረስ» ያለው ማን ነበር?