ሀዋሳ፡ ግንቦት 25/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) አሲዳማ አፈርን በኖራ በማከም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ በደቡብ ክልል ግብርና ቢሮ የወልቂጤ አፈር ምርምር ማዕከል አስታወቀ፡፡
ማዕከሉ በ2015/16 የምርት ዘመን ከ6 ሺህ በላይ የአፈር ናሙና ላይ ምርምር እያደረገ እንደሚገኝም ተጠቁሟል፡፡
የወልቂጤ አፈር ምርምር ማዕከል ሀላፊ አቶ ግዛቸው ደምስ ለጣቢያችን እንደገለጹት ማዕከሉ የጉራጌ፣ ስልጤና ሀዲያ ዞኖች እንዲሁም የም ልዩ ወረዳን ማዕከል አድርጎ የአርሶ አደሩን ማሳ ከአፈር አሲዳማነት ለመከላከል እየሰራ ይገኛል ፡፡
ማዕከሉ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ የአፈር ናሙና ምርምር በሰርቶ ማሳያ ማዕከል በመሥራት ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ በማከናወኑ ለውጥ እየተገኘ ነው ብለዋል፡፡
ማእከሉ ድጋፍና ክትትል በሚያደርግባቸው አካባቢዎች በ2014/15 የምርት ዘመን ከ7 ሺህ በላይ የአፈር ናሙና በላብራቶሪ ምርመራ ያደረገ ሲሆን 56 በመቶው አሲዳማ ሆኖ መገኘቱን ሀላፊው ተናግረዋል፡፡
በ2015/16 የምርት ዘመን ደግሞ ከ6 ሺ በላይ የአፈር ናሙና ተሰብስቦ በላብራቶሪ ምርመራ እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቁመው ከዚህም ውስጥ 3ሺ 500 ናሙና ምርመራ የተከናወነ ሲሆን 50 በመቶው በአሲዳማነት እንደተጠቃ ተናግረዋል፡፡
በአሲዳማነት የተጠቃ አፈር ምርትና ምርታመነትን በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል ያሉት አቶ ግዛቸው አርሶ አደሩ የባለሙያ ምክረ ሀሳብ በመቀበል መሬቱን በኖራ ማከም ካልቻለ ውጤታማ እንደማይሆን ገልጸዋል፡፡
አርሶ አደሩ መሬቱን በኖራ ከማከም ጎን ለጎንም የተፈጥሮ የአፈር ማዳበሪያ መጠቀም እንዲሁም የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራውን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስታውቀዋል፡፡
በጉራጌ ዞን የአሲዳማነት አፈር ካለባቸው አካባቢዎች መካከል የጉመር ወረዳ አንዱ ሲሆን የወረዳው አርሶ አሮች እንደሚናገሩት አካባቢው ተዳፋታማ በመሆኑ ማሳቸው ለአሲዳማነት ተጋልጧል፡፡ ይህም በምርታማነታቸው ላይ ተጽዕኖ አሳድሮ እንደቆየ ገልጸዋል፡፡
አሁን ላይ መሬታቸውን በኖራ በማከማቸው ቀደም ሲል ከሚያገኙት ምርት የተሻለ ውጤት እያገኙ እንደሆነ ተናግረዋል ፡፡
ዘንድሮ በቂ ማዳበሪያ እያገኙ እንዳልሆነም ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ዘጋቢ፡ አለምሰገድ እስጢፋኖስ- ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪና የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ አለማየሁ ባውዲ በክልሉ የሚገኙ የየተለያዩ ብሔሮች ዘመን መለወጫ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ !!
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አት ደመቀ መኮንን በመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ንግግር አደረጉ
300 ለሚሆኑ ወላጅ አጥ ተማሪዎች ኢትዮ- ቴሌኮም ሳውላ ድስትሪክት ከ270 ሺህ ብር በላይ የሚገመት የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ