ፎረሙ የውጭ ኩባንያዎችን በመሳብ ውጤትማ ነው ተባለ

በአዲስ አበባ ለሦስት ቀናት የተካሄደው የኢንቨስትመንት ፎረም የውጭ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች እንዲሰማሩ ዕድል መፍጠሩ ተመለከተ፡፡

የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት አቅም ለማስተዋወቅ ላለፉት ሦስት ቀናት በአዲስ አበባ ሲካሄድ የነበረው “ኢንቨስት ኢትዮጵያ 2023 ፎረም” ዛሬ ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ ፎረሙ ኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ማስተዋወቅ የቻለችበት ነው ብለዋል፡፡

በዚህም አዳዲስ የውጭ ኩባንያዎች ወደ ኢንቨስትመንት ዘርፉ እንዲገቡ ፎረሙ ዕድል መፍጠሩን ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

አምስት ግዙፍ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎችን ጨምሮ ከሌሎች ኩባንያዎች ጋር የኢንቨስትመንት ሥምምነት በማድረግ ፎረሙ በስኬት መጠናቀቁን ነው ያመላከቱት፡፡

ይህም በ2015 በጀት ዓመት ከ6 ቢሊየን ዶላር በላይ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለማምጣት ለተያዘው ዕቅድ ትልቅ ድርሻ አለው ነው ያሉት፡፡

ለኢንቨስትመንት ጥበቃ ማድረግና የሚያጋጥሙ ችግሮችን መፍታት መንግሥት ለዘርፉ ትኩረት ከሰጣቸው ጉዳዮች መካከል መሆኑንም ነው ያስገነዘቡት፡፡

የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) መንግሥት ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ ለመፍጠር ፖሊሲዎችና የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎችን ተግባራዊ እያደረገ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ግብርና፣ ማዕድን፣ አይሲቲ፣ ቱሪዝምና ማኑፋክቸሪንግ ቁልፍ የኢንቨስትመንት ዘርፎች እንደሚሆኑ ገልጸው ባለሃብቶች ዕድሉን እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል።