“የባሌን እጅ አይቼ አላውቅም”
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በሀገራችን ሴቶች ወደ አደባባይ ወጥተው ያላቸውን ችሎታ የሚያሳዩበት እድል አልነበረም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን ሴቶች ተጠቃሚ ያልሆኑበትን ልማድ አሽቀንጥረው በመጣል በተሰለፉበት የሥራ መስክ ውጤታማ እየሆኑ መጥተዋል፡፡ ቀደም ባሉ ዘመናት ሴቶች እንዲማሩ እንኳን አይፈቀድላቸውም ነበር፡፡ አሁን ግን ከወንዶች እኩል የመማር ዕድል እያገኙ ነው፡፡
በዚህ ጽሁፍ የሚገጥሟቸውን የሕይወት ፈተናዎች ተቋቁመው፣ በተሰማሩት መስክ ደግሞ በርትተው በመስራታቸው ጥሩ ደረጃ ላይ ስለደረሱ አንዲት እናት ተሞክሮ እንዳስሳለን፡፡ ወ/ሮ በቀለች ዋዳ ይባላሉ፡፡ በወላይታ ዞን በዳሞት ፉላሳ ወረዳ በሌራ ሰኞ ቀበሌ በ1960 ዓ.ም ተወለዱ፡፡ ትምህርት መማር የጀመሩት በ10 ዓመታቸው በሌራ ሰኞ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነበር፡፡