በደቡብ ክልል በ2012 የትምህርት ዘመን ከ 7 ሚሊየን በላይ ተማሪዎችን ለማስተማር እየተሰራ ነው፡፡
 
ሀዋሳ፡ ጷጉሜ 02/2011 ዓ.ም (ደሬቴድ) በ2012 የትምህርት ዘመን ከ 7 ሚሊየን በላይ ተማሪዎችን መዝግቤ ለማስተማር እየሰራሁ ነው አለ የደቡብ ክልል ትምህርት ቢሮ፡፡
 
በመላው የክልሉ ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች ምዝገባ እስከ መስከረም ሁለት ብቻ መሆኑን ወላጆች አውቀው ልጆቻቸውን ከወዲሁ እንዲያስመዘግቡ ጥሪ ቀርቧል፡፡
 
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ተሰማ ዲማ እንዳሉት በ2012 የትምህርት ዘመን በቅድመ መደበኛ 1 ነጥብ 7 ሚሊየን፤ ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል 4 ነጥብ 7 ሚሊየን፤ ከ9 እስከ 12ኛ ክፍል ደግም 6 መቶ 81 ሺህ ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር ታቅዶ ወደ ስራ ተገብቷል፡፡
 
አቶ ተሰማ አክለው እንዳሉት ከዚህ ቀደም ምዝገባ የሚካሄደው ከነሃሴ 25 በኋላ በመሆኑ የትምህርት ስራችንን ወደኋላ እየጎተተ የጊዜ ብክነትን ከማስከተሉ ባለፈ የትምህርት ጥራት ላይ የራሱ ሆነ ተጽእኖ ስላለው ችግሩን ለመቅረፍ ዘንድሮ ምዝገባችንን ከነሃሴ 13 ጀምረናል ፤የምናጠናቅቀውም መስከረም 2 ነው ብለዋል፡፡
 
ከመስከረም 2 በኋላ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ምዝገባ የማይኖር መሆኑን ወላጆች አውቀው ልጆቻቸውን ከወዲሁ አስመዝግበው እንዲያጠናቅቁም ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
 
ለትምህርት ዘመኑ ትምህርት ቤቶችን ውብ፤ ሳቢ፤ ጽዱና ማራኪ መደረጉን ገልጸው አስፈላጊ የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ እንዲሟሉላቸው ተደርጓል ብለዋል፡፡
 
በጸጥታ እክል ሳቢያ አገልግሎት መስጠት ያቆሙ ትምህርት ቤቶችም ወደስራ እንደሚገቡ ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ታምራት ሽብሩ