በቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ከ19 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት አደንዛዥ ዕፅ ተያዘ፡፡

ሀዋሳ፡ መስከረም 08/2012 ዓ.ም (ደሬቴድ) በቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ የጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ከ19 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት አደንዛዥ ዕፅ ተያዘ፡፡

የገቢዎች ሚኒስቴር ህግን ለማስከበር እየሰራ ባለዉ ስራ በርካታ በአገር ላይ ጉዳት የሚያደርሱና ተተኪዉን ትዉልድ በሱስ የሚበርዙ የኮንትሮባንድ ቁሳቁሶች እየተያዙ ነዉ፡፡

በዚሁ መሰረት በቦልቪያናዊዉ ናማኒ ቺንቼ ኢቬሊን የፓስፖርት ቁጥር AE57255 ከብራዚል ሳዖ ፖሎ አዲስ አበባ የገባዉ 8 ኪሎ ግራም የኮኬይን አደንዛዥ ዕፅ በቦሌ የጉምሩክ ፈታሾች በቁጥጥር ስር ዉሏል፡፡

ዕፁን ይዞት ይጓዝ በነበረዉ ግለሰብ ላይ ከብራዚል ሳኦ ፖሎ ጀምሮ በጉምሩክ ኮሚሽን ኢንተለጀንስ ቡድን ባደረገዉ የተቀናጀና ጠንካራ ክትትል በቁጥጥር ስር ሊዉል ችሏል፡፡ ይህንን አድካሚና የተቀናጀ ስራ በመስራት እፁን መያዝ ለቻሉ የቦሌ አየር ማረፊያ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አመራር አካላትና ሰራተኞች የገቢዎች ሚኒስቴርና የጉምሩክ ኮሚሽን ያለዉን አድናቆት ገልጿል፡፡

ባለፈዉ ሳምንትም 20 ሚሊየን ብር የሚገመት 10 ነጥብ 8 ኪሎ ግራም የሚመዝን አደንዛዥ ዕፅ መያዙ የሚታወስ ነዉ፡፡
ምንጭ፡ የገቢዎች ሚኒስቴር