በመማር ማስተማር ስራዎች ወቅት የፖለቲካ አመለካከት ማንጸባረቅ አይገባም - ዶክተር ጥላዬ ጌቴ

ሀዋሳ፡ መስከረም 12/2012 ዓ.ም (ደሬቴድ) በኢትዮጵያ የፖለቲካ ውሳኔ ከሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ውጪ በመማር ማስተማር ሂደቱ የሚሳተፉ አካላት የፖለቲካ አመለካከታቸውን በመማር ማስተማሩ ሂደት ማንጸባረቅ እንደሌለባቸው የትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ።
አዲሱ የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታም ምሁራን ከፖለቲካ አመለካከታቸው ወጥተው በሳይንሱና በምርምር ባገኙት ውጤት ላይ ማተኮር እንዳለባቸው ያስገድዳል።
የትምህርት ጥራቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ ለመምጣቱ ስርዓተ ትምህርቱ፣ ደረጃውን የጠበቀ መማሪያ ትምህርት ቤትን ጨምሮ የግብዓት እጥረት፣ የዘርፉ ተዋንያን የአቅምና ፍላጎት ውስንነት በምክንያትነት ይጠቀሳሉ።
ከዚህ ባለፈም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገኙ የትምህርት አመራሮች በፖለቲካ ተጽዕኖ ስር መውደቅና ያንን ወደ ተማሪዎቻቸው ማስረጻቸው ችግሩን አባብሶታል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጥላዬ ጌቴ እንዳሉት “በየትኛውም ዓለም ትምህርት ከፖለቲካ ነጻ ሊሆን አይችልም”።
ለአብነትም “የአንደኛ ደረጃ ትምህርትን በግዴታ እሰጣለሁ፤ ትምህርት ለዜጎቼ በነጻ እሰጣለሁ፤” የሚሉት ሃሳቦች ፖለቲካዊ ውሳኔ የሚያስፈልጋቸው መሆናቸውን በመግለጽ።
የስርዓተ ትምህርት ጉዳይ ላይም ፖለቲካዊ ውሳኔ ካልተሰጠበት መርሃ ግብሩ ውጤታማ ሊሆን እንደማይችልም በማከል።
ይሁን እንጂ ትምህርት ነጻነትን ስለሚሻ ከቅድመ መደበኛ ትምህርት እስከ ዩኒቨርሲቲ ያሉ የትምህርት አመራሮችና ባለሙያዎችም በፖለቲካ አመለካከታቸው ሳይሆን በሙያ ብቃታቸው ብቻ መመደብ ይኖርባቸዋል ብለዋል።
የሀገር በቀል እውቀት እናስተምራለን ሲባልም የአንድን እምነት ወይም የፖለቲካ ድርጅት አመለካከትና ርዕዮተ ዓለም መጫን አለመሆኑን ይገልጻሉ።
አዲሱ የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታም ምሁራን ከፖለቲካ አመለካከታቸው ወጥተው በሳይንሱና በምርምር ስራዎች ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ አመላክቷል ብለዋል።
በአገራችን ደግሞ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ህብረ ብሄራዊት ኢትዮጵያን መገንቢያ ማዕከል እንጂ የእርስ በርስ ግጭት መፍጠሪያ መሆን እንደሌለባቸውም ይመክራሉ ሚኒስትሩ።
ምሁራን የትኛውም አይነት የፖለቲካ አመለካከት ይኑራቸው የሚያስተምሩት ግን ሳይንሱንና የምርምር ግኝታቸውን ብቻ መሆን እንዳለበት በማውሳት።
በተለይም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራን ተማሪዎቻቸውን እውቀትና ክህሎት የሚያስጨብጡበት እንጂ በፖለቲካ አመለካከታቸው ለችግር የሚዳረጉበት መሆን የለበትም ብለዋል።
ተማሪዎችም የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ የተረዱ፣ ስራ ፈላጊ ሳይሆኑ ስራ ፈጣሪ ሆነው መውጣት የሚችሉበትን አጋጣሚ መጠቀም እንዳለባቸው አሳስበዋል እንደ ኢዜአ ዘገባ።

የዘንድሮው የአልበርት ኦስቫልድ የሄሰን የሰላም ሽልማት ዛሬ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተበረከተ

ሀዋሳ፡ መስከረም 12/2012 ዓ.ም (ደሬቴድ) የዘንድሮው የጀርመኑ የአልበርት ኦስቫልድ ድርጅት የሄሰን የሰላም ሽልማት ዛሬ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ተበርክቷል።
ዛሬ ከቀትር በፊት በሄሰን ፌደራዊ ግዛት ዋና ከተማ ቪስባደን በሚገኘው የፌደራል ግዛቱ ምክር ቤት በተከናወነው የሽልማት አስጣጥ ሥነ ሥርዓት የተገኙት የኢትዮጵያ የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈርያት ካሚል ሽልማቱን ተቀብለዋል።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ የሄሰን ፌደራዊ ግዛት ጠቅላይ ሚኒስትር የሄሰን ፓርላማ አባላት የጀርመን መንግሥት ባለሥልጣናት የተለያዩ ድርጅቶች ተወካዮች እና የኢትዮጵያ መንግሥት ዲፕሎማቶች ተገኝተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሰላም ሽልማቱ የተሰጣቸው በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ሰላም ለማውረድ በመቻላቸው ነው።
የሄሰን የሰላም ሽልማት የቦርድ ስራ አመራር እና የሄሰን ፓርላማ ፕሬዝዳንት ቦሪስ ራየን፤ "ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለአፍሪቃ አህጉር ታላቅ ተስፋ ከተጣለባቸው መሪዎች አንዱ ናቸው" ሲሉ አመስግነዋቸዋል።
የሄሰን ፌደራዊ ግዛት ጠቅላይ ሚኒስትር ፎከር ቡፋየርም ዐቢይ ለኢትዮጵያ እና ለኤርትራ ሰላም ካበረከቱት አስተዋጽኦ በተጨማሪ በአፍሪቃ ቀንድ ግጭቶችን ለማስወገድ የሚያደርጉትን ጥረትም ማድነቃቸውን ኢቢሲ ዘግቧል።

ኢትዮ ቴሌኮም የደቡብ ሪጅን ወላጅ ላጡ ህጻናት ለትምህርት የሚያስፈልጉ ደብተሮችን ድጋፍ አደረገ፡፡
በተለያዩ ምክንያቶች ወላጆቻቸውን ያጡና ድግፍ የሚሹ ልጆች ወደ ትምህርት ቤት እንዲሄዱ በማሰብና በሀገር ደረጃ የተጀመረውን በጎ ስራ ለማጠናከር ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል ለሚማሩ ተማሪዎች ድጋፍ ማድረጉን የኢትዮ-ቴሌኮም የደቡብ ሪጂን አስታወቀ፡፡

የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል መንግስት መስተዳደር ምክር ቤት በ202ኛ መደበኛ ስብሰባው በሁለት አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

ሀዋሳ፡ መስከረም 12/2012 ዓ.ም (ደሬቴድ) መስተዳድር ም/ቤቱ የሲዳማ ዞንን በክልል የመደራጀት ህዝበ ውሳኔ ለማካሄድ የማስፈፀሚያ ፕሮጀክት ማቋቋሚያ ደንብ ላይም በመምከር ውሳኔ ማስተላለፉ ተጠቁሟል፡፡

Subcategories

የቅጂ መብት © 2019 ደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት