የኢትዮጵያ መንግስት በሕዳሴው ግድብ የውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ዙሪያ የተጀመረውን ምክክር ለማስቀጠል ቁርጠኛ ነው

ሀዋሳ፡ መስከረም 25/2012 ዓ.ም (ደሬቴድ) በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የግብጽ፣ ኢትዮጵያ እና ሱዳን የውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮች መስከረም 5 እና 6 ቀን 2012 ዓ.ም በካይሮ ባካሄዱት ስብሰባ ባስቀመጡት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት በካርቱም የሶስትዮሽ ስብሰባቸውን አካሂደዋል፡፡
ከሚኒስትሮቹ ስብሰባ አስቀድሞ የአገሮቹ ገለልተኛ የሳይንሳዊ ጥናት ቡድን ከመስከረም 19 እስከ 22 ቀን 2012 ዓ.ም በካርቱም አምስተኛ ዙር ስብሰባውን አካሂዶ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሙሌት እና የውሃ አለቃቅ ቴክኒካዊ ጉዳዮች ዙሪያ መክሯል ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በአገራቱ መካከል የሚደረገው ቴክኒካዊ ምክክር ብቸኛው የመፍትሄ አማራጭ በመሆኑ መቀጠል እንደሚኖርበት ያምናል ነው የተባለው፡፡
የሳይንሳዊ ቡድኑ አራት ስብሰባዎችን አድርጎ አበረታች ውጤት እያሳየ ባለበት ወቅት ግብጽ በተናጠል ያቀረበችው የውሃ ሙሌት እና አለቃቀቅን የሚመለከተው ሰነድ ከትብብር ማዕቀፉ ውጪ የሆነ እና ሂደቱን ያናጠበ  ሆኗል ተብሏል፡፡
ሆኖም የውሃ ሚኒስትሮች የኢትዮጵያ የውሃ ሙሌት እና አለቃቀቅ እቅድ፣ የግብጽ መንግስት የሚያቀርበው ሰነድ እንዲሁም ሱዳን በጉዳዩ ላይ የምታቀርበው ሰነድ ለሳይንሳዊ ቡድኑ ቀርቦ ዝርዝር ትንታኔ እንዲደረግበት እና ምክረ-ሃሳብ እንዲቀርብለት በመስከረም ወር 2012 ዓ.ም በካይሮ በተደረገው ስብሰባ ወስነዋል፡፡
በካርቱም ለአራት ቀናት በተካሄደው ስብሰባ የሳይንሳዊ ቡድኑ በመስከረም ወሩ የካይሮ ስብሰባ በተሰጠው አቅጣጫ መሠረት የኢትዮጵያን የግድብ ሙሌት እና የውሃ አለቃቀቅ ዕቅድ ፣ እንዲሁም ሱዳን እና ግብጽ ያቀረቡትን የሙሌት እና የውሃ አለቃቀቅ ቴክኒካዊ ጉዳዮችን የሚዳስሰውን ሃሳብ አዳምጦ ውይይቶችን አካሂዷል፡፡
ውይይቱ ሶስቱም ቡድኖች በተስማሙበት ርዕሰ ጉዳይ መዘርዝር ላይ የተመሰረተ ሲሆን በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ከመስማማት ተደርሶ በሌሎቹ ላይ የሃሳብ መለያየቶች ተመዝግበዋል፡፡
እነዚህ የሃሳብ ልዩነቶች በሳይንሳዊና ጥናት ቡድኑ ውይይትና ትንተና መግባባት ሊደረስባቸው የሚችሉ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ ግድቡን ለመሙላት ያቀረበችው እቅድ የታችኛውን ተፋሰስ አገራት ጥቅም ለመጠበቅ ያላትን አቋም ያሳያል፡፡
ይህም በተጨማሪ ኢትዮጵያ እና ሱዳን ማናቸውም ቴክኒካዊ ጉዳዮች ለሳይንሳዊ ጥናት ቡድኑ ቀርበው ትንተና እንዲደረግባቸው ገንቢና አካታች የውይይት አካሄድ ቢከተሉም የግብጽ ወገን ያቀረብኳቸው ሃሳቦች በሙሉ ተቀባይነት ካላገኙ ውይይቱ ሊቀጥል አይችልም በሚለው የማያሰራ አቋሙ በመቀጠሉ የሳይንሳዊ ጥናት ቡድኑ ስራውን በተሟላ አኳኋን ማከናወን ሳይችል ቀርቷል፡፡
ይህ የግብጽ አቋም የሳይንሳዊ ጥናት ቡድኑ ስብሰባ እንዲሁም የሚኒስትሮች ስብሰባው ስምምነት በተደረሰባቸው ጉዳዮች ላይ ጭምር ሪፖርት እንዳያዘጋጁ አድርጓል፡፡
የግብጽ አካሄድ አዲስ ሳይሆን ከዚህ ቀደምም በግድቡ ላይ ሶስቱ አገራት ሊያከናውኑት የነበረውን የውሃ፣ የአካባቢያዊና ማህበራዊ ተጽእኖ ጥናት በግብጽ ወገን እንዲስተጓጎል በተደረገ ጊዜ የታየ የሳይንስ እና የምክክር የመፍትሄ አማራጭን የማፋለስ ዘዴ ነው፡፡
ኢትዮጵያ አለመግባባት መፍቻ ዘዴን የሚደነግገውን የመርህ መግለጫ ስምምነቱን አንቀጽ 10 ጠቅሶ መፍትሄ ለመፈለግ ጊዜው እንዳልሆነ እና ቴክኒካዊ ምክክሩ ሊቀጥል እንደሚገባ ታምናለች፡፡
የውሃ ሚኒስትሮቹ በሁለት ቀናት ስብሰባቸው የሳይንሳዊ ጥናት ቡድኑ የደረሰበትን ተመልክተው አቅጣጫ ለማስቀመጥ ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም የግብጽ ወገን ቀድሞውኑ የምክክር ሂደቱ እንዲፈርስ አቋም ይዞ የመጣ በመሆኑ ጉባኤው የሳይንሳዊ ጥናት ቡድኑ በቀጣይነት ማከናወን ስላለበት ተግባር መመሪያ ሳያስተላልፍ ቀርቷል፡፡
የግብጽ መንግስት ሶስተኛ ወገን በጉዳዩ ጣልቃ እንዲገባ እያቀረበ ያለው ሃሳብ በሶስቱ አገራት የትብብር መድረክ የታየውን አበረታች ሂደት የሚያጣጥል እና ሶስቱም አገራት በመጋቢት 2007 ዓ.ም. የፈረሙትን የመርሆዎች መግለጫ ስምምነት የሚጥስ ተግባር ነው፡፡
የሶስተኛ ወገን ጣልቃ-ገብነት ኢትዮጵያ እና ሱዳን የማይቀበሉትና ተገቢ ያልሆነ፤ በአገራቱ መካከል ያለውን ዘላቂ ትብብር የሚጎዳ፤ ለውይይት ያለውን በቂ እድል ወደ ጎን የሚያደርግ እና ገንቢ የሆነውን የውይይት መንፈስ የሚያደፈርስ ነው፡፡
ቴክኒካዊ ምክክር የሚጠይቀው የግድብ ሙሌት እና ውሃ አለቃቀቅ ጉዳይ ለፖለቲካ ምክክር እንዲቀርብ የሚጠይቀው ሃሳብም የጉዳዩን ጸባይ ያላገናዘበ፣ የሶስቱ አገራት መሪዎች የውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጉዳዩን ለመፍታት የሰጡትን መመሪያ የጣሰ እንዲሁም ተገቢ መፍትሄ ለመስጠት የማያስችልም ነው፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ልዩነቶችን ለመፍታት እድል የሚፈጥረውን የምክክር ሂደት ለማጠናከር እንደሚሰራ እየገለጸ በጉዳዩ ላይ የሚሰራጨው የመገናኛ ብዙሃን እንዲሁም ሌላ አሉታዊ ዘመቻ የሶስቱን አገራት መተማመን ከመሸርሸር ያለፈ ውጤት እንደማይኖረው ይገልጻል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በተደጋጋሚ እንደገለጸው የአባይን ውሃ የኢትዮጵያ ህዝቦችን የአሁን እና የወደፊት ፍላጎት ለማሟላት እና ብሄራዊ ጥቅምን ለማረጋገጥ ማልማቱን በመቀጠል ርትዕን የጠበቀ እና በማናቸውም የተፋሰሱ አገራት ላይ ጉልህ ጉዳት የማያደርስ አጠቃቀም እንዲኖር ይሰራል፡፡
በተጨማሪ የኢትዮጵያ መንግስት በሕዳሴ ግድብ ላይ በሚደረገው ውይይት የሚከተለው አቅጣጫ የናይል ውሃን አስመልክቶ ለተደረጉት እና በኢትዮጵያ ላይ ምንም አይነት ተፈጻሚነት የሌላቸውን ስምምነቶች እውቅና የማይሰጥ እንዲሁም የላይኛውን የናይል ተፋሰስ አገራት መብት የማይጥስ እንዲሆን ነው መባሉን ከኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መግለጫ ያመለክታል፡፡

ኢትዮጵያ ንቁ ተሳትፎ ያደረገችበት 74ኛው የመንግስታቱ ድርጅት ጉባኤ ተጠናቀቀ
ሀዋሳ፡ መስከረም 20/2012 ዓ.ም (ደሬቴድ) በጉባኤው ላይ ኢትዮጵያ በፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው በተመራ የልዑካን ቡድኗ በኩል ንቁ ተሳትፎ አድርጋለች።
ኢትዮጵያ ጉባኤውን በምክትል ፕሬዝዳንትነት መርታለች፤ 80 በሚሆኑ የጉባኤው መድረኮች ላይም ተሳትፋለች።
የአየር ንብረት ለውጥ፣ የዓለም የጤና ሁኔታና መሰል ዓለም ዓቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ኢትዮጵያ ገንቢ ሃሳቦችን አካፍላለች።
ከጉባኤው ጎን ለጎንም ከተለያዩ አገራት መሪዎችና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ውይይት ተደርጓል።
እንደ ኢቢሲ ዘገባ በአሜሪካ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ፍጹም አረጋም በጉባኤው ተሳትፈዋል፡፡

የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ ነው - ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ

ሀዋሳ፡ መስከረም 16/2012 ዓ.ም (ደሬቴድ) በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው የልማት ተግባራት አንዱ በማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራበት መሆኑን ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ ገለጹ፡፡

በኢትዮጵያ በህጻናት ላይ የሚታየውን የመቀንጨር ችግር ለመፍታት የተቀረጸው የሰቆጣ የውሳኔ ሃሳብ ላይ የሚመክረው ጉባኤ በኒውዮርክ ተካሂዷል፡፡

በዚህ መድረክ ላይ ንግግር ያደረጉት ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ እንዳሉት ኢትዮጵያ ባለፉት 16 ዓመታት የህጻናት መቀንጨርን በ20 በመቶ መቀነስ ችላለች፡፡

ከአንድ ዓመት በፊት የጸደቀው የምግብና የስርዓተ ምግብ ፖሊሲ መቀንጨርን ለመከላከል የተቀረጸውን የሰቆጣን የውሳኔ ሀሳብ ተግባራዊ ለማድረግ ቀልፍ እርምጃ ነው ብለዋል፡፡

ችግሩን ለመቅረፍም ከሁሉም አጋሮች ጋር ተባብሮ ለመስራት ኢትዮጵያ ያላትን ቁርጠኝነት የገለጹት ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ አጋር አካላትም ድጋፋቸውን የበለጠ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በስብሰባው ላይ የተሳተፉት አጋሮች በበኩላቸው እስካሁን የተገኘው ውጤት አበረታች መሆኑን ነው ያመለከቱት፡፡

በቀጣይም በሰቆጣ የውሳኔ ሀሳብ ላይ የተቀመጡት ግቦች እንዲሳኩ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በቅርበት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል፡፡

ጥናቶች እንደሚጠቁሙት በኢትዮጵያ 38 በመቶ የሚሆኑት ህጻናት የመቀንጨር ችግር ያጋጥማቸዋል፡፡

ምንጭ፡- የፕሬዝዳንት ጽ/ቤት

 

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ 5ኛው ብሔራዊ የገለልተኛ የሳይንሳዊ ጥናት ቡድን ስብሰባ ተጀመረ

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ 5ኛው ብሔራዊ የገለልተኛ የሳይንሳዊ ጥናት ቡድን ስብሰባ በካርቱም ሱዳን መካሄድ ጀመረ።
የጥናት ቡድኑ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽን ያሳተፈ ሲሆን በግድቡ የውኃ ሙሌትና አለቃቀቅ ዙሪያ የሚመክር ገለልተኛ አካል ነው ተብሏል፡፡
የጥናት ቡድኑ እ.አ.አ ከመስከረም 15 እስከ16/2019 በካይሮ በተደረገው ስብሰባ ወቅት በሦስቱ አገራት የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች በተለዩ አጀንዳዎች ላይ በመወያየት እ.አ.አ ከጥቅምት 4 እስከ 5 2019 በካርቱም በሚካሄደው የሦስቱ አገራት ውሃ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ሪፖርት እንደሚያቀርብ ይጠበቃል።

ምንጭ፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

በዓባይ ወንዝ ዙሪያ ከትብብር ውጪ ሌላ አማራጭ የለም - ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ

ሀዋሳ፡ መስከረም 16/2012 ዓ.ም (ደሬቴድ) የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በ74ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ንግግር አድርገዋል።
ፕሬዚዳንቷ በአማርኛ ባደረጉት ንግግራቸው በኢትዮጵያ የተጀመረውን ለውጥ ተከትሎ መንግስት በበርካታ ዘርፎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህ መሰረትም የዜጎችን ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብት በማስከበር፣ በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በሴቶች ተሳትፎና በተለያዩ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ አመርቂ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ በንግድና ኢንቨስትመንት ዙሪያ የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ በመቀመር በርካታ ስራዎች እያከናወነች መሆኗንም አክለዋል።
በመንግስት ይዞታ ስር የነበሩ የልማት ድርጅቶች ወደ ግል ይዞታ የማዘዋወር ስራ የሀገር ተጠቃሚነትን ባረጋገጥ መልኩ ለማከናወን እንቅስቃሴ መጀመሩንም አንስተዋል።
የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተም ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት መርሃ ግብር በመቅረፅ አበረታቸ ስራ መስራቷን ነው የተናገሩት።
በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ያለውን የፀጥታና የደህንነት ሁኔታ ከማስከበር አንፃርም ኢትዮጵያ የአንበሳውን ድርሻ እየተወጣች የምትገኝ መሆኑን አውስተዋል።
እንደ ኤፍቢሲ ዘገባ የአባይ ወንዝ በተመለከተ ባደረጉት ንግግርም ወንዙ ለተፋሰሱ ሀገራት የጋራ ሃብት እንጂ የጥርጣሬ እና የውድድር ምንጭ ሊሆን አይገባም ነው ያሉት።
የአባይን ወንዝ የጋራ ተጠቃሚነትን ባረጋገጠ መልኩ ለመጠቀምም የተፋሰሱ ሀገራት በትብብርና በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ አፍሪካ በመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክርቤት ቋሚ መቀመጫ አንዲኖራት ጠይቀዋል።

Subcategories

የቅጂ መብት © 2019 ደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት