በዓባይ ወንዝ ዙሪያ ከትብብር ውጪ ሌላ አማራጭ የለም - ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ

ሀዋሳ፡ መስከረም 16/2012 ዓ.ም (ደሬቴድ) የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በ74ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ንግግር አድርገዋል።
ፕሬዚዳንቷ በአማርኛ ባደረጉት ንግግራቸው በኢትዮጵያ የተጀመረውን ለውጥ ተከትሎ መንግስት በበርካታ ዘርፎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህ መሰረትም የዜጎችን ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብት በማስከበር፣ በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በሴቶች ተሳትፎና በተለያዩ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ አመርቂ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ በንግድና ኢንቨስትመንት ዙሪያ የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ በመቀመር በርካታ ስራዎች እያከናወነች መሆኗንም አክለዋል።
በመንግስት ይዞታ ስር የነበሩ የልማት ድርጅቶች ወደ ግል ይዞታ የማዘዋወር ስራ የሀገር ተጠቃሚነትን ባረጋገጥ መልኩ ለማከናወን እንቅስቃሴ መጀመሩንም አንስተዋል።
የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተም ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት መርሃ ግብር በመቅረፅ አበረታቸ ስራ መስራቷን ነው የተናገሩት።
በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ያለውን የፀጥታና የደህንነት ሁኔታ ከማስከበር አንፃርም ኢትዮጵያ የአንበሳውን ድርሻ እየተወጣች የምትገኝ መሆኑን አውስተዋል።
እንደ ኤፍቢሲ ዘገባ የአባይ ወንዝ በተመለከተ ባደረጉት ንግግርም ወንዙ ለተፋሰሱ ሀገራት የጋራ ሃብት እንጂ የጥርጣሬ እና የውድድር ምንጭ ሊሆን አይገባም ነው ያሉት።
የአባይን ወንዝ የጋራ ተጠቃሚነትን ባረጋገጠ መልኩ ለመጠቀምም የተፋሰሱ ሀገራት በትብብርና በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ አፍሪካ በመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክርቤት ቋሚ መቀመጫ አንዲኖራት ጠይቀዋል።

ምርጫ ቦርድ የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ አማራጭ ምልክቶችን ይፋ አደረገ

ሀዋሳ፡ መስከረም 15/2012 ዓ.ም (ደሬቴድ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ህዝበ ውሳኔ የሚካሄድባቸውን አማራጭ ምልክቶች ይፋ አደረገ።

ቦርዱ ሕዳር 3 ቀን 2012 ዓ.ም የሲዳማን ዞን የክልልነት ጥያቄ ተከትሎ ለማካሄድ ላቀደው ሕዝበ ውሳኔ አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረገ መሆኑ ይታወቃል።

ሁለቱ የህዝበ ውሳኔ አማራጭ ሃሳቦች የሚወከሉበትን ምልክቶች ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልልና ከሲዳማ ዞን ምክር ቤት ጋር በመምከር ሁለት አማራጭ ምልክቶችን ይፋ አድርጓል።

በዚሁ መሰረት ”ሲዳማ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ውስጥ እንዲቆይ እፈልጋለሁ” ለሚለው አማራጭ የጎጆ ቤት ምልክት እንዲሆን ወስኗል።
እንዲሁም ”ሲዳማ ራሱን ችሎ በክልልነት እንዲደራጅ እፈልጋለሁ” ለሚለው አማራጭ የሻፌታ ምልክት ሆኖ ለህዝበ ውሳኔው ድምጽ መስጫነት እንዲያገለግል የተወሰነ መሆኑን ቦርዱ በላከው መግለጫ አስታውቋል። (ኢዜአ)

የምስራቅ አፍሪካ አገራት አመራሮች ለፈጠሩት ሰላምና የኢኮኖሚ ትስስር እውቅና ተቸራቸው

 

የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ፣ የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂና የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሙሃመድ አብዱላሂ የኮንኮርዲያ ዓመታዊ የአመራር ሽልማት አሸናፊ ሆነው ተመረጡ።

መሪዎቹ ሽልማቱን አሸናፊ የሆኑት በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ባሉ አገሮች መካከል ለተፈጠረው ሰላም እና የኢኮኖሚ ትስስር ላበረከቱት አስተዋጽፆ ነው።

ሶስቱ አመራሮች ተቀራርበውና ተደጋግፈው መስራት በመቻላቸው በአካባቢው ሰላም እንዲሰፍን እንዲሁም የኢኮኖሚ ትስስር እንዲፈጠር በማድረጋቸው የኮንኮርዲያ ዓመታዊ የአመራር ሽልማት አሸናፊ ለመሆን እንዳበቃቸው ሽልማቱን ያዘጋጀው ድርጅት ገልጿል።

ሽልማቱን በተባበሩት መንግስታት ስብሰበባ ላይ እየተካፈሉ የሚገኙት የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሙሃመድ አብዱላሂ ተቀብለዋል። ፕሬዚዳንቱ በሽልማቱን በተቀበሉበት ወቅት የቀጠናውን ሰላም ቀጣይነት ለማረጋገጥ የበለጠ እንደሚሰሩ ገልጸዋል ሲል ድርጅቱ በድረገጹ አስፍሯል።

የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው በዮ.. ማስቃላ በዓል ለጋሞ ዞን ሕዝብ መልዕክት አስተላለፉ

የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ርስቱ ይርዳው የዮ.. ማስቃላ በዓልን አስመልክቶ መልዕክት አስተላለፉ፡፡

በመልዕክታቸው የጋሞ ዞን ህዝብ ራሱን፣ አካባቢውን ብሎም ሀገሩን ወደ ብልጽግና ለማሻጋገር ከመቼውም ጊዜ በላቀ ትጋት መንቀሳቀስ አለበት ብለዋል፡፡

 

የዞኑ ወጣቶችም አባቶች ያስጠበቁትን የሰላምና የይቅርታ ወርቅ ባህል በመረከብ ምክንያታዊነትን፣ አብሮነትን፣ ትብብርን፣ ሰላምና ፍቅርን መርህ በማድረግ የዞኑን ብሎም የክልሉን ህዝቦች የለውጥ ፍላጎት እውን እንዲሆን በመስራት ታሪካቸውን በደማቅ ቀለም እንዲጽፉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

 

ምሁራንም የጋሞ አባቶች ተንበርክከው እና እርጥብ ሳር ይዘው ለምድሪቱ ሰላም ያወረዱበትን ድንቅ ዕሴት በማጎልበት፣ ለሰላም፣ ለልማትና ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የምርምር ስራዎችን በማቅረብና ሳይንሳዊ ድጋፍ በመስጠት ድህነትንና ኋላቀርነትን በመታገል የዜግነት ግዴታቸውን መወጣት እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል፡፡

ምንጭ፡ የጋሞ ዞን አስተዳደር የህዝብ ግንኙነት ጽ/ቤት

 

 

ኢትዮጵያ በመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ ላስመዘገበችው ውጤት የዕውቅና ሽልማት አገኘች

 

ሀዋሳ፡ መስከረም 14/2012 ዓ.ም (ደሬቴድ) ኢትዮጵያ በመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ ላስመዘገበችው ውጤት የዕውቅና ሽልማት ማግኘቷን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

 

በኒውዮርክ ከተማ እየተካሄደ ባለው የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ ላስመዘገበችው ውጤት የዕውቅና ሽልማት ለፕሬዝደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተበርክቶላቸዋል::

ዉጤቱ ሊዘገብ የቻለው የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ የጀርባ አጥንት ሆነው በሚሰሩት የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች ትጋት እንደሆነ የጤና ሚኒስቴር ገልጿል::

ይህንን የዕውቅና ሽልማት ያበረከተው አክሰስ ቻሌንጅ በመባል የሚታወቅ መቀመጫውን አሜሪካን ሀገር ያደረገ በጤና እና ትምህርት ተደራሽነት ላይ የሚሰራ ድርጅት መሆኑ ተጠቁሟል::
ሽልማቱን ዶክተር ጽዮን ፍሬው ኢትዮጵያን በመወከል ተቀብላለች::

ምንጭ፡ የጤና ሚኒስቴር

Subcategories

የቅጂ መብት © 2019 ደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት