ደቡብ አፍሪካ በናይጄሪያ የሚገኘውን ኤምባሲዋን ዘጋች

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 30/2011 ዓ.ም (ደሬቴድ) ደቡብ አፍሪካ በናይጄሪያ የሚገኘውን ኤምባሲዋን ለመዝጋት የተገደደችው በደቡብ አፍሪካ ናይጄሪያውያን ላይ እየደረሰ ባለው ጥቃት ምክንያት በናይጄሪያ ኤምባሲዋ ላይ የአፀፋ ጥቃት በመሰንዘሩ ነው።

ባለፈው ሳምንት እሁድ የጀመረው በሌላ አፍሪካ ሃገራት ዜጎች ላይ ያነጣጠረው ጥቃት እስከ ዛሬዋ እለት ድረስ ቀጥሎ የብዙዎች ንብረት ተዘርፏል፤ ወድሟልም።

የናይጀሪያ መንግሥት ጥቃቱን ያወገዘው ሲሆን የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርም በበኩላቸው ድርጊቱ አሳፋሪ እንደሆነ ተናግረዋል።

ናሌዲ ፓንዶር “በውጭ ሀገራት ዜጎች ላይ እየደረሰ ባለው ጥቃት እንዲሁም በንብረታቸው መውደም ከፍተኛ ሀዘን ተሰምቶናል” ማለታቸውን የሀገሪቱ ሚዲያ ኤስኤቢሲ ዘግቧል።

በናይጄሪያ መዲና አቡጃ የሚገኘውን የደቡብ አፍሪካ ኤምባሲ ለመዝጋት የተገደዱት በኤምባሲው በሚሰሩ ሰራተኞች ላይ ማስፈራሪያና ዛቻ ከደረሰባቸው በኋላ እንደሆነ ሚኒስትሯ ለሮይተርስ ተናግረዋል።

ምንጭ፡ ቢቢሲ