የወባ ወረርሽኝ እንዳይከሰት ህብረተሰቡ ከወዲሁ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ሊያደርግ ይገባል ተባለ
 
ሀዋሳ፡ ነሐሴ 30/2011 ዓ.ም (ደሬቴድ) የወባ ወረርሽኝ እንዳይከሰት ህብረተሰቡ ከወዲሁ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ሊያደርግ እንደሚገባ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
 
የክረምት ዝናብን ተከትሎ በአብዛኛው ከመስከረም እስከ ታህሳስ ወር ዋነኛ የወባ መተላለፊያ ወቅት መሆኑንና ህብረተሰቡ ቀድሞ ጥንቃቄ እንዲያደርግ የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክተር ወይዘሮ ሕይወት ሰለሞን አሳስበዋል፡፡
 
75 በመቶ የሚሆነው የሀገራችን ክፍል ለወባ በሽታ ስርጭት አመቺ ሲሆን 60 በመቶ የሚሆነው ህዝብም በእነዚህ አካባቢዎች ይኖራል፡፡
 
በመሆኑም ህብረተሰቡ አጎበር እንዲጠቀም፣ የበሽታው ስሜት ሲኖር ቶሎ ወደ ህክምና መስጫ ማዕከላት እንዲሄድ እንዲሁም ለወባ በሽታ አምጪ ትንኝ መራቢያ አመች የሆኑ የታቆሩ ውሃዎችን ማፋሰስና ማዳረቅ የሚጠበቅ መሆኑን ዳይሬክተሯ ጠቁመዋል፡፡
 
በማያያዝም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት፣ ክልሎች፤ ዞኖች፣ ወረዳዎችና የጤና ተቋማት የተጠናከረ የወባ በሽታ ክትትልና ቅኝትን በቀጣዮቹ ወራት ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል፡፡