ወይዘሮ ሂሩት በኢትዮጵያ የደቡብ አፍሪካ አምባሳደር ጋር ተወያዩ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 30/2011 ዓ.ም (ደሬቴድ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ በኢትዮጵያ የደቡብ አፍሪካ አምባሳደር ንዱሚሶ ንሺንጋን በዛሬው ዕለት በጽህፈት ቤታቸው አነጋግረዋል።

በዚህ ወቅትም በኢትዮጵያና በደቡብ አፍሪካ መካከል ያለውን የጠበቀ ታሪካዊ ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እየተሰራ መሆኑን ወይዘሮ ሂሩት ተናግረዋል።

ሰሞኑን ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ በደቡብ አፍሪካ በሚኖሩ የሌሎች አፍሪካ ሀገር ዜጎች ላይ በደረሰው ጥቃትና የንብረት ዝርፊያ በእጅጉ ማዘናቸውንም ገልጸዋል።

ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ያስተላለፉት መልዕክት አበረታች መሆኑንና በጉዳዩ የተሳተፉ ጥፋተኞች ለህግ እንደሚቀርቡ ያላቸውን እምነት መግለፃቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

መንግስት በደቡብ አፍሪካ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አስፈለጊውን ጥበቃ እንዲያደርግላቸውም ጠይቀዋል።
አምባሳደር ንዱሚሶ ንሺንጋን በበኩላቸው በደቡብ አፍሪካ የተከሰተው ድርጊት ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው አሳዛኝ ድርጊት መሆኑን አንስተዋል።

የደቡብ አፍሪካ መንግስት ለጉዳዩ ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ በመሆኑ ነገሮች በፍጥነት ወደነበሩበት እንደሚመለሱ ያላቸውን እምነትም አስታውቀዋል ሲል ኤፍቢሲ ዘግቧል።