ሚኒስቴሩ በደቡብ አፍሪካ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በውጭ ሃገር ዜጎች ላይ እየተፈጸመ ያለውን ጥቃት አወገዘ
 
ሀዋሳ፡ ነሐሴ 29/2011 ዓ.ም (ደሬቴድ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በደቡብ አፍሪካ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የውጭ ሃገር ዜጎችን ኢላማ ባደረገ መልኩ እየተፈጸመ ያለውን ጥቃት አወገዘ።
 
የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዜጎችን በተመለከተ መግለጫ አውጥቷል።
በመግለጫውም በደቡብ አፍሪካ ኢትዮጵያውያን ዜጎችን ጨምሮ በውጭ ሃገር ዜጎች ላይ እየተፈጸመ ያለውን የንብረት ዘረፋና ጥቃት በፅኑ እንደሚያወግዝ አስታውቋል።
 
ሚኒስቴሩ በመግለጫው የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ድርጊቱን አውግዘው ያወጡት መግለጫ በአድናቆት የሚያበረታታ መሆኑንም ገልጿል።
 
ፕሬዚዳንቱ በድርጊቱ የተሳተፉ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል ለህግ ለማቅረብ መወሰናቸው ተስፋ ሰጭ መሆኑንም በመግለጫው አመላክቷል።
 
ሚኒስቴሩ የደቡብ አፍሪካ ባለስልጣናት ለጉዳዩ እልባት ለመስጠትና በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ የሚያደርጉትን ጥረት በቅርበት እንደሚከታተለውም አስታውቋል ሲል ኤፍቢሲ ዘግቧል።