በደቡብ አፍሪካ በተቀሰቀሰው አመጽ መንግስታት ማስጠንቀቅያ እየሠጡ ነው

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 28/2011 ዓ.ም (ደሬቴድ) በደቡብ አፍሪካ ባለቤትነታቸው የውጭ ዜጎች የሆኑ የንግድ ማዕከላት ዒላማ ያደረገ አመጽ መቀስቀሱን ተከትሎ በርካታ የአፍሪካ ሃገራት ለዜጎቻቸው ደህንነት በማሰብ ማስጠንቀቂያ እየሰጡ ይገኛሉ፡፡

በደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ እንዳስታወቀው የንግድ ማእከል በሆነችው ጆሀንስበርግ ኢትዮጵያውያን ሱቆቻቸውን ከዝርፊያና ከቃጠሎ ለመታደግ እንዲዘጉ አሳስቧል፡፡

በሌላ በኩል የዚምባብዌ ትራንስፖርት ሚኒስቴር በደቡብ አፍሪካ ያለው ሁኔታ እስኪረጋጋ ድረስ የጭነት መኪኖች ወደዛ መጓዝ እንደሌለባቸው አስጠንቅቋል፡፡

እየወጡ ያሉ ዘገባዎችን መሰረት በማድረግም ሚኒስቴሩ የውጭ ሃገራት ከባድ መኪኖች ኢላማ መደረጋቸውንና በርካቶች መዘረፋቸውንም አስታውቋል፡፡

የናይጄሪያ መንግስት በበኩሉ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጎኦፍሪ ኦንየማ የቲውተር ገፅ እንዳስቀመጠው ጥቃቱ በዋነኝነት በናይጄሪያ የንግድ ስራ ላይ ያነጣጠረ መሆኑን ገልፆ “ይበቃችኋል” የሚል መልእክት አስተላልፏል፡፡

ሰኞ እለት የደቡብ አፍሪካ የፖሊስ ሚኒስትር በሀኪ ሰሌ እንዳሉት አመጹ ከውጪ ሃገር ሰዎች ጥላቻ ይልቅ ወደ ወንጀል ያመዝናል፤ ”ግብ የለሽ ድርጊት” ሲሉም አውግዘውታል ሲል የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ቢቢሲን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡