አዲሱ የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው ማን ናቸው?

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 27/2011 ዓ.ም (ደሬቴድ) 6ኛው እና ክልሉን በምክትል ርዕሰ መስተዳድርነት የሚያገለግሉት አቶ ርስቱ ይርዳው ማን ናቸው? የትና በየትኞቹ የስራ ተግባራት አገልግለዋል፡፡

ባለፉት 26 ዓመታት የደቡብ ክልልን 5 ርዕሳነ መስተዳድሮች በኃላፊነት አስተዳድረዋል፡፡

የደቡብ ክልልን በኃላፊነት የማስተዳደር ፖለቲካዊ ስልጣንን የወሰደው የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ በምክር ቤቱ ባለው ውክልና መንግስት እየሰየመም እያስተዳደረም ይገኛል፡፡

ባለፉት 26 ዓመታትም እነማን ሕዝቡን በርዕሰ መስተዳድርነት አገለገሉ ሲል የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የታሪክ ማህደርን ፈትሿል፡፡

በእነዚህ ጊዜያት አዲሱን ጨምሮ 6 የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች ክልሉን የማስተዳደር ኃላፊነት ተረክበዋል፡፡ የጉራጌ ዞንና ወረዳን አሰተዳድረው፤ በፌዴራል ከፍተኛ የስራ ቦታዎችም ያገለገሉት አቶ ርስቱ ይርዳው 6ኛውና ክልሉን በምክትል ርዕሰ መስተዳድርነት ያገለግሉ ዘንድ የክልሉ ምክር ቤት ሙሉ ይሁንታ ሰጥቷቸዋል፡፡

በዚህ ማዕረግም ክልሉን ሲመሩ እሳቸው የመጀመሪያው ሆነዋል፡፡
ከ1985 እስከ 1993 ዓ.ም ድረስ ክልሉን ለ8 ዓመታት ያህል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው ያገለገሉት አቶ አባተ ኪሾ ነበሩ፡፡ የእሳቸውን ዱካ በመከተልም አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ አራት አመታትን፣ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ደግሞ 7 ዓመታትን፣ ቀጥሎ አቶ ደሴ ዳልኬ በርዕሰ መስተዳድርነት ክልሉን ካገለገሉ በኋላ ለአቶ ሚሊዮን ማቲዎስ ስፍራውን አስረክበዋል፡፡

አቶ ሚሊዮን ማቲዎስም በክልሉ ምክር ቤት 5ኛው ዙር 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 9ኛ መደበኛ ጉባኤ የርዕሰ መስተዳድር ስልጣናቸውን በይፋ ለአቶ ርስቱ ይርዳው አስተላልፈዋል፡፡

አቶ ርስቱ ይርዳው 6ኛውና ክልሉን በምክትል ርዕሰ መስተዳድርነት እንዲያገለግሉ ቃለ መሃላ ፈጽመዋል፡፡

ለመሆኑ አቶ ርስቱ ማናቸው? በየትኞቹ ቦታዎችስ አገልግለዋል? ውልደትና እድገታቸው በጉራጌ ዞን እነሞርና ኤነር ወረዳ ጉንቹሬ ከተማ ነው፡፡ የቀለም ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁም ወረዳና ዞንን በአስተዳዳሪነት አገልግለው ወደ አፍሪካ መዲና አዲስ አበባ ለላቀ የአገልግሎት ስልጣን ታጭተው ከ2005 እስከ 2011 ዓ.ም ከአዲስ አበባ አስተዳደር እስከ ፌደራል የተለያዩ የስልጣን ቦታዎች ማገልገልም ችለዋል፡፡

አቶ ርስቱ ይርዳው በፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የክልል ጉዳዮች አማካሪ፣ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት የማህበራዊ ጉዳዮች ክትትል ሚኒስትር ዲኤታ፣ በግብርና ሚኒስቴር የታዳጊ ክልሎች ልዩ ድጋፍ ሚኒስትር ዲኤታ፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የኢኮኖሚ ዘርፍ አማካሪና የንግድ ቢሮ ኃላፊ፣ የኢፌዲሪ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር፣ የኢፌዲሪ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር በጥቅሉ የባለሙያነትን ሳይጨምር በዘጠኝ የተለያዩ የሹመት ቦታዎች አገልግለው ነው 10ኛውን የላቀ ህዝብ የማገልገል ስልጣን ጊዜው ሆኖ የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እንዲሆኑ ይሁንታ ያገኙት፡፡

የ44 ዓመቱ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው በትምህርት ዝግጅታቸው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በማኜጅመንት ሲሆን ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በከተማ ልማት አስተዳደር ተቀብለዋል፡፡

አዲሱ የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር በለውጥና ነውጥ ውስጥ ያሉ አያሌ የክልሉ ክፍተቶች ጎልተው በተስተዋሉበት ወቅት ነውና ወደ ስልጣን የመጡት ስራቸው እጅግ ትጋትን የሚሻ፣ ሁሉን በእኩል የሚያይ፣ ፍትሀዊነትን የሚያረጋግጡ፣ ከራስ ጥቅም ይልቅ ሀገራዊና ክልላዊ ለውጡን ማስቀጠልና ማሻገር የሚገባቸውን ተራማጅ የለውጥ አመራሮችን ከመሰየም እስከ ማስከተል እና ክልሉንም ሀገርንም ማሻገር ይጠበቅባቸዋል፡፡

ይህ ይሳካ ዘንድም ሁሉም የበኩሉን ጠጠር በመወርወር የስልጣን ጊዜያቸው በመልካም ስራ ታግዞ ለውጡን የሚያሳካ ይሆን ዘንድ ሁሉም ሊያግዛቸው ይገባል፡፡

የ44 ዓመቱ አዲሱ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው የክልሉን ህዝብ ከመምራት ባለፈ 3 ልጆቻቸውንና ቤተሰባቸውን እንደሚያስተዳድሩ ለመረዳት ችለናል፡፡ 
    ዘጋቢ፡ ታምራት ሽብሩ