በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አደጋ ሊያደርሱ ከሚችሉ አጋጣሚዎች ራሳቸውን እንዲጠብቁ ጥሪ ቀረበ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 27/2011 ዓ.ም (ደሬቴድ) በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አደጋ ሊያደርሱ ከሚችሉ አጋጣሚዎች በመራቅ ራሳቸውን እንዲጠብቁ በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስጠነቀቀ።

ኤምባሲው በደቡብ አፍሪካ በተለይም በውጭ ሃገር ዜጎች በሚንቀሳቀሱ የንግድ ድርጅቶች ላይ ዘረፋ እየተፈጸመ እና ግጭቶችና አለመረጋጋቶች እየተፈጠሩ መሆኑን የተለያዩ ምንጮችን ዋቢ አድርጎ ጠቅሷል።

በመሆኑም ኢትዮጵያውያን ዜጎች በእነዚህ ዘረፋዎች፣ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች ሰበብ በህይወት እና በአካል ላይ አደጋ ሊያደርሱ ከሚችሉ ማናቸውም አይነት ፍጥጫዎች እንዲርቁ አስጠንቅቋል።

ወቅታዊ ሁኔታው እስከሚረጋጋ ድረስ ውድና በቀላሉ ወደ ገንዘብ የሚቀየሩ ንብረቶች እንዳይዙ ማድረግና ከተቻለም ሁኔታው እስከሚረጋጋ ድረስ ሱቆችን አለመክፈት፤ እንዲሁም እርስ በእርስ መረጃዎችን በመለዋወጥ ሰላማዊ ያልሆኑ ዝንባሌዎች ሲያጋጥሙ ለአካባቢው ፖሊስ እንዲያሳውቁም ጠይቋል።

በተደራጀ መንገድ ከአካባቢው የጸጥታ አካላት እና ማህበረሰብ ጋር በቅርበት በመስራት ችግሮች እንዳይከሰቱና ከተከሰቱም በውይይት እንዲፈቱ መስራት ያስፈልጋልም ብሏል ኤምባሲው።

ከዚህ ባለፈም ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ መረጃዎችን ለመስጠትና ድጋፍ ለማግኘት የኤምባሲውን የቀጥታ የስልክ ቁጥሮች 012 346 42 57 እና 012 346 29 47 መጠቀም እንደሚችሉም አስታውቋል።

የደቡብ አፍሪካ መንግስት ለዘላቂ መፍትሄ የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው ያለው ኤምባሲው፤ ሚሲዮኑ የሚያስተባብረው በኢጋድ አምባሳደሮች ፎረም በአፍሪካውያን ዜጎች ላይ የደረሰው ችግር እንደ አጀንዳ ተወስዶ የሃገሪቱ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ኃላፊዎች በተገኙበት ውይይት እንደተደረገበትም ጠቁሟል።

በዚህም ለጉዳዩ አጽንኦት ተሰጥቶት ተከታታይነት ያለው የጋራ መድረክ እንዲፈጠርና በሃገሪቱ በሚኖሩ የውጭ ዜጎች ጉዳይ ምክክሮችን ለማድረግ ሁኔታዎች እንዲመቻቹ መጠየቁንም አንስቷል።

ዘረፋዎች፣ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች ዜጎች ላይ የከፋ ጉዳት ሳያስከትሉ መፍትሄ እንዲያገኙም መረጃዎችን ለሚመለከታቸው የደቡብ አፍሪካ የመንግስት አካላት አቅርቦ እየተከታተለ መሆኑንም ገልጿል።

ኤምባሲው ለዜጎች መብትና ደህንነት መጠበቅ የጀመረውን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥልና በዚህ ረገድ መረጃዎችን ተከታትሎ ለዜጎች እንደሚያደርስ መግለጹን ኤቢሲ ዘግቧል፡፡