ለሰላም ግንባታ ዩኒቨርሲቲዎች የሚጠበቅባቸውን ያህል አልተወጡም ተባለ
 
ሀዋሳ፡ ነሐሴ 28/2011 ዓ.ም (ደሬቴድ) በሰላም ግንባታ ዙሪያ ከፍተኛ የመንግስት የትምህርት ተቋማት የሚጠበቅባቸውን ያህል አልተወጡም ተባለ፡፡
 
ለሰላም ግንባታ የዪኒቨርሲቲዎች ሚና በሚል መሪ ቃል የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከምሁራንና ተማሪዎች ጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል፡፡
 
የሀዋሳ ዩንቨርሲቲ የህግና ጉድ ገቨርናንስ ትምህርት ክፍል ከሴንተር ኦፍ ኮንሰርን ጋር በመተባበር ለሰላም ግንባታ የዩኒቨርሲቲዎች ሚና በሚል መሪ ቃል ከምሁራንና የሁለተኛ ዲግሪ የሰላምና ግጭት አፈታት የሚያጠኑ ተማሪዎችን ያሳተፈ የምክክር መድረክ አካሂዷል፡፡
 
ዩኒቨርሲቲዎች የግጭት መንስኤዎች ሳይሆኑ ግጭቶች ቢፈጠሩ እንኳ መፍትሄዎችን በማበጀትና ትንተናዎችን በመስጠት ለሰላም መስፈን የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ያሉት በመድረኩ የመነሻ ሀሳብ ያቀረቡት በሰላም ማህበረሰብ ድርጅቶች መረጃ ማዕከል ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ ኩሲያ በቀለ ናቸው፡፡
 
በተለይም ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተስተዋለው የሰላም እጦት ዙሪያ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አወንታዊ ሚናቸውን ማበርከት ሲገባቸው ዝምታን መርጠዋል ሲሉ አቶ ኩሲያ ተናግረዋል፡፡
 
ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ወይም ዩኒቨርሲቲዎች ግጭት ሳይከሰት በፊት የግጭት አዝማሚያዎችን በማጥናት አስቀድሞ የመከላከል ስልትን በመንደፍ የድርሻቸውን መወጣት እንደሚገባቸው ገልፀዋል፡፡
 
ከፍተኛ የመንግስት የትምህርት ተቋማት ዓለምአቀፍ አስተሳሰቦች የሚንሸራሸሩባቸው ቢሆኑም በኢትዮጵያ ግን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በዚህ ቁመና ላይ አይገኙም ያሉት በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የአንትሮፖሎጂ መምህር ዶክተር መለሰ ማዳ ናቸው፡፡
 
ዩኒቨርሲቲዎች የሚጠበቅባቸውን ሊወጡ የሚችሉት ከፖለቲካዊ ወገንተኝነት በፀዳ መልኩ ከተንቀሳቀሱ ነው ሲሉ ሀሳባቸውን ገልፀዋል፡፡
 
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በአንፃራዊ ሰላማዊ የትምህርት ጊዜያትን ቢያሳልፍም በሰላም እሴት ግንባታ ረገድ ከራስ ባለፈ ለውጭው ማህበረሰብ ማበርከት የሚገባውን ያህል አልሰራም የሚሉት በዩኒቨርሲቲው የህግና ጉድ ገቨርናንስ ኮሌጅ ዲን ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ ናቸው፡፡ ዩኒቨርሲቲው በቀጣይም በርካታ የቤት ሥራዎች ይጠብቁታል ብለዋል፡፡
 
በሰላምና ግጭት አፈታት የትምህርት ዘርፍ የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ደመቀች ዳዊትና ደስታ ሙሉጌታ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ያላቸውን ተደማጭነት ለሰላምና ለሀገራዊ አንድነት በማዋል ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ያሳስባሉ፡፡
ዘጋቢ፡ ማሬ ቃጦ