በደቡብ ክልል ከ13 ሺህ 500 በላይ ህገወጥ የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ
 
ሀዋሳ፡ ግንቦት 14/2012 ዓ.ም (ደሬቴድ) በደቡብ ክልል ከ13 ሺህ 500 በላይ ህገወጥ የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ መወሰዱን የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡
 
የደቡብ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ወጤ ቶሼ የኢድ ዓልፈጥርን በዓል ምክንያት በማድረግ የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ እንዳይደረግ እና በግብይት ቦታዎች ለቫይረሱ ተጋላጭነት እንዳይኖር የጥንቃቄ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
 
ዳይሬክተሩ ዛሬ ባስተላለፉት መልዕክት ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ በህገወጥ ተግባር ላይ በተሰማሩ የንግዱ ማህበረሰብ ላይ ክትትልና ቁጥጥር ለማድረግ በየደረጃው የዋጋ ማረጋጋት ግብረ ኃይል በማደራጀት ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡
 
በዚህም 13 ሺህ 515 ህገወጥ የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ መወሰዱን እና ከ2 ሚሊየን በላይ የቅጣት ገንዘብ ለመንግስት ገቢ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡
 
በክልሉ ያለው የግብይት ስርዓት በጠባብ ቦታ የታጨቀ በመሆኑ ለኮሮና ቫይረስ ተጋላጭነትን ለመቀነስ በተሰራው ስራ 283 የነበረውን ወደ 534 ማስፋት መቻሉን የተናገሩት ዳይሬክተሩ አያይዘውም ለአዲስ የገበያ ስፍራዎችም አስፈላጊውን መሰረተ ልማት የማሟላት ተግባር እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
 
ምርትን በመጋዝን በማቆየት የአቅርቦት እጥረት በሚፈጥሩ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ በመውሰድ የተቀመጡ ምርቶች ወደ ገበያ እንዲወጡ መደረጉን አቶ ወጤ ተናግረዋል፡፡
 
የገበያ አቅርቦት ክፍተትን ለመሙላት 19 ዩኒየኖችና 129 የህብረት ስራ ማህበራት ምርት ከሚገኝባቸው አካባቢዎች የማሰባሰብ ስራ በማከናወናቸው እስከ አሁን ባለው ሂደት ከ47 ሺ ኩንታል በላይ ምርት ተሰባስቦ ለገበያ እየቀረበ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
 
በኢድ አልፈጥር በዓል ምክንያት የሸማቹ ቁጥር ስለሚጨምር አጋጣሚውን ለመጠቀም ምርትን ለጤንነት አስጊ ከሆኑ ባዕድ ነገሮች ጋር በመቀላቀል የሚሸጡ ነጋዴዎች ሊኖሩ ስለሚችሉ ሸማቹ ማህበረሰብ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጠቁመዋል፡፡
 
አቶ ወጤ ከቆዳና ሌጦ ዘርፍ ጋር በተያያዘ ለበዓሉ የሚታረዱ እንስሳት ቆዳቸው በጥንቃቄ፣ በጥራትና በአግባቡ ተሰብስቦ ለማዕከላዊ ገበያ እንዲቀርብ ሁሉም የበኩሉን ኃላፊነት እንዲወጣ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
 
በሀገራችን ኮሮና ቫይረስ ከተከሰተበት ማግስት ጀምሮ አላስፈላጊ ትርፍ ለማጋበስ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ህገወጥ ነጋዴዎችን ለህግ አሳልፈው በመስጠት እና ገበያ እንዲረጋጋ በመስራት የበኩላቸውን ሚና የተወጡ ታማኝ ነጋዴዎችንም አመስግነዋል፡፡
 
በበዓል ገበያ የሸማቹ ቁጥር ስለሚጨምር የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ሸማቹና የንግዱ ህብረተሰብ ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግና አላስፈላጊ ንኪኪዎችን በማስወገድ ርቀታቸውን ጠብቀው እንዲገበያዩ አቶ ወጤ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
 
ምክንያታዊ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉትና ባዕድ ነገር ቀላቅለው በሚሸጡ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ለመውሰድ እንዲቻል ህብረተሰቡ በ8034 ነጻ የስልክ መስመር ጥቆማ በመስጠት የበኩሉን ኃላፊነት እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ኢያሱ ሽፈራው