የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳው ለ1441ኛው ኢድ-አልፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

 

ሀዋሳ፡ ግንቦት 14/2012 ዓ.ም (ደሬቴድ) የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳው ለእስልምና እምነት ተከታዮች ለ1441ኛው ኢድ-አልፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

 

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው “የክልላችን እና የሀገራችን የእስልምና እምነት ተከታዮች ለኢድ-አልፈጥር በዓል እንኳን በሰላም አደረሳችሁ፣ ኢድ ሙባረክ!” ብለዋል፡፡

 

ህዝበ ሙስሊሙ ያለፈው አንድ ወር ለዓለማችንና ለህዝባችን ሰላምና ደህንነት በጾምና በጸሎት ፈጣሪን ሲለምንና ሲማፀን የቆየበት ታላቁ የረመዳን ፆም ጊዜ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

 

አቶ እርስቱ በዓሉ በጋራ በመሰባሰብ በተለያዩ ሀይማኖታዊ ስርዓቶች በድምቀት የሚከበር ቢሆንም ዘንድሮ በሀገራችን በተጋረጠው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በአደባባይና በመስጅድ በጋራ ማክበር የሚቻል አልሆነም ብለዋል፡፡

 

“የዘንድሮውን የኢድ አልፈጥር በዓል ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ተጠንቅቀን በመሻገር ቀጣዩን ዓመት እንደወትሮው ማክበር እንድንችል ፈጣሪ ይርዳን” በማለት መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡

 

የእምነቱ ተከታዮች በየቤታቸው በመሆን በዓሉን ሲያከብሩ አከላዊ ርቀታቸውን በጠበቀ መልኩ መሆን እንዳለበት ያሳሰቡት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በዓሉን እንደተለመደው የተቸገሩትን በማሰብና በመደጋገፍ ማሳለፍ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

    

ህዝበ ሙስሊሙ የኢድ-አልፈጥርን በዓል ሲያከብርም ሆነ ለበዓሉ የተለያዩ ዝግጅቶችንና እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል በመንግስት የወጡ መመሪያዎችን እና በሕክምና ባለሙያዎች የሚሰጡ ምክሮችን ተግባራዊ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ኢያሱ ሽፈራው