በኢትዮጵያ ዘላቂ የሆነ የዲሞክራሲዊ ስርዓት ለመገንባት ምርጫው መራዘሙ ምክንያታዊ መሆኑ ተገለፀ

 

ሀዋሳ፡ ሚያዝያ 29/2012 ዓ.ም (ደሬቴድ) በኢትዮጵያ ዘላቂ የሆነ የዲሞክራሲዊ ስርዓት ለመገንባት ምርጫው መራዘሙ ምክንያታዊ መሆኑን በደቡብ ክልል የሚንቀሳቀሱ አንድ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በሀዋሳ ከተማ ባደረጉት ውይይት ገልፀዋል፡፡

 

በውይይቱ የተሳተፉት የደቡብ ብልጽግና ፓርቲ፣ የወላይታ ሕዝቦች ዴሞክራሲዊ ግንባር (ወህዴግ)፣ የጌዲኦ ሕዝብ ዴሞክረሲያዊ ደርጅት ሲሆኑ ምርጫ መራዘሙን በተመለከተ የየፓርቲያቸውን አቋም ለጋዜጠኞች አብራርተዋል፡፡

 

በነሀሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሊካሄድ የታቀደው ምርጫ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው ወረርሽኝ ኮቪድ-19 ምክንያት ማካሄድ ያለመቻሉ ምክንያታዊና ተገቢ እንደሆነ የተናገሩት የጌዲኦ ሕዝብ ዴሞክረሲያዊ ደርጅት ሊቀመንበር የሆኑት አቶ አለሣ መንገሻ ናቸው፡፡

 

ምርጫ መራዘሙንም ለወከላቸው ህዝብ ለማስገንዘብ ፓርቲያቸው ከፌዴራልና ከክልል መንግስት ጋር በጋራ እንደሚሰራ አብራርተዋል፡፡

 

በደቡብ ብልጸግና ፓርቲ የዲሞክራሲያዊ ተቋማት ዘርፍ ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር አንተነህ ሙሉ ምርጫ መራዘመን በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

 

የኢትጵዮያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ዘንድሮ ነሀሴ 23 ይደረጋል ብሎ ባወጣው መርሃ ግብር መሰረት ስራዎች በመከናወን ላይ እንደነበሩ ጠቁመው ይሁን እንጂ መርሃ ግብሩን ለማስፈፀም በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ማካሄድ ያለመቻሉን ገልጸዋል፡፡

 

በኢትዮጵያ የይስሙላ ምርጫ ማካሂድ ሳይሆን ዘላቂ የሆነ የዲሞክራሲ ስርዓት ለመገንባትና የተሻለ ጠንካር መንግሰት ለመፍጠር እንደሆነ ረዳት ፕሮፌሰሩ አንስተዋል፡፡

 

አክለውም ገዥው ፓርቲና ተፎካካሪ ፓርቲዎች የህብረተሰቡን ደህንነት ለመጠበቅና  እንዲሁም አማራጭ ፕሮግራሞቻቸውንና ፖሊሲዎቻቸውን ለመራጭ ህዝብ ለመግለጽ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ምርጫው መራዘሙ ተገቢ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

 

የወላይታ ህዝቦች ዴሞክራሲዊ ግንባር (ወህዴግ) ማዕከላዊ ኮሚቴ ፀሀፊ አቶ ሙሉጌታ አኔቦ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫ ማራዘሙ ተገቢ ያለመሆኑ ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ፋሲል ኃይሉ