በደቡብ ክልል የኮሮና ቫይረስን ለመቆጣጠር ቤት ለቤት የሚደረገው አሰሳ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው ተገለፀ

ሀዋሳ፡ ሚያዝያ 26/2012 ዓ.ም (ደሬቴድ) በደቡብ ክልል የኮሮና ቫይረስን ለመቆጣጠር ቤት ለቤት የሚደረገው አሰሳ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው ገልጸዋል፡፡

 

የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው በተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

 

በደቡብ ክልል ቤት ለቤት በተደረገ አሰሳ 325 ሺህ ቤቶች ላይ አሰሳ መደረጉንና 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ለሚሆን ህዝብ አሰሳ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡ ይህንንም አሰሳ አጠናክሮ መቀጠሉ ቫይረሱን ለመከላከል ለሚደረገው ጥረት ውጤታማነት ይረዳል ብለዋል፡፡

 

በቅርቡ በስልጤ ዞን ስልጢ ወረዳ የተገኙት የ45 ዓመት ሴት ቤት ለቤት በተደረገ አሰሳ እንደሆነ ተናግረው በቫይረሱ ከተያዙት ግለሰብ ጋር ንክኪ ይኖራቸዋል ተብሎ የተገመቱ አስራ ስድስት ሰዎች ወደ ለይቶ በማቆያ መግባታቸውን አስረድተዋል፡፡

ግለሰቧ በበሽታው የተያዙበት መንገድ ግልጽ ባለመሆኑ ለቫይረሱ የተጋለጡበት መንገድ  እስከሚገኝ ድረስ የንክኪ ምንጩን ፍለጋው ተጠናክሮ እንደሚቀጠል ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ ጠቁመዋል፡፡

 

ከሞያሌ ተነስቶ ሀላባ ዞን ከተገኝው የ25 ዓመት ወጣት ጋር ንክኪ አላቸው ተብሎ የተገመቱ 37 ሰዎች ወደ ቤተሰቦቻቸው ሳይቀላቀሉ ወደ ለይቶ ማቆያ የገቡ ሲሆን ከግለሰቡ ጋር ንክኪ አላቸው ተብሎ የተገመቱ ሌሎች አራት ሰዎች ባለመገኘታው የእነዚህ ሰዎች ፍለጋ ተጠናከሮ መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡

 

በተጨማሪም ከግለሰቡ ጋር ንክኪ አላቸው ተብሎ ሚገመቱ 113 ሰዎች ወደ ለይቶ ማቆያ መግባታቸውን ተውቋል፡፡

 

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በመግለጫቸው በሁለተኛነት ትኩረት አድርገው የገለጹት የወባ ወረርሽኝ ስጋት በክልሉ መኖሩን ነው፡፡

 

በዘጠኝ ዞንና በአንድ ልዩ ወረዳ የወባ ወረርሽኝ ስጋት እንዳለ ጠቁመው ህብረሰተቡ የጤና ኤክስቴንሽ ባለሙያዎች ሚሰጡትን የጥንቃቄ መረጃ በመተግበር ለወባ የሚያጋልጡ ነገሮችን ላይ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በደቡብ ኦሞ፣ በጎፋና በጋሞ ዞኖች በሚገኙ አምስት ወረዳዎች የኮሌራ በሽታ መከሰቱን የገልፁት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ከዚህ በፊት በሽታውን የመከላከል ስራ በመሰራቱ የቀነሰ ቢሆንም በአመስት ወረዳዎች ግን በሽታው ጥንቃቄ አንዲደረግ አሳስበዋል፡፡

 

በልዩ ሁኔታ ኮሌራ በሽታ ለታየባቸው አካበቢዎች የንጹህ ውሃ መጠጥ አቅርቡት በመደረግ ለይ እንዳለ አክለው ገልፀዋል፡፡

 

በመጨረሻም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የአሰሳ ቡድንና የጤና ባለሙያዎች ለሚያደርጉት ያላሰለሰ ጥረት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ፋሲል ኃይሉ