በደቡብ ክልል በኮሮና ቫይረስ የተያዘ ተጨማሪ አንድ ሰው መገኘቱ ተገለጸ

 

ሀዋሳ፡ ሚያዝያ 25/2012 ዓ.ም (ደሬቴድ) በደቡብ ክልል በኮሮና ቫይረስ የተያዘ ተጨማሪ አንድ ሰው መገኘቱን የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ አቅናው ካውዛ ገልጸዋል፡፡

 

በስልጤ ዞን ስልጢ ወረዳ ጡጦ ዞጋሬ ቀበሌ አካባቢ ነዋሪ የሆኑት የ45 ዓመት ሴት በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠው ቤት ለቤት በተደረገ አሰሳ መሆኑ ታውቋል፡፡

 

ግለሰቧ በተለምዶ የጉልት ስራ ተብሎ በሚጠራው ግብይት የሚተዳደሩ ሲሆን የጉዞ ታሪክ እንደሌላቸው ተገልጿል፡፡

 

ሰባት የቤተሰቡ አባላትና ጎረቤቶቻቸው ጭምሮ ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ መደረጉን የቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

 

በቫይረሱ የተያዙት ሴት ባለቤት በተደረገለት ምርመራ ከቫይረሱ ነፃ መሆኑን ኃላፊው ጠቁመው በክልሉ በድምሩ ሁለት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መኖራቸውን አስታውቀዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ፋሲል ኃይሉ