የኮሮና ቫይረስ እንዳይስፋፋ በሚደረገው ጥረት በህብረተሰቡ ውስጥ መዘናጋት መታየቱ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ሚያዝያ 22/2012 ዓ.ም (ደሬቴድ) የኮሮና ቫይረስ እንዳይስፋፋ በሚደረገው ጥረት በህብረተሰቡ ውስጥ መዘናጋት መታየቱን የደቡብ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሰናይት ሰለሞን በፅህፈት ቤታቸው ዛሬ ገልፀዋል፡፡

በደቡብ በክልል የኮሮና ቫይረሱ ባይከሰትም በቀጣይ መቼ ሊከሰት እንደሚችል መገመት ሰለማይቻል ህብረተሰቡ ከዚህ በፊት ሲወስድ የነበረውን ጥንቃቄ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው ተናግረዋል፡፡

በቅርቡ በተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሰረት አዋጁን በሚተላለፉ አካላት ላይ እርምጃ በመወሰድ ላይ እንደሆነና በዚህም 1 ሺህ 712 አሽከርካሪዎች አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ጥሰው በመገኘታቸው አስተማሪ እርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ 1 ሺህ 821 በንግድ ዘርፍ የተሰማሩ አካላት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተላልፈው በመገኝታቸው ህጋዊ እርምጃ መወሰዱን ጠቅሰው በንግዱ ዘርፍ ላይ የሚገኙ አካላት ቫይረሱን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት እገዛቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሰረት የሚወሰዱ እርምጃዎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል፡፡

በመጨረሻም የአዋጁ አፈፃጸምን በተመለከተ ሚዲያዎች ትኩረት አድርገው አንዲሰሩ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ፋሲል ኃይሉ