ኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ለሚደረገው ትግል ባለድርሻ አካላት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ መጎልበት እንደሚገባ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ሚያዝያ 08/2012 ዓ.ም (ደሬቴድ) ኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ለሚደረገው ትግል የተለያዩ ባለድርሻ አካለት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ መጎልበት እንደሚገባ የደቡብ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ላይ ተናግረዋል፡፡

ለመላዉ የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ካስተላለፍ በኃላ ኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ለሚደረገው ጥረት ለተለያዩ ባለድርሻ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የተለያዩ ሙያ ማህበራት፣የሴቶች አደረጃጀት፣ወጣቶች፣የኪነ- ጥበብ ባለሙያዎች፣የእግር ኳስ ማህበራት ከደቡብ ብልጽግና ፓርቲ ጋር በመቀናጀት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ላደረጉት ስራ አቶ ጥላሁን ከበደ አመስግነዋል፡፡

በክልሉ ለሚገኙ የቤተዕምነት መሪዎችና የሃይማኖት አባቶች፣አገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶችና ሠራተኞች፣በክልሉ የሚገኙ ተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮችና አባላት፣ሚዲያ አመራሮችና ባለሙያዎች፣የፀጥታ አካለትና ሌሎች ባለ ድርቫ አካላት የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ለሚደረገው ጥረት የተሰጣቸውን ኃላፊነት በተገቢው በመወጣት ላይ እንደሚገኙ ገልጸው በቀጣይ እገዛቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል፡፡

በክልሉ የሚገኙ ተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮችና አባላት በዚህ ጊዜ ስለ ልዩነት የሚወራበት ሳይሆን ከሁሉም በላይ ለሆነዉ ክቡር የሰዉ ልጅ ህይወት መታደግ የውዴታ ግዴታ በሆነበት ጊዜ ላይ መሆኑ ተናግረው ይህንን የችግር ጊዜ ልባዊ ትብብርና ርብርብ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡

ይህንን የችግር ጊዜ መሻገር የምንችለው ተደጋግፈን በጋራ መቆም ብቻ መሆኑን ጠቁመው ከክልሉ አመራር ጎን በመሆን ባህላዊና ሃይማኖታዊ ስርዓታችንን በመጠቀም መረዳዳት፣ መተጋገዝ፣ መከባበር፣ ይቅር መባባልን አስፈላጊ መሆኑ አብራርተዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ፋሲል ኃይሉ