የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ ሜሪ ጆይ ማዕከልን ጎበኙ

ሀዋሳ፡ መጋቢት 11/2012 ዓ.ም (ደሬቴድ) የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ እና የከተማው አስተዳደር ካቢኔ አባላት የሀዋሳ ሜሪ ጆይ ማዕከልን ጉብኝተዋል::

የሜሪ ጆይ መስራችና ስራ አስኪያጅ ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ ለሀዋሳ ከተማ ምክትል ከንቲባ ተቋሙን፣ በተለያዮ ተቋማት አማካኝነት ለሜሪ ጆይ የተደረጉ ድጋፎችንና አረጋዊያኑ የሚገለገሉባቸው ክፍሎች የሚገኙበትን ደረጃ አስጎብኝተዋል::

ህብረተሰቡና መንግስት ለሜሪ ጆይ ሁለገብ ማዕከል የሚያደርጉት ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከሜሪ ጆይ ምስረታ ጀምሮ አጋርነቱ ባለመለየቱ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በተቋሙ የውሃ፣ የመብራት እና በመኖሪያ ቤታቸው ሆነው ለሚረዱ አረጋዊያን ምግብ ለማድረስ የተሽከርካሪ እጥረት አንዳለ ሲስተር ዘቢደር አንስተዋል፡፡

አያይዘውም የመንግስት ሰራተኛው በቋሚነት በየወሩ ከደመወዙ የአንድ ብር ድጋፍ አንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ባለው አቅም ለሜሪ ጆይ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ አንደሚቀጥል ምክትል ከንቲባው ተናግረው የውሃ እና የመብራት ችግሮች በአጭር ጊዜ ውስጥ ምላሽ እንደሚያገኙ ቃል ገብተዋል፡፡

በማዕከሉ ለሚኖሩ አረጋዊያን የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር በየዓመቱ የሚታደስ የጤና ኢንሹራንስ ሽፋን እንደሚደርግ ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል፡፡

በተያያዘም ከመንግስት ሰራተኞች ከወርሃዊ ደመወዝ አንድ ብር በቋሚነት እንዲቆረጥ ለማድረግ ከከተማው ካቢኔና ከመንግስት ሰራተኞች ጋር ውይይት በማድርግ ምላሽ እንደሚሰጡ ገልጸዋል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ ለሳኒቴሽን አገልግሎት የሚውሉ አልኮሎች እና የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ቁሳቁሶችን ደጋፍ ማድረጉ ተውቋል፡፡
ዘጋቢ፡ ፋሲል ኃይሉ