በደቡብ ክልል በ216 የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ ተወሰደ

ሀዋሳ፡ መጋቢት 10/2012 ዓ.ም (ደሬቴድ) በደቡብ ክልል ህገወጥ ተግባር ሲፈፅሙ በተገኙ 216 የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ መውሰዱን የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡

የደቡብ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሂክማ ከይረዲን ህገ ወጥ ንግድን ለመከላከል የተከናወኑ ተግባራትን በተመለከተ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

ኃላፊዋ በመግለጫቸው በንግዱ ማህበረሰብ የሚታየውን ህገ ወጥ ተግባርና የዋጋ ጭማሪ ለመቆጣጠር ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ከክልል ጀምሮ እስከታችኛው መዋቅር ድረስ በአካል በመገኘት የቁጥጥር ተግባር እያከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ግብረ ኃይሉ ባከናወነው የቁጥጥር ስራ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ፣ ባዕድ ነገር ሲቀላቅሉ እጅ ከፍንጅ በተያዙ እና ጊዜ ያለፈባቸው ምርቶችን ሲሸጡ በተገኙ 216 የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ መውሰዱን ወይዘሮ ሂክማ ገልፀዋል፡፡

በተደረገው ፍተሻም 6 ግለሰቦች ባዕድ ነገር ሲቀላቅሉ እጅ ከፍንጅ በመያዛቸው የንግድ ድርጅታቸውን ከማሸግ ባለፈ ተይዘው በህግ እንዲጠየቁ ተደርጓል ብለዋል፡፡

በሀገር ውስጥ የኮሮና ቫይረስ መከሰቱን ተከትሎ በህገ ወጥ ተግባር ተሰማርተው በተገኙ መድሀኒት ቤቶች ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በተደረገው ቁጥጥር እርምጃ መወሰዱንም ኃላፊዋ ጠቁመዋል፡፡

ወይዘሮ ሂክማ በመግለጫቸው የንግዱ ማህበረሰብ የስራ ባህሪያቸው ከበርካታ ደንበኞቻቸው ጋር የሚያገናኛቸው ስለሆነ ከአላስፈላጊ ንኪኪ በመቆጠብ፤ የእጅ ንጽህናቸውን በመጠበቅና መከላከያ በመጠቀም እራሳቸውንና ማህበረሰቡን ከኮሮና ቫይረስ እንዲከላከሉም አሳስበዋል፡፡

ህብረተሰቡም ግብረ ኃይሉ የሚያደርገውን የቁጥጥር ስራ በማገዝ እና በህገ ወጥ ተግባር ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች ሲያጋጥማቸው ለዚሁ በተዘጋጀው 8034 የስልክ መስመር ጥቆማ በመስጠት እንዲተባበርም ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ኢያሱ ሽፈራው